By Jochebed Kinfemichael Suga, 4th year medical student at Myungsung Medical College

ጆኬቤድ ክንፈሚካኤል ሱጋ (ሚዩንግሱንግ ህክምና ኮሌጅ የ፬ አመት ተማሪ)

Reviewed/Approved  by: Dr. Fitsum Tilahun (Editor at Yetena Weg/ Nephrologist)

 

በደንብ ያልታከመ የስኳር ህመም ከሚያመጣቸዉ ችግሮች ውስጥ አንዱ እና ዋነኛዉ የኩላሊት በሽታ ነዉ፡፡ ከስኳር ጋር ተያይዞ የሚመጣ የኩላሊት በሽታ የኩላሊት የማጣራት አቅምን በማዳከም በሰዉነታችን ውስጥ ቆሻሻ እና ፈሳሽ እንዲጠራቀም ያደርጋል፡፡ ይህም ቀስ በቀስ ስር በመስደድ የኩላሊትን ሙሉ በሙሉ ስራ ማቆምን ያስከትላል፡፡

የስኳር በሽታ የኩላሊት ችግርን እንዴት ሊያመጣ ይችላል?

በደማችን ውስጥ የስኳር መጠን መጨመር በኩላሊታችን ዉስጥ በሚገኙት ትንንሽ የደም ቧንቧዎች ላይ ጉዳት በማድረስ በተፈጥሮ በኩላሊት የማይወገዱ ፕሮቲኖች በሽንት ውስጥ እንዲወጡ ያደርጋል፡፡ ይህም ሲቀጥል ቀስ በቀስ የኩላሊት የማጣራት አቅምን በማዳከም በኩላሊቶቻችን በኩል የሚወገዱ በሰዉነታችን ዉስጥ ያሉ ቆሻሻ ውህዶች እዛዉ እንዲቀሩ በማድረግ በሰውነታችን ላይ ችግር ይፈጥራል፡፡

የኩላሊት በሽታ ከስኳር ጋር የተያያዘ ነው ለማለት ዋነኛዉ መስፈርት በደም ዉስጥ የስኳር መጠን መጨምር ቢሆንም ከዛ ባለፈ በርካታ ምክንያቶች አስተዋፅዖ ያደርጋሉ፡፡ ከነዚህም ዉስጥ የሰዉነት ግፊት መጨመር እና የሰዉነት የስብ መጠን መጨመር ዋነኞቹ ናቸዉ፡፡ እነዚህ አስተዋፅዖዎች በኩላሊት ላይ ብቻቸውን ከሚያደርጉት ተፅዕኖ ይልቅ በደም ዉስጥ የስኳር መጠን መጨመር አንዱ ለሌላኛዉ ኩላሊት መጎዳት አመቺ ሁኔታን በመፍጠር የኩላሊት ህመም በፍጥነት ስር እንዲሰድ ያደርጋሉ፡፡

ከስኳር በሽታ ጋር ተያይዞ ለሚመጣ የኩላሊት ችግር አስተዋፅዖ የሚያደርጉት ምንድናቸዉ?

በደንብ ያልታከመ ከፍተኛ የስኳር መጠን

በደንብ ያልታከመ ከፍተኛ የደም ግፊት

ማጨስ

የኮሌስትሮል መጠን መጨመር

የሰውነት እንቅስቃሴ አለማድረግ

ተመላላሽ ወይም ስር የሰደደ የኩላሊት ኢንፌክሽን

በደም ዉስጥ ከፍተኛ የዩሪያ መጠን መኖር (hyperuricemia)

አስቀድሞውኑ ከስኳር በሽታ ጋር ያልተያያዘ የኩላሊት በሽታ መኖር

የእድሜ መጨመር

ለረጅም ጊዜ የስኳር በሽታ ታማሚ መሆን

 

ከስኳር በሽታ ጋር ተያይዞ የሚመጣ የኩላሊት ችግር ምልክቶች ምንድን ናቸዉ?

አብዛኛዉን ጊዜ ከስኳር በሽታ ጋር ተያይዞ የሚመጣ የኩላሊት በሽታ ኩላሊት ላይ ጉዳት ማድረስ ሲጀምር ግልፅ የሆኑ ምልክቶችን አያሳይም፡፡ ምልክት የሚያሰጥ ደረጃ እስኪደርስ ድረስ ብዙ አመታትን ይወስዳል፡፡ ስለዚህም የኩላሊት የጉዳት ደረጃዉ እስኪጨምር ድረስ ያለምልክት ሊቆይ ይችላል፡፡ የኩላሊት ጉዳት መጠኑ የመጨረሻ ደረጃ ሲደርስ ግን ኩላሊት የማጣራት እና ሌሎች ስራዎቹን ማቆም ይጀምራል፡፡ በዚህን ጊዜም የበሽታውን ምልክቶች ማስተዋል እንጀምራለን፡፡እነዚህም ምልክቶች

የሰውነት ማበጥ

የድካም ስሜት

ራስ ምታት

ማቅለሽለሽ እና ማስመለስ

የምግብ ፍላጎት መቀነስ

ከስኳር በሽታ ጋር ተያይዞ ለሚመጣ የኩላሊት በሽታ የመለያ ምርመራዎች ምንድናቸዉ?

ማንኛዉም የስኳር ታማሚ በሚያደርገዉ መደበኛ ክትትል ሀኪሙ የኩላሊቱን የጤና ሁኔታ ለመከታተል የተለያዩ የሽንት እና የደም ምርመራዎችን ያደርጋል፡፡

የሽንት ምርመራ፡ በዚህ የምርመራ አይነት ባልተለመደ ሁኔታ ከፍ ብሎ ያለ የፕሮቲን መጠንን እና የኢንፌክሽን መኖር እና አለመኖርን ለማረጋገጥ የሚደረግ ነዉ፡፡

የደም ምርመራ፡ የኩላሊት መድከም እና ስራ ማቆም በሚጀምርበት ሰአት በደም ዉስጥ የሚገኙ የኩላሊት መስራት ወይም አለመስራትን ወይም መጎዳትን የሚያሳዩ ውህዶችን ለማየት የሚደረግ ምርመራ ነዉ፡፡

የአልትራሳዉንድ ምርመራ: የኩላሊታችንን መጠን ለማወቅ ይረዳናል::

የኩላሊት ባዮፕሲ: ብዙን ጊዜ በሀገራችን ላይ ባይሰራም ከስኳር በሽታ ሌላ መንስኤን ሲጠረጠር የሚያደርጉት ምርምራ ነው::

እነዚህ ምርመራዎች የኩላሊቱን አጠቃላይ ሁኔታ ስለሚነግሩን ኩላሊታችን በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ለማወቅ ይረዱናል፡፡

አንድ የስኳር ታማሚ የኩላሊት በሽታ ምልክቶችን ማሳየት በሚጀምርበት ወቅት በአይኑ ላይ ከስኳር በሽታ ጋር የተያያዘ ችግር ይኖራል ተብሎ ስለሚታሰብ የአይን ምርመራ ማድረግ ይኖርበታል::

ከስኳር በሽታ ጋር ተያይዞ የሚመጣ የኩላሊት ችግር እንዴት ይታከማል?

ከስኳር በሽታ ጋር ተያይዞ የሚመጣ የኩላሊት በሽታ ፈዋሽ የሚባል ህክምና የለውም፡፡ ነገር ግን በኩላሊት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ማዘግየት ወይም ስር እንዳይሰድ ማድረግ ይቻላል፡፡ ከኩላሊት ጋር ተያይዘዉ ለሚመጡ ችግሮች መድሃኒቶችን በመስጠት የሚደረግ ህክምና እና የኩላሊት መስራት አቅም ሲቀንስ ደግሞ የኩላሊት እጥበት መጀመር አለበት፡፡ ሆኖም ነገሩ ሲከፋ በኩላሊት እጥበት ብቻ መኖር ስለማያስችል እነዚህ ታካሚዎች የኩላሊት ንቅለ ተከላ ያስፈልጋቸዋል፡፡

ከስኳር በሽታ ጋር ተያይዞ የሚመጣን የኩላሊት በሽታ እንዴት መከላከል ይቻላል?

ማንኛዉም የስኳር ታማሚ የሆነ ሰዉ ከስኳር ጋር ተያይዞ የሚመጣን የኩላሊት በሽታ ለመከላከል ቢያንስ በአመት አንድ ጊዜ ምርመራ ማድረግ አለበት፡፡ ይህም በስኳር በሽታ ምክንያት የሚኖር የኩላሊት ችግርን አስቀድሞ በማወቅ ስር ሳይሰድ መቆጣጠር ያስችላል፡፡

ከስኳር በሽታ ጋር ተያይዞ ለሚመጣ የኩላሊት በሽታ ዋነኛዉ ህክምና በደም ውስጥ ያለዉን የስኳር መጠን መቆጣጠር ነዉ፡፡ ስለሆነም የስኳር በሽታ ተጠቂ የሆነ ሰው ለሚሰጡት መድሃኒቶች በአግባቡ መጠቀም እና የስኳር መጠኑን መቆጣጠር ያስፈልጋል፡፡

የደም ግፊት እና ከፍተኛ የኮሌስትሮል መጠንን መቆጣጠር

የሰዉነት ክብደት መጠንን መቆጣጠር

ጤናማ አመጋገብ እና የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ

 

እነዚህን መከላከያ መንገዶች ከስኳር በሽታ ጋር ተያይዞ የሚመጣን የኩላሊት በሽታ ማዘግየት እና ስር ሳይሰድ ለማወቅ ይረዱናል፡:

 

የጤና ወግ 

ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።

የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።

https://linktr.ee/Yetena_Weg