ጥበብ የቋንቋ እና ቃላት ውስንነትን በማለፍ የማይዳሰሱትን የሰው ልጅ እይታዎች ለሌሎች በማስተላለፍ ለረዥም ጊዜ ከፍተኛ ሚና ሲጫወት ቆይቷል። ከታሪክ ምስክርነት እንደምንረዳው የስነ-ጥበብ እና የሕክምና ቅርኝት ለጤናው ዘርፍ ላቅ ያለ አዎንታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል።
የጥበብ እና የህክምና ግንኙነት እንዴት ይተነተናል?
በጥበብ የታገዘ ህክምና ህመምተኞች ዘና እንዲሉ፣ ጭንቀትን እንዲቀንሱ እና ለፈውስ እንዲበረታቱ፤ በተጨማሪም ሥር የሰደደ ህመምን፣ ካንሰርን፣ የአእምሮ ጤና መታወክን ጨምሮ የተለያዩ የጤና ጉዳቶችን እንዲቋቋሙ ይረዳቸዋል።
በህክናምው መስክ ስነ-ጥበብ ስዎች ፍላጎታቸውን፣ ስሜታቸውንና ህመማቸውን ምስላዊ ቋንቋን በመጠቀም እንዲገልጹ ትልቅ አስተዋጽዎ አድርጓል። የስነ-ጥበብ ውጤቶች በተለያዩ የታሪክ ምዕራፋት አካላዊ እና ስሜታዊ ሁነቶችን እጅጉን ባማረና በሚስብ መንገድ ገልፀውታል።
ለምሳሌ የዝነኛዋን ሜክሲኳዊት አርቲስት ፍሪዳ ካህሎ ማራኪ ስእሎችን እንውሰድ። ፍሪዳ ደፋርና ኮርኳሪ በሆነው የቁም ሥዕሎቿ የሰአሊዋን አካላዊና ውስጣዊ ህመም አሳይታበታለች። የጥበብ ስራዎቿ በተመሳሳይ ፈተና ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ቋንቋና ዘር ሳይገድባቸው የራሳቸውን ህመም እንዲያዩ፣ እንዲሁም እራሳቸውን እንዲገልጹና ለማህበረሰባዊ ማናቃቅያነት እንዲጠቀሙበት አስችሏቸዋል።
ከትዳር አጋሯና ሰአሊ ከነበረው ባለቤቷ ከተፋታች በኋላ የሳለችው Autorretrato con Collar de Espinas የሚል ርዕስ ያለው የራስ ምስል ውስጣዊ ትግልና ስሜትቷን በሚገርም ሁኔታ አሳይታበታለች። ስለዚህ ምስል ተጨማሪ ለማንበብ The Importance of Frida Kahlo’s Self-Portrait With Thorn Necklace and Hummingbird – ArtsperMagazine
ስነ-ጥበብ እና የአእምሮ ጤና
ስነ-ጥበብ ለዘመናት የአእምሮ ጤና እክል ያለባቸው ታካሚዎች መጽናኛ፣ ህመማቸውን መተፍፈሻና የመዳኛ መንገድ በመሆን አገልግሏል። ስፍር ቁጥር የሌላቸውን የአለማችንን ህዝቦች ስሜት መንካት የቻለውን የአስደናቂው የቪንሰንት ቫን ጎግ ስራዎችን እንመልከት። የቫን ጎግ ገላጭ ብሩሾች እና ደማቅ ቀለሞች በጊዜው የነበረበትን የአእምሮ ውዥንብር ጥልቀት በሚያስደምም ሁኔታ አሳይተዋል፤ የሄደበትን መንገድ ውበት እና ተጋድሎም በሚያስገርም መልኩ ገልፀዋል፤ ክዚህም ባለፈ የሰዕሎቹ ተመልካቾች ሁሉ በስራዎቹ ውስጥ የራሳቸውን ስሜት ውስብስብነት እንዲፈትሹ እድል ስጥተዋል።
ቫን ጎግ በፈረንጆች 1889 ወደ የአእምሮ መታከሚያ ሆስፒታል ገብቶ በህክምና ሲረዳ በነበረበት ጊዜ “The Starry Night.” የሚል ስያሜ ያለው ታዋቂ ሰዕሉን ለአለም አበርክቷል። ሰዕሎቹ ባጠቃላይ ሰአሊው የሚሰማውን ምስቅልቅል፣ መንፈሳዊ የድህነት (የመዳን) ጉዞና የህይወት ልምዱን የሚገልጽባቸው መንገዶች ሆነው አገልግለውታል። ሰዕሎቹ ከህይወቱ ውጣ ውረድ ጋር ያላቸውን ቁርኝት ይህን ጽሁፍ ያንብቡ። Vincent Van Gogh: An Artistic Journey In The Darkness of Life. | by TimeTrails | ILLUMINATION | Medium
ስነ-ጥበብ እና የህክምና ትምህርት
የሕክምና ትምህርት ቤት ተማሪዎች ስነ ጥበብን የትምህርታቸው አካል ቢያደርጉ የአስተዋይነትን እና ለስራቸው ጠቃሚ ክህሎቶች እንዲያዳብሩ በእጅጉ ይረዳቸዋል ። የጤና ባለሙያዎች ከጥበብ ጋር በመተዋወቃቸው ለታካሚዎቻቸው ርህራሄ እና ግንዛቤን እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል፤ ይህም የተሻለ እንክብካቤ እንዲሰጡ በማድረግ የታካሚዎችን የአገልግሎት ጥራት ከፍ እንዲል ያደርጋል። ከዚህም በተጨማሪ ፈጠራን በማበረታታት የታካሚ እንክብካቤን የሚያሻሽሉ አዳዲስ አቀራረቦችን እና ቴክኒኮችን ወደተግባር እንዲለወጡ ያስችላቸዋል።
በሌላ በኩል የጤና አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትም ይበልጥ የሚያረጋጋ እና ፈውስን የሚያበረታታ አካባቢ ለመፍጠር በመጠባበቂያ ክፍሎች፣ ኮሪደሮች እና በታካሚዎች ክፍል ውስጥ የስነ-ጥበብ ስራዎችን ማሳየት ይችላሉ።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት የስነ-ጥበብ ኮርሶችን የሚወስዱ የህክምና ተማሪዎች ከማይወድሱት በላቀ ሁኔታ ራሳቸውን የመመልከት፣ ደካማ ጎናቸውን የማየት ምስቅልቅሎችን የመቀበል አቅማቸው የትሻሉ ሆነው ተገኝተዋል። ተማሪዎቹ በተለይም ነገሮችን ከሌሎች አንጻር የመመልከት አቅምና የሌሎችን አጣብቂኝ የመረዳት ክህሎት አዳብረው ተገኝተዋል።
ስነ-ጥበብ እንደ ግንዛቤ ማስጨበጫ
ጥበብ ስለ ጤና ጉዳዮች ግንዛቤ ለማስጨበጥ እና ማህበራዊ ለውጦችን ለማነሳሳት ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል፤ ለምሳሌ እንቅፋቶችን በማለፍ የተገለሉ ማህበረሰቦችን ለመድረስ፣ ድምፃቸውን ለማጉላት እና የጤና ፍላጎቶቻቸውን የመደገፍ ልዩ አቅም አለው። በአርቲስቶች እና በጤና ባለሙያዎች መካከል ባለው የፈጠራ ትብብር፣ የፍትሃዊ ጤና አገልግሎት ተደራሽነትን መንገድ በመክፈት እና የማህበረሰብ ደህንነትን ለማረጋገጥ ይረዳል።
ትውልደ ኢትዮጵያዊት አይዳ ሙሉነህ ካናዳ በተካሄደው ቴክስታይል ኤግዚቢሽን ሙዚየም ላይ ባቀረበችው ዲጂታል ፎቶግራፍ ላይ የብዙዎችን ቀልብ ለመያዝ ችላለች። በስራዋ ስለ ንፁህ ውሃ እጥረት እና ውሀን ለመቅዳት ረጅም መንገድ ስለሚጓዙት ልጃገረዶች የትምህርት እና ማህበራዊ ህይወት መጉላላት አመላክታለች። በዚህ ስራዋ ውሃ የልጃገረዶቹ ህይወት ላይ ያለውን ትልቅ ተጽዕኖ አሳይታለች።
በመጨረሻም ጥበብ ሰዎችን በመሰብሰብ እና የማህበረሰባዊ አንድነት ስሜትን በመፍጠር ለታካሚዎች፣ ቤተሰቦች እና ጤና ባለሙያዎች የበለጠ እንግዳ ተቀባይ እና አካታች አስተሳሰብን መፍጠር ይችላል።
ጥበብን በሕክምና ልምምድ ውስጥ ማካተት ብዙ ጥቅሞችን ሊያስገኝ ቢችልም ፣ የጤና ባለሙያዎች ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ አንዳንድ ተግዳሮቶችም አሉ። ከሥልጠና እጥረት እና የገንዘብ ድጋፍ እጦት እስከ የጊዜ እጥረት ያሉት ሁኔታዎች ኪነጥበብን ከህክምና ጋር ያለችግር የሚያካትት ሥርዓትን ለመፍጠር ፈታኝ ያደርጉታል።
መፍትሄዎች
በኪነጥበብ ላይ የተመሰረተ የህክምና ስልጠናን ማዋቀር እና ከሥነ-ጥበብ ቴራፒስቶች ወይም ከሌሎች የፈጠራ ባለሙያዎች ጋር በመተባበር መስራት ይቻላል።
በተጨማሪም የጤና ባለሙያዎች ከውጭ ምንጮች የገንዘብ እርዳታ መፈለግ ወይም ከሆስፒታል አስተዳዳሪዎች ጋር በበጀት ዙርያ በመነጋገር ውጤታማ በሆነ መንገድ ለዚህ ሀሳብ ድጋፍ መጠየቅ ይችላሉ። ጥበብን አሁን ከተነደፉት ዕቅዶች ጋር ማዋሃድ እና ከሌሎች የጤና ባለሙያዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ከላይ የተጠቀሱትን ፈተናዎች ማሸነፍ ይቻላል።
ኪነጥበብን ያማከለ ህክምና ውጤታማንትን ለመጨመር የታካሚ ምርጫዎችን መገምገም እና የእያንዳንዱን ታካሚ ፍላጎት ማጤን ሊያስፈልግ ይችላል። ይህም ውጤታማነትን ለመለካት እና ተፅእኖውን ለማሳየት ፈታኝ ቢሆንም ፣ ከተመራማሪዎች እና ገምጋሚዎች ጋር በመተባበር ተገቢውን መረጃ በተሳካ ሁኔታ የመሰብሰብ እና የመለካት ችሎታን ማዳበር ሊያስፈልገን ይችላል።
የጤና-ወግ “ጥበብ እና ጤና – ጳጉሜ 4 እና 5/2015”
በኪነጥበብ እና በህክምና መካከል ባለው ጥልቅ ግንኙነት ላይ በመመስረት፣ እኛ የጤና ወጎች መጪውን “የጥበብ እና የጤና ኤግዚቢሽን” እነሆ ብለናል። ይህ ኤግዚቢሽን የስነ-ጥበብን እና የጤናን ቁርኝትን ሁለንተናዊ ተፈጥሮ ከሌሎች ጋር በመሆን የሚመረምሩበት እና የሚተነትኑበትን መድረክ አዘጋጅተናል።
የሰው ልጅ ስሜቶች እና ልምዶችን በጥልቀት በመመርመር በኪነጥበብ እና ጤና መካከል ስላለው ግንኙነት ሰፋ ያለ ግንዛቤ ያገኛሉ። ይህም የጤና ባለሙያዎች ዘለቅ ብለው ታካሚዎቻቸውን በጥልቀት እንዲረዱ እና ርህራሄን እንዲያጎለብቱ ይረዳል።
የጤና ወግ
ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።
የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።
https://linktr.ee/Yetena_Weg