የስኳር በሽታ ምንድነው ? አንዴት የኩላሊት ህመምን ያስከትላል ?
Tweet
የስኳር በሽታ ሰውነታችን በቂ የኢንሱሊን ንጥረ ነገር ማመንጨት ሳይችል ሲቀር አልያም የተመረተውን ኢንሱሊን በአግባቡ መጠቀም ሳይችል ሲቀር የሚከሰት በሽታ ነው።
ስንት እይነት የስኳር ህመም አለ?
በአብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ውስጥ የሚገኙት የስኳር በሽታ አይነቶች ሁለት ሲሆኑ፣ አይነት 1 እና አይነት 2 ይባላሉ። አይነት 1 የተባለው የስኳር በሽታ አብዛኛውን ጊዜ የሚከሰተው ልጆች ላይ ሲሆን በሌላ ስሙ ‘በልጅነት የሚከሰት የስኳር በሽታ’ ወይም ‘የኢንሱሊን ጥገኛ የስኳር በሽታ’ ይባላል። ይህ የስኳር ህመም የሚከሰተው ጣፊያ በቂ ያልሆነ የኢንሱሊን ንጥረነገር ማምረት በማይችልበት ጊዜ ነው፣ ይህም ማለት ህመምተኛው በህይወት ዘመኑ ሙሉ የኢንሱሊን ንጥረነገርን በመርፌ መልክ እየወሰደ ይኖራል ማለት ነው።
አይነት 2 የስኳር በሽታ የሚባለው ደግሞ በአብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል በስፋት የሚገኘው የስኳር በሽታ አይነት ነው። ይህ በሽታ አብዛኛውን ጊዜ የሚታየው እድሜያቸው ከ40 በላይ የሆኑ ሰዎች ላይ ሲሆን በሌላ ስሙ ‘በአዋቂነት እድሜ የሚከሰት የስኳር በሽታ’ ወይም ‘ የኢንሱሊን ጥገኛ ያልሆነ የስኳር በሽታ’ ይባላል። ይህኛው አይነት የስኳር ህመም ላይ ጣፊያ በቂ የሆነ የኢንሱሊን ንጥረነገር ማምረት ቢችልም፣ ሰውነታችን ግን የተመረተውን ኢንሱሊን ባግባቡ መጠቀም አይችልም። በደም ውስጥ የሚጠራቀመው ከፍተኛ የሆነ የስኳር መጠንም ሊስተካከል የሚችለው በሚወሰዱ መድሃኒቶች ብሎም የአመጋገብ ስርአትን በማስተካከል ነው። አንዳንድ ህመምተኞች ግን ኢንሱሊን መውሰድ ሊኖርባቸው ይችላል።
የስኳር በሽታ ኩላሊት ላይ የሚፈጥረው ችግር
የስኩር በሽታ ትንንሽ የደም ስሮችን ይጎዳል፣ ኩላሊት ውስጥ የሚገኙት ትንንሽ የደም ስሮች ሲጎዱ፣ ኩላሊታችን ደምን የማጣራት ተግባሩን በትክክል መከወን አይችልም። ይህ ማለትም፣ ሰውነታችን መያዝ ከሚገባው በላይ ውሃ እና ጨው ይይዛል ማለት ነው፣ ይህ ደግሞ ለክብደት መጨመር እና የእግር ማበጥ ያጋልጣል። ሽንት ውስጥ የፕሮቲን መጠን ይጨምራል፣ አንዲሁም መወገድ የሚገባቸው ኬሚካሎች ሰውነት ውስጥ ይከማቻሉ።
የስኳር በሽታ በተጓዳኝነት የነርቭ ጫፎችን ይጎዳል። ይህ ደግሞ ሽንት በመሽናት ጊዜ ችግር ሊፈጥር ይችላል። የሽንት መጠን በሽንት ፊኛ ውስጥ በሚበዛበት ጊዜ የሚፈጠረው ግፊት፣ ሽንት ወደ ኋላ ማለትም ወደ ኩላሊቶች እንዲመለስ ስለሚያደርገው ኩላሊትን ለ ኢንፌክሽን ሊያጋልጠው ይችላል፤ የስኳር ህመምተኞች ሽንት ውስጥ የሚገኘው ከፍተኛ የስኳር መጠን ለባክቴሪያዎች የተመቸ የመራቢያ ቦታ ነው።
ምን ያህሉ የስኳር ህመምተኞች ለኩላሊት ህመም የተጋለጡ ናቸው?
30 በመቶ የሚሆኑት የአይነት 1 ስኳር ህመምተኞች እንዲሁም ከ 10 እስከ 40 በመቶ የሚሆኑት የ አይነት 2 ስኳር ህመምተኞች ለከፍተኛ የኩላሊት ጉዳት የተጋለጡ ናቸው
የስኳር ህመምተኞች ላይ በመጀመሪያ የሚታዩ የኩላሊት ህመም ምልክቶች ምንድን ናቸው?
በስኳር ህመምተኞች ላይ የሚታየው የመጀመሪያው ኩላሊት ህመም ምልክት፣ በሽንት ውስጥ አልቡሚን የሚባለው የፕሮቲን መጠን መጨመር ነው። ይህ ምልክት የግል ሃኪምዎ የኩላሊትን ጤንነት ከመመርመሩ ረጅም ጊዜ በፊት የሚታይ ምልክት ስለሆነ ይህን ምርመራ ቢያንስ በአመት አንዴ ማድረግ ይመከራል።
ክብደት መጨመር፣ የእግር ማበጥ፣ ከወትሮው በተለየ ለሊት ላይ ለሽንት መነሳት፣ የደም ግፊት መጨመር በተያያዥነት ሊታዩ የሚችሉ የኩላሊት ህመም ምልክቶች ናቸው።
በተወሰኑ ወራት አንዴ የደም ግፊት እንዲሁም የደምና የሽንት ምርመራ ማድረግ ችግሩ ሳይከሰት ቶሎ ለመከላከል ይረዳል።
የስኳር ህመምተኞች ላይ በሂደት (በስተመጨረሻ) የሚታዩ የኩላሊት ህመም ምልክቶች ምንድን ናቸው?
ኩላሊቶች በሚደክሙበት ጊዜ በደም ውስጥ የሚገኘው ዩሪያ ናይትሮጅን [Blood Urea Nitrogen] እና ክሪያቲኒን የሚባሉት ኬሚካሎች ይከማቻሉ። በዚህም ምክንያት ማቅለሽለሽ፣ ማስመለስ፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ ከፍተኛ የድካም ስሜት፣ የሰውነት ማሳከክ፣ የጡንቻ ህመም (በተለይ እግሮች ላይ) እና የ ደም ማነስ። የኩላሊቶች የመስራት አቅም እየተመናመነ በሚሄድበት ጊዜ ሰውነታችን የሚጠቀመው የኢንሱሊን መጠን እያነሰ ይሄዳል። ይህም የሚሆነው ኩላሊታችን ኢንሱሊንን በተገቢው መልኩ ማጣራት ስለማይችል ነው።
በስኳር ህመምተኞች ላይ የሚታዩ የኩላሊት ህመም ምልክቶች | |
1 | በሽንት ውስጥ የሚታይ ፕሮቲን (አልቡሚን) |
2 | ከፍተኛ የደም ግፊት |
3 | የእግር ማበጥ |
4 | ለሊት በተደጋጋሚ ለሽንት ከእንቅልፍ መነሳት |
5 | በደም ውስጥ ከፍተኛ የክሪያቲኒን መጠን |
6 | ከበቂ በታች የስኳር መድሃኒቶች ማስፈለግ |
7 | የጠዋት ማቅለሽለሽ |
8 | ድካም፣ የደም ማነስ፣ መገርጣት |
9 | ማሳከክ |
ኩላሊቶች ቢጎዱ ምን ይፈጠራል?
በመጀመሪያ የኩላሊቶቹ ችግር በስኳሩ ምክንያት የመጣ መሆኑን ሃኪሞት ማረጋገጥ ይኖርበታል ይህም ምክንያቱ የኩላሊት ችግር በሌሎች በሽታዎች ምክንያት ሊመጣ ስለሚችል ነው።
የኩላሊቶቻችንን ጤንነት ለመጠበቅ ማድረግ የሚገቡን ነገሮች
- የደማችንን የስኳር መጠን ማስተካከል
- ከፍተኛ የደም ግፊትን መቆጣጠር
- የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽንን በጊዜ መታከም
- ከሽንት ጋር የተያያዙ ችግሮችን መቅረፍ
- ኩላሊትን ሊጎዱ የሚችሉ መድሃኒቶችን (በተለይም የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶችን) በብዛት አለመጠቀም
የኩላሊቶችን ጤንነት ለረጅም ጊዜ ጠብቆ ማቆየት
የኩላሊት ህመም ስፔሻሊስት (ኔፍሮሎጂስት) የህክምና ዘዴዎችን በግልጽ መልኩ ለህመምተኛው እንዲሁም ለቤተሰቡ ይገልጻል። ለኩላሊት ጤንነት አስተዋጾ ከሚያደርጉ ነገሮች ዋንኞቹ ከፍተኛ የደም ግፊትን መከላከል ሲሆን ሌላኛው ደሞ ለኩላሊት ጤንነት የተመረጠ አመጋገብን መከተል ነው። ከዕለት ተዕለት ምግባችን ውስጥ የ ፕሮቲንን መጠን መቀነስ ሊኖርብን ይችላል ።
ከነዚህ በተጨማሪ የኩላሊቶችን ጉዳት ለመቀነስ በሃኪም ACE Inhibitors/ARB የሚባሉ መድሃኒቶችን ሀኪምዎ ሊያዝልዎት ይችላል።
በቅርብ የወጡ ጥናቶች ደግሞ ኤስጂ ኤል 2 (SGLT2I) የሚባሉ መድኃኒቶች የስኳር መድኃኒቶች የኩላሊት ህመም እንዳይባባስ እንደሚረዱ ያሳያሉ። ለእርስዎ ጠቃሚ እንደሆነ ለማወቅ ሀኪምዎን ያማክሩ ።
በስኳር ህመምተኞች ላይ የሚከሰት የመጨረሻ ደረጃ የኩላሊት መድከም
ይህ የሚከሰተው የኩላሊቶች ጉዳት መመለስ ከሚቻልበት አቅም በላይ ሲሆን ነው። ይህም ማለት የኩላሊቶች የመስራት አቅም ከ 10 እስከ 15 ፐርሰንት ሲሆን ነው።
በዚህም ጊዜ በማሽን ኩላሊትን የማጣራት ተግባር (ዳያሊሲስ) አልያም የኩላሊት ንቅለ ተከላ ያስፈልጋል።
የስኳር ህመምተኛ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ማድረግ ይችላል?
በሚገባ። ከቀዶ ጥገናው በኋላ ግለሰቡ የሚጠቀመውን የኢንሱሊን መጠን መጨመር ሊያስፈልግ ይችላል።ከንቅለተከላው በኋላ የህመምተኛው የምግብ ፍላጎት ይስተካከላል። የግለሰቡ ሰውነትም አዲሱን ኩላሊት እንዲቀበለው የሚረዱ ስቴሮይድ የሚባሉ መድሃኒቶችን መውሰድ ሊያስፈልግ ይችላል።
የስኳር ህመምተኞች ህይወታቸውን በጤናማ መልክ እንዴት ማስቀጠል ይችላሉ?
- በቤት ውስጥ የደም የስኳር መጠንን መለካት
- ስለ ደም ግፊት ትልቅ ግንዛቤን ማዳበር፣ ከተቻለም ቤት ውስጥ የደም ግፊትን መለካት
- የአመጋገብ ስርአትን ማስተካከል