Written by Dr. Samrawit Wondwossen (Medical intern at Myungsung Medical College)
Reviewer: Dr. Nafkot Girum (Assistant professor of Dermatovenereology)
የሥጋ ደዌ ምንድን ነው?
የሥጋ ደዌ በሽታ “ማይኮባክቲሪየም ሌፕራ” በተባለ ባክቴሪያ የሚመጣ ኢንፌክሽን ነው ::
በሽታው ነርቮችን፣ ቆዳን፣እና አይንን ሊጎዳ ይችላል :: ይህ በሽታ የተጎዱ አካባቢዎችን “የመነካት፣ ሙቀት እና ቅዝቃዜ የመለየት እና የህመም” ስሜት እንዳይሰማቸው የሚያደርግ ሲሆን፤ እስከ መቆረጥ ወይም የመቃጠል አይነት ጉዳቶች ሊያምራ ይችላል ::
ባክቴሪያው ነርቮችን ሲያጠቃ ከቆዳው በታች ማበጥን፣ የቆዳ ነጣ ማለትን እና የነርቭ እብጠትን ሊያስክትል ይችላል :: ነርቮቹ ህክምና ካልተደረገላቸው ሰውነታችን የተጎዱትን ጣቶች በመሟጠጥ የእግር፣ ወይም የእጅ ጣቶችን ማጣት አልያም ሽባነትን ሊያስከትል ይችላል :: የፊት ነርቮች ከተጎዱ ደግሞ ዓይነ ስውርነት ሊያስክትል ይችላል ::
ሰዎች እንዴት በሥጋ ደዌ ይያዛሉ እንዴትስ ይተላለፋል?
- በበሽታው ለመያዝ ለብዙ ወራት ካልታከመ የሥጋ ደዌ ታማሚ ጋር ረጅም የቅርብ ግንኙነት መኖር ያስፈልጋል::
- የሥጋ ደዌ ካለበት ሰው ጋር በአጋጣሚ በመገናኘት የሥጋ ደዌ በሽታ አይተላለፍም::
- እጅ ለእጅ በመጨባበጥ ፣ በመተቃቀፍ ፣ አውቶቡስ ላይ አጠገብ ለአጠገብ በመቀመጥ ወይም ምግብ አብረው በመብላት አይተላለፍም::
- በጾታዊ ግንኙነት አይተላለፍም::
- በተጨማሪም በእርግዝና ወቅት ከእናት ወደ ፅንስ ልጇ የመተላለፍ እድሉ ዝቅተኛ ነው::
ምልክቶች
ምልክቶቹ በዋናነት በቆዳ፣ በነርቭ እና በሰውነት ላይ የሚገኙ ክፍት ቦታዎች ውስጥ ለስላሳ እና እርጥብ ቦታዎች (mucous membrane) ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ::
የቆዳ ምልክቶች
- በቆዳ ላይ ነጣ ነጣ ያሉ ስሜት አልባ ምልክቶች( በመቀመጫ እና ቀዝቃዛማ የቆዳችን አካባቢዎች ላይ)
- በቆዳ ስር ላይ እብጠቶች
- ህመም የሌላቸው ቁስሎች
- ህመም የሌለው እብጠት (ፊት ወይም ጆሮ ላይ)
- የቅንድብ መጥፋት
በነርቮች ላይ በሚደርስ ጉዳት ምክንያት የሚመጡ ምልክቶች
- የተጎዱ የቆዳ አካባቢዎች ስሜት አልባ መሆን
- የጡንቻ ድክመት ወይም ሽባነት
- ዓይነ ስውርነት (የፊት ነርቮች ሲጎዱ)
በሽታው እንዴት ነው የሚታወቀው?
- ከተለመደው ቆዳ ነጣ ያሉ ንጣፎች በመኖር
- ከቀዘቃዛማ የቆዳችን ክፍሎች ወይም ከእባጮች የሚወሰድ ምርመራ (slit skin smear)
በሽታው እንዴት ይታከማል?
- በተመሳሳይ ጊዜ በሚያገለግሉ 3 የአንቲባዮቲኮች ጥምረት ይታከማል::
- ሕክምናው ብዙውን ጊዜ ከ6 ወር እስከ 1 ዓመት ይቆያል::
- ህክምናው በታዘዘው መሰረት ከተጠናቀቀ ህመሙ የመዳን እድሉ ክፍተኛ ነው::
References
- https://www.who.int/news-room/fact-sheets/detail/leprosy
- https://www.cdc.gov/leprosy/index.html
- uptodate.com/contents/leprosy-epidemiology-microbiology-clinical-manifestations-and-diagnosis
- https://www.uptodate.com/contents/leprosy-treatment-and-prevention