የጤና ወግ ፍኖተ ካርታ

ኮሮና ቫይረስ ስርጭትን በኢትዮጲያ ውስጥ ለመግታት ምናልባት ኢትዮጵያ ከቻይና እና ከደቡብ ኮሪያ በበለጠ ብዙ ልትማር የምትችለው የቬይትናምን ምሳሌ በመውሰድ ነው።

የኮሮና ቫይረስ በሃገራችን መስፋፋቱን ለመገደብና ለመቆጣጠር ኢትዮጵያ በመንግስት ደረጃ ግብረ ኃይል አቋቁማ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራች ትገኛለቸ። የጤና ወግ እነዚህን ጥረቶች ለማገዝ ህዝብና መንግስት ምን ማድረግ እንዳለባቸው በዚህ ጽሁፍ ትዳስሳለች። ይህን ጽሁፍ ሃሳብ ኒው ዮርክ ታይምስ ከዘገበው አስተማሪ ጽሁፍ ወስደን የሃገራችንን ሁኔታ ጋር በማገናዘብ ለኢትዮጵያ በሚሆን ሁኔታ እንዲህ አቅርበነዋል። 

እነ ቻይናና ደቡብ ኮርያ የቫይረሱን መስፋፋት ለግዜው መቆጣጠር ችለዋል። ምን የተለየ ነገር አረጉ? ሃገራችን ከነሱ ምን ትማራለች?

በእርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ እስከአሁን የተረጋገጡት 12 ታማሚዎች ብቻ ናቸው፤ ለዚህ ምክንያቱ የቫይረሱ ምርመራ (test) በበቂ ሁኔታ ስላልተካሄደ እንደሆነ መገመት ይቻላል። የጤና ባለሞያዎቹ በይበልጥ እየመረመሩ በሄዱ ቁጥር መጠኑ ከፍ ማለቱ አይቀርም። ብዙ ነገር ልንሰራባቸው የምንችለውን ውድ ጊዜያቶች ውሳኔ ቶሎ ካለመስጠት አባክነን ሊሆን ይችላል። አሁንም የነቻይናን ስኬት ለመድገም መንግስት ከፍተኛ ቅንጅትና በጀት መድቦ መንቀሳቀስ አለበት፤ በዚህ ረገድ መንግስት ቀደም ብሎ  ያስቀመጠው በጀት በጣም ጥሩና የሚበረታታ ነው። ከዚ በተጨማሪና በጣም አስፈላጊው ነገር ህዝብ የመንግስትን መመሪያ መከተልና ማክበር አለበት።

ምናልባት ኢትዮጵያ ከ ቻይና እና ከ ደቡብ ኮሪያ በበለጠ  ብዙ ልትማር የምትችለው የ ቬይትናምን ምሳሌ በመውሰድ ነው።

ቬይትናም ከ ቻይና ጎረቤት ሀገር ናት ፣ የኮሮና ቫይረስ ቀድሞ ከተገኘባቸው ሃገራት አንዷ ነች ። እንደ ቻይና እና ደቡብ ኮሪያ ብዙ የኢኮኖሚ አቅም የላትም ። ብዙ ሰዎችን ለመመርምር በቂ የሆነ Test kit የላትም። ሆኖም ገና የመጀመሪያዎቹ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ህመምተኞች እንደተገኙ ከፍተኛ የሆነ የተቀናጀ ሥራ በመስራታቸው የበሽታውን መስፋፋት ለመግታት ችለዋል። ይሄ ደግሞ ከብዙ ቦታ በተለይም ከ ዓለም ጤና ጥበቃ አድናቆት ተችሮዓቸዋል። ትምህርት ቤቶችን አስቀድሞ በመዝጋት፣ሰው ከቤት እንዳይወጣ ወታደር ጭምር በማሰማራት ተግብረዋል። በሽታው የተገኘባቸውን ሰዎች አስቀድሞ በማግለል አና ከነሱ ጋር የተገናኙትን በሙሉ አፈላልጎ በመለየት የተማሚዎች ቁጥር ከፍ እንዳይል አርገዋል። እኛ ብዙ ሰው እንደ ደቡብ ኮሪያ መመርመር አቅም አይኖረንም፣ ያሉንን የመከላከል አማራጮች ግን በከፍተኛ ሁኔታ መጠቀም እና መንግስትም ይሄንን በማስገደድ ጭምር ማስፈፀም ሊኖርበት ይገባል። 

ምን ምን አማራጮች አሉ የሚለውን;  ሰሞኑን ኔው ዮርክ ታይምስ በዘገባው ያናገራቸው ባለሞያዎች የሰጡትን ምክር ወስደን በኛ አገር ሁኔታ ምን መሆን አለበት የሚለውን አስቀምጠናል። 

1 ተመራማሪዎችና የጤና ባለሞያዎችን መስማት።

በዚህ ጊዜ ከፖለቲከኞች ይልቅ የጤና ባለሞያዎች መድረኩን መያዝ አለባቸው፤ በተደጋጋሚ በሚድያው እነሱን ማቅረብና ግንዛቤ ማስጨበጥ። 

2 በከተሞች መካከል ያለውን እንቅስቃሴ በእጅጉ መቀነስ።

 እጅግ አስፈላጊ ከሆኑ እንቅስቃሴዎች ውጨ መንግስት ሌሎች እንቅስቃሴዎችን መገደብ አለበት። የትኛውም አይነት እንቅስቃሴ በተቻለ መጠን ማቆም። የጣልያንና የቻይና ልዩነት ይሄ ነበር ቻይና ወድያውኑ እንቅስቃሴዎችን ስትገድብ ጣልያን ቀስ በቀስ ነበር ያደረገችው። የቀናት ልዩነት የብዙዎችን ህይወት ከቫይረሱ ይታደጋል።

3 ምርመራውን በመውሰድ በተቀናጀ ሁኔታ ማድረግ

ከምንም በላይ በተቻለ መጠን ምርመራዎችን ማፋጠን በሃገር ደረጃ የት እንዳለን ፣ከዚህ በማስከተል ምን ማረግ እንዳለብን እንድንረዳ ይጠቅመናል፤ ያለንበትን ሳናውቅ የወደፊት እቅዳችንን ማወቅና መተግበር ይቸግራል። 

4 ታማሚዎችን ከሌሎች ጋር እንዳይቀላቀሉ ለብቻ መለየት።  

እስካሁን እንዳየነው የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ለየት የሚያደርገው ብዙ ጊዜ በ ተወሰኑ ቡድኖች ውስጥ መታየቱ ነው።ወይ ቤተሰብ ውስጥ ፣ ወይ አንድ ስራ ቦታ፣ ወይ ቤተ ክርስትያን ውስጥ እንደ cluster ይታያል። በቻይና ከ75-80% የሚሆኑት ታማሚዎች በቤተሰቦች ውስጥ ነው የተገኘው።ያ ደግሞ ጥሩ ክትትል ከተደረገበት ባለበት አፍኖ ለመያዝ የተወሰነ ዕድል ይሰጣል። ለዛም ነው መንግስትን ከፍተኛ ቁርጠኝነት ወስዶ እንቅስቃሴዎችን እንዲገድብ የምንጠይቀው።  አብዛኛው ታማሚዎች የከፋ ምልክት ባያሳዩም ወደ ሌሎች ማስተላለፋቸው አይቀርም። ታማሚዎችን ማግለልና ለብቻው የተዘጋጀ ቦታ ማስቀመጥ ገና ካሁኑ ትልቅ ስራ ይጠይቃል። በቻይና ዉሃን ጊዜአዊ ሆስፒታሎች ተሰርተው ነበር፤ ለሃገራችን ይሄ ከባድ ነው፤ ቢሆንም ታማሚዎችን ሳያገሉ በሽታውን ማቆም ስለማይቻል መንግስት አቅምን ያገናዘበ መፍትሄ ካሁኑ መፈለግ አለበት። ያልተላለፉ ኮንዶምንየሞች፣ የዩኒቨርሲቲ ዶርምተሪዎች ፣የተለያዩ የመንግስት ህንፃዎች ለዚህ የመለያ እና የማግለያ ማዕከልነት ሊያገለግሉ ይችላሉ።

5 ትኩሳት እና ሌሎች ምልክትዎችን ቶሎ የመለየት ስራ በየቦታው በፍጥነት እና በተቀናጀ ሁኔታ ማድረግ 

ይሄ ቫይረሱ ያለባቸውን ለማወቅ ስለሚያግዝ ትኩሳቶችን መለካት በተለያየ ቦታ ያስፈልጋል። 

6 ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች የተገናኙዋቸውን ሰዎች ሁሉ በቅርብ መከታተል። 

ቫይረሱ ያተገኘባቸው ሰዎች ሳያውቁት ከብዙ ሰው ጋር ይገናኛሉ፤ እነዚህን ሰዎች በተራቸው ለሌሎች ሊያስተላልፉ ስለሚችሉ ፈልጎ ማግኘትና የጤናቸውን ሁኔታ በቅርብ መከታተል ያስፈልጋል። የጤና ጥበቃ ሚኒስትር እስካሁን ከሁለት መቶ ሰዎች በላይ ክትትል እያረግ እንደሆነ ተናግሯል። ይሄ ቁጥር የታማሚዎች ቁጥር ሲጨምር ስለሚጨምር ገና ካሁኑ ዝግጅት ይፈልጋል።

7    መንግስት መሰረታዊ አገልግሎቶች እንዳይቋረጡ አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ አለበት።

ባሁን ሰአት ትምህርትና አንዳንድ አገልግሎቶች ተቋርጠዋል። ነገር ግን ከህክምና አገልግሎት በተጨማሪ መሰረታዊ አገልግሎቶች ለምሳሌ ውሃና መብራት የምግብ አገልግሎት ፋርማሲዎች በአግባቡ እንዲሰሩ ሰራተኞችም ለቫይረሱ እንዳይጋለጡ አስፈላጊ ነገር ሁሉ መደረግ አለበት። መንግስት በየክልሉ ዜጎች ህግን እንዲከተሉ አገልግሎቶች በአግባቡ እንደሚሰሩ ለማረጋገጥ እስከ ቀበሌ ደረስ ያለውን መዋቅሩን እንዲሁም የፖሊስና የፌደራል ሃይሉን መጠቀም አለበት።

8. ቬንትሌተርና የመተንፈሻ ኦክስጅኖችን በተቻለ ፍጥነት መግዛት

የቫይረሱን መመርመሪያዎችና የተለያዩ ለህክምና ተቃሚ መሳሪያዎች በእርዳታ ከቻይናዊው ቢልየነር ጃክ ማ ወደ ሃገራችን ገብቷል። አሁንም ከ አለም ጤና ድርጅት ጋር በመተባበር ቬንትሌተሮችና ኦክስጅን የሚገቡበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል። ባለሀብቶች ለዚህ ጥረት ድጋፍ ቢያደርጉ ችግሩን ማቃለል ይቻላል።ከዛም ባለፈ የመተንፈሻ ማሽን ላይ የመስራት ልምድ ያላቸው ሀኪሞች እይረት ስለሚኖር ጤና ጥበቃ ይሄንን ክፍተት ለመሙላት አስቸካይ ስልጠናዎችን ጊዜው ሳይረፍድ ቢያዘጋጅ ይመረጣል።

9. አዳዲስ ህክምና መስጫ ቦታዎችን ማዘጋጀት

ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ቻይና በፍጥነት ሆስፒታሎችን መስራት አይቻልም፤ ቢሆንም ይሄንን ክፍተት ለመሙላት መንግስት ካሁኑ አማራጮችን ማመቻቸት አለበት። ከዚህም አንጻር ቅድም ከላይ እንደጠቀስነው ለምሳሌ አዳዲስ ሰው ያልገቡባቸውን ኮንዶሚኒየም ቤቶችን ወይም ከፍተኛ ትምህርት ቤቶችን እንደአማራጭ ተጠቅሞ  እና አስፈላጊውን ዕቃ በማማላት ካሁኑ መዘጋጀት አለበት። የከተማ ከንቲባዎች የ ክልል ፕሬዝዳንቶች ካሁኑ መዘጋጀት አለባቸው። 

10 በጎ ፈቃደኞችን መመልመል።

ለቻይና ስኬት አንደኛው ምክንያት በጎ ፈቃደኞችን መመልመሏ ነበር። በኢትዮጵያ ይሄ አይከብድም፤ ገና ካሁኑ የተለያዩ በጎ ፈቃደኞች ይህንን እያረጉ ስለሆነ እነዚህንና ሌሎችን ሰብስቦ በተለያየ ስራ ላይ ማቀናጀት ያስፈልጋል።

11 እንደታማሚው ሁኔታ ለሚሰጡትን መድሃኒቶችና የህክምና አይነቶች ቅድሚያ መስጠት። 

በአለም ላይ አዳዲስ እየተሞከሩ ያሉ መድሃኒቶችን እየተከታተሉ እንደታማሚው የህመም ሁኔታና በባለሞያ ምክር የሙከራ ሂደቶች ማድረግ። በባለሞያ የተደገፉ በሌሎች ሃገራት ያሉ የህክምናና ተስፋ ሰጪ መድሃኒቶችን ውጤት መከታተልና ወደ ሕክምና ፕሮቶኮላችን ማካተት ያስፈልጋል። 

12 ከጎረቤት አገሮች እንዲሁም ከተቀረው የአለማችን ክፍል ጋር በዚህ ጊዜ ተቀራርቦ መስራት።

ይህ በጣም አስፈላጊ ነው ነገር ግን ተቀራርቦ መስራት ከቤት ይጀምራል። በተለይ በሃገራችን ውስጥ ያሉትን የተለያየ የፖለቲካ እምነት ያላቸው ሰዎች ተቀራርበው የሚሰሩበት ጊዜ ነው። ይህን ጊዜ ካመጣብንን ከባድ ፈተና ወደ በረከት መለወጥ ይቻላል። የፖለቲካ ልዩነታችንን ትተን ተቀራርበን የምንሰራበት ጊዜ መሆን አለበት።

13 የሃይማኖት ተቋማትና አባቶች ሚና 

የሃይማኖት ተቋማት ከመቼውም ጊዜ ባላይ ህዝባቸውን መምከር አለባቸው። በሃይማኖት ቦታዎች ያለውን መሰብሰብ ለማስቆም የጸና አቋም ድፍረትና ማስተዋል ይጠበቅባቸዋል። ከመንግስት ጋር በጋራ በመስራት የጤና ባለሞያዎች የሚሉትን ሁሉ ተከታዮቻቸው ሳያዛንፉ እንዲተገብሩ መምከርና መገሰጽ አለባቸው። መንግስት ይሄን በማይሰሙት ላይ ጉዳዩ የህዝብ ጤንነት መሆኑን ተገንዝቦ አስፈላጊውን ውሳኔ ማድረግ አለበት።

14 በዋነኛነት መንግስት እያካሄዳቸውን ያለውንም ሆነ ሊያካሂዳቸው ያሰባቸውን ስብሰባዎች ማቋረጥ አለበት።

ይሄን በማድረጉ ሌሎችም ቫይረሱን እና ባጠቃላይ የችግሩን አሳሳቢነት እንዲረዱና ፈለግ እንዲከተሉ ያደርጋቸዋል። ባለስልጣናት እስከታችኛው የስልጣን ተዋረድ ድረስ ይህንን ማስተግበር መቻል አለባቸው። 

15 ሚድያዎች በተደጋጋሚ ቫይረሱን እንዴት መከላከል እንደሚቻል ህዝቡን ማስተማር አለባቸው፤

በተለይ አካላዊ መራራቅን ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጡት ይገባል። ለአይና ለጆሮ በሚማርክና በማይሰለች ሁኔታ ሁሌም ማስተማር አለባቸው። ትእዛዛና ምክር የሚተላለፉትን የመንግስት አባላትም ሆነ ህዝብ በሚድያ ሽፋን በመስጠት ሂስ መስጠት፣ ተጠያቂነት እንዲኖር ማድረግ ብዙ ስራ ይጠብቃቸዋል።

ይህንን ቫይረስ ለመከላከልና ለማሸነፍ ሁላችንም አቅማችንን ሁሉ አሟጠን መጠቀም አለብን።

Yetena weg