ዶ/ር ትንሳኤ አለማየሁ ; የህፃናት ህክምና ስፔሻሊስት እና የህፃናት ተላላፊ በሽታዎች ህክምና ሰብ-ስፔሻሊስት 

የ COVID19 ወረርሽኝ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ የእድሜ እና የጾታ ልዩነት ሳይከተል በሁሉም ሀገራት ያሉ ነዋሪዎችን እያጠቃ ነው፡፡ እድሜያቸው ከ18 አመት በታች ያሉ ህፃናት እና ታዳጊዎች ከአለም ህዝብ 29.3% ድርሻ ይይዛሉ፡፡ ስለዚህም በሚከተለው ጽሁፍ ህብረተሰባችን በዚህ እድሜ ክልል ስለሚከሰተው የCOVID19 ህመም ሊያነሳ የሚችላቸውን ጥያቄዎች በመረጃ አስደግፌ ለመመለስ እሞክራለሁ፡፡ ከአራስነት እድሜ ክልል ተነስተን በእድሜ ከፍ ወዳሉት ልጆች ደረጃ በደረጃ እንመለከታለን፡፡

  1. የCOVID19 ህመም ከእናት ወደ ጽንስ ሊተላለፍ ይችላል?

ባሁኑ ሰአት የCOVID19 ታማሚዎች ቁጥር በመቶ ሺዎች ቁጥር ቢደርስም፣ ለመውለድ የተቃረቡ እናቶች ላይ ተከስቶ ወደ ጽንስ  ህመሙ ተላለፈ ወይስ አልተላለፈም የሚለው ጥያቄ የተመለሰው በ10 ቻይናውያን እናቶች ብቻ ነው፡፡ ይህ ቁጥር ባለሙያዎችም እናቶችም ለሚጠይቁት ጽንስ ይጎዳል ወይ ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመሆን እጅግ አነሳ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ከላይ ባነሳኃቸው 10 ቻይናውያን እናቶች የCOVID19 ህመም አምጪ ቫይረስ (SARS-Cov-2) ልጆቹ በተወለዱ ሰአት አልታየባቸውም፡፡ ይህንን ጥያቄ በበቂ ለመመለስ ተጨማሪ ጥናቶች እየተደረጉ ነው፡፡ ስለጉዳዩ ተጨማሪ ንባብ ለማድረግ የሚከተሉትን ሊንኮች ተጫኑ፡፡ ተጨማሪ መረጃ 1ተጨማሪ መረጃ 2       

  1. የህፃናት COVID19 ከአዋቂዎች የCOVID19 ህመም የተለየ ምልክቶች አሉት?

የህመም ምልክቶች በሁሉም እድሜ ክልል ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ከሁሉም አብዝተው የሚታዩት ትኩሳት (በ88% የሚሆኑት ታማሚዎች)፣ ሳል (በ68% የሚሆኑት ታማሚዎች) እና ድካም (በ38% የሚሆኑት ታማሚዎች) ናቸው፡፡ ሌሎች በጥናቶች ውስጥ በብዛት ያልታዩ ምልክቶች አክታ ማስወጣት (እድሜያቸው ትንሽ የሆኑ ህፃናት ማድረግ የማይችሉት)፣ የትንፋሽ መቆራረጥ፣ መቆረጣጠም (እድሜያቸው ትንሽ የሆኑ ህፃናት መግለጽ የሚያቅታቸው)፣ የጉሮሮ ህመም እና ራስ ምታት (እድሜያቸው ትንሽ የሆኑ ህፃናት መግለጽ የሚያቅታቸው)፣ ብርድ ብርድ የማለት እና ማቅለሽለሽ/ማስታወክ ናቸው፡፡

  1. የCOVID19 ህመም ህፃናትን አይዝም ይባላል፡፡ ምን ያህል እውነትነት አለው?

አንድ የCOVID19 ታማሚ የተለያዩ እድሜ ላይ ያሉ በህመሙ ያልተያዙ ሰዎች መሀል ቢኖር የበሽታ የመያዝ እድላቸው ለሁሉም እድሜ ክልሎች ተመሳሳይ ነው ፡፡ መተላለፍያውም በትንፋሽ እና በንክኪ ነው፡፡ ነገር ግን የህመሙ ምልክቶች ህፃናት እና ታዳጊዎች ላይ በአብዛኛው ከአዋቂዎች ሲነፃፀር የቀለሉ ናቸው፡፡ እስካሁን ካሉ ጥናቶች ውስጥ ይህንን በተሻለ መልኩ የሚገልፀው በዚህ ሊንክ የሚገኘው እና ቻይና በመዘገበቻቸውን የመጀመርያ 72,000 ታካሚዎች ላይ የተመሰረተው ነው ፡፡ ከነዚህ 72,000 ታካሚዎች እድሜያቸው 18 አመት እና ከዛ በታች የሆኑት 965 ሲሆኑ ከመሀላቸውም አንድ ሞት ብቻ ተመዝግቧል፡፡ በአብዛኛው የሚለውን ግን ልብ እንበል፡፡ ምክንያቱም እንደአዋቂዎች ቶሎ ቶሎ ባይሆንም በፀና የሚታመምም፣ የሚሞትም ልጅ ሊታይ ይችላል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን እድሜያቸው ከ18 – 35 አመት የሆኑ ወጣቶችን ከአዛውንቶች ጋር እያነፃፀሩ እስካሁን የተሰሩ የምርምር ጥናቶች በብዛት የሉም፡፡ ከአሜሪካ የሚወጡ ቁጥራዊ መረጃዎች ግን (በምርምር ጥናት ሳይሆን) ከ18 – 35 አመት የሆኑ ወጣት ታማሚዎች ልክ እንደ አዛውንቶች ሁሉ ቁጥራቸው የበዛ መሆኑን ያሳያሉ፡፡

  1. ስለ COVID19 ህመም ለህፃናት እንዴት ማስረዳት ይቻላል?

እስካሁን እንደሰማነው እጃችንን በውሀ እና በሳሙና 40 ሰከንዶች እና ከዛ በላይ ለሆነ ጊዜ በትክክለኛው ቴክኒክ በመጠቀም ማጽዳት እና ማህበረሰባዊ መራራቅን (Social distancing) በመከተል መከላከል ይቻላል፡፡ ታማሚዎችም በሚያስሉ ሰአት አፍና አፍንጫቸውን መሸፈን፣ መስኮት በመክፈት አየርን ማዘዋወር ተጨማሪ መንገዶች ናቸው፡፡ 

አስቡት፣ ከላይ የገለጽኩትን መልእክት ለህፃናት መግለጽ እንዴት አዳጋች እንደሆነ፡፡ ወቅቱ ለአዋቂዎችም መልእክቱን ማድረስ ያልተቻለበት ነው፡፡

ለህፃናት ማስተላለፍ የምንፈልገውን መልእክት በስእላዊ መግለጫ እና በመዝሙሮች በመጠቀም ማስረዳት እንችላለን፡፡ የሚከተሉት ስእሎች ለዚህ ምሳሌዎች ናቸው (“ኮሮና ቫይረስ እባላለሁ፡፡ የጉንፋን አምጪ ቫይረሶች ዘመድ ነኝ፡፡ ከሰው ሰው መዝለል እወዳለሁ፡፡ ወደ እናንተ ስመጣ ትከሳት እና ሳል ይዤ እመጣለሁ፡፡ እጃችሁን በውሀ እና ሳሙና በደንብ በመታጠብ ወደ እናንተ እንዳልመጣ ማድረግ ትችላላችሁ”)፡፡  

ከስር በ ቪዲዮ የምናየው በ ሳምራዊት ለማ የተዘጋጀው ማስተማሪያ ለ ለልጆች የኮሮና ቫይረስን መተላለፊያ መንገዶችን ለማስረዳት እና እንዴት እራሳቸውን ከበሽታ እንደሚጠብቁ ያሰረዳል።

https://youtu.be/7sHQe0kyuq0
  • የCOVID19 ህመም እናት ወደ አራስ ህፃናት እናዳይተላለፍ ምን ማድረግ እንችላለን?

በኢትዮጵያውያን ባህል አንዲት እናት በምትወልድ ሰአት በተለይ የመጀመርያዎቹ 2 ወራት ላይ ብዙ ጠያቂዎች ቤቷ ይመላለሳሉ፡፡ ስለዚህም በዚህ ወቅት አራስ ህፃናት የCOVID19 ህመም እና ሌሎችም የመተንፈሻ አካላት ህመሞች ካለው ጠያቂ ህመም እንዳይጋባባቸው ሁለት ዋና መንገዶችን መጠቀም ይቻላል፡፡ 1ኛ፡ ጠያቂዎች በርቀት እንዲቀመጡ ማድረግ፡፡ የአለም የጤና ድርጅት የCOVID19 ህመም እንዳይተላለፍ የአንድ ሜትር ርቀትን ሲጠቁም የአሜሪካው የበሽታ መከላከያ እና ቁጥጥር ተቋም ሁለት ሜትሮችን ይጠቁማል፡፡ በተለይም አራስ ህፃናት ወደተኙበት ክፍል ውስጥ ከናካቴው ጠያቂዎች እንዳይገቡ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ 2ኛ፡ እናቶች እና አራስ ህፃናት የሚተኙበትን ክፍሎች በቂ የአየር ዝውውር እንዲያገኝ ማድረግ፡፡

ባለንበት ራሳችንን እንጠብቅ፡፡

የጤና ወግ

በመረጃ የተመሰረተ ሕክምና ብቻ ።  

………………………………………………………………………………………………………………………..

ይህ የጤና ወግ ድረ ገፅ ነው።
ስለ ጤንነታችሁ ማወቅ የምትፈልጉትን መረጃ የምታገኙበት ፣ በህክምና ባለሙያዎች የሚዘጋጅ የመረጃ ምንጭ ነው።
ሁልግዜም ከሀኪማችሁ ተማከሩ፣ ተጨማሪ መረጃ ከፈለጋችሁ የኛን ድረ ገፅ ጎብኙ።

በጥናት የተደገፈ መረጃ ብቻ እናቀርባለን።

የህክምና ባለሙያዎች ለህሙማኖቻችሁ የሚሆን የሚነበብ መረጃ ከፈለጋችሁ ይህን ግፅ ጠቁሟቸው። ህሙማኖቻችሁ እንዲያውቁት የምትፈልጉትን ነገር መረጃ ጠቅሳችሁ ፃፉልን፣ ስምችሁን ጠቅሰን እናወጣለን። የህክምና ተማሪዎች እንዲጽፉ እናበረታታለን።

በተጨማሪም በጤና ወግ ፖድካስት፣  በ ዩትዩብ ፣በ ትዊተር ፣ በ ፌስቡክ ፣ በቴሌግራም የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ገፆቻችን ታገኙናላችሁ ።