በ ዶ/ር ፍፁም ጥላሁን (MD )

በዚህ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጊዜ Herd Immunity ከበሽታ ሊጠብቀን አይችልም። መኖሩንም ማወቅ አንችልም። የተነገሩንን የመከላከል እርምጃዎች እንከተል።

Herd Immunity ማለት በአንድ ማህበረሰብ ያሉ ሰዎች ውስጥ ለ አንድ ተላላፊ በሽታ ምን ያህሉ በሽታውን የመከላከል አቅም አላቸው የሚለውን ነው የሚነግረን። ሰዎች ይሄን የመከላከል አቅም ወይ ታመው ከበሽታው ሲያገግሙ ያገኙታል ወይም በ ሕብረተሰብ ጤና የሚመረጠው ደግም ማህበረሰብ አቀፍ በሆነ የክትባት  ዘመቻ ሁልኑም ወይም አብዛኛውን ሕብረተሰብ ማዳረስ ሲቻል ነው። 

Herd Effect የምንለው ደግሞ በ ማህበረሰብ ውስጥ ከፍ ያለ የ Herd Immunity በመኖሩ የ አንድ በሽታ ከ አንዱ ሰው ወደ ሌላ ሰው የመተላለፍ እድሉ ሲቀንስ ነው።  ምን ያህሉ ሰው ለ አንድ በሽታ የመከላከል አቅም ሲኖረው ነው ይሄን Herd Effect የምናየው የሚለው የሚወሰነው በሽታው ምን ያህል ተላላፊ ነው በሚለው ነው።  

ለምሳሌ ኩፍኝን (Measeles )ብንወስድ- ኩፍኝ በጣም ተላልፊ  በሽታ ነው። አንድ የታመመ ሰው ከ 12-18 ሌሎች ሰዎችን በበሽታ ሊያሲዝ ይችላል። ያን ቁጥር የመባዛት መጠን -Reproduction Number  (Ro ) እንለዋለን። አንድን ሕብረተሰብ ከኩፍኝ በ Herd Immunity አማካኝነት ከበሽታ ለመከላከል ከ93-95% የሚደርሰው የህብረተሰቡ አካል በከትባት ወይም በበሽታው አስቀድሞ መያዝ ምክንያት ለበሽታ የመከላከል አቅም ሊ ኖረው ይገባል። 

የኮሮና ቫይረስን ካየን  የመባዛት መጠን -Reproduction Number (Ro)  ከ 2.5 እስክ 3 ያህል ነው።  በ Herd Immunity አማካኝነት ከኮሮና ቫይረስ በሽታ (COVID 19) ለመከላከል እስከ 70% ሚደርሰው የ በሽታ የመከላከል አቅም ሊኖረው ይገባል። ክትባት ስለሌለው ይሄ ሊፈጠር የሚችለው እነዚህን ሰዎች ለበሽታ እንዲጋለጡ በመፍቀድ ነው።

ለዛም ነው አሁን  ስለ Herd Immunity ማውራት ጊዜውን ያልጠበቀና እና አደገኛ ነው የምንለው። ዘርዘር አድርገን እናውራ።

በመጀምሪያ በኮርና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ዘላቂ የሆነ የመከላከል አቅም ይኖራቸዋል ወይ የሚለው አይታወቅም።  ለምሳሌ በሽታው መጀመሪያ የታየባቸው እንደ ውሃን (ቻይና ) አካባቢዎች ከበሽታው ነፃ ናችሁ የተባሉ ሰዎች ተመልሰው በሽታው እንደተገኘባቸው ሪፖርቶች እያየን ነው። ስለዚህ በኮሮና  ቫይረስ የተያዘ ሰው ዘላቂ በሽታውን የመከላከል አቅም ስለማዳበሩ የምናውቀው ነገር የለም ወይም በጣም አናሳ ነው። በሌለበት ስለ Herd Imunity ማውራት አይቻልም።

ሁለት ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ዘላቂ የሆነ በሽታን የመከላከል አቅም ይኖራቸዋል እንኳ ብንል የ Herd Immunity ውጤት ወይም Herd Effect  ላይ ለመድረስ 70% ሰው በበሽታው መያዝ ይኖርበታል። እስካሁን በምናውቀው መረጃ በ COVID19 ከታ መሙት ሰዎች ውስጥ ከ 15-20 % የሚሆኑት በሆስፒታል ተኝተው መታከም ይኖርባቸዋል ፣ እስከ 5% የሞሆኑት ደግሞ የ ፅኑ ህሙማን ደረጃ ክትትል ያስገልጋቸዋል።  ከሁሉም ቦታዎች ካሉ መረጃዎች አነስ ያለውን ቁጥር እንኳ ብንወስድ እስክ 1% ያህል ሰው ለሞት ይዳረጋል። 

Hospitalization, intensive care unit (ICU) admission, and case–fatality percentages for reported COVID–19 cases, by age group —United States, February 12–March 16, 2020

ያንን ወደ ኢትዮጵያ ወስደን ስንተረጉመው ፣ 100 ሚልየን ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ አለ ብለን ብንነሳ ይሄ የ Herd Immunity ምክር ይሰራል እንኳ ቢባል 70 ሚልየን ሰው መታመም አለበት። ከነዚህ ውስጥ እስክ 15 ሚልየን የሚሆኑት የሆስፒታል አልጋ አግኝተው መታከም አለባቸው።  ወደ 3,500,000 ሰው ደግሞ ፅኑ ሕክምና ያስፈልገዋል። ወደ 700,000 የሚሆን ሰው ደግሞ ምንም ሕክምና ቢደረግለት ህይወቱ ያልፋል። እንግዲህ ሰው ዝም ብሎ ስራውን ይቀጥል ፣ በ Herd Immunity እንድናለን የሚሉ አደናጋሪ ሃሳቦችን የሚሰጡ ሰዎች የሚያቀርቡት ሃሳብ ዋጋው ይሄ ነው።  3,500,000 የሚደርስ ሕዝብ ለፅኑ ህመም ደረጃ ቢጋለጥ ማወቅ ያለብን – በ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የ መተንፈሻ መሳሪያዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ብቻ መሆናቸውን ነው ። 19 ሚልየን ሕዝብ የሞኖርባት የ ኒውዮርክ ስቴት የኮሮና ቫይረስን ለማከም ወደ 30,000 ተጨማሪ ቬንትለተሮችን ነው የጠየቀችው። 

ከዛ ባለፈ የሚሞቱት በእድሜ የገፉ ሰዎች ናቸው የሚል ሃሳብ በ ሞራልም ትክክል ያልሆነ እና ይሄን ሃሳብ ከሚያጋሩ ሰዎች የማይጠበቅ ነው። ማነው እናቱን እና አባቱን  ለበሽታ አሳልፎ የሚሰጥ። 

እሱም ቢቀር  በቅርብ ጥናቶች እንዳየነው ደግሞ ብዙ ወጣቶች በዚህ በሽታ ለፅኑ ህመም አልፎም ለሞት እንደሚዳረጉ አሳይታል። ወደ ሆስፒታ ገብተው መታከም ከነበረባቸው ሰዎች ውስጥ ወደ 38% የሚሆኑት  እድሜያቸው ከ 20 እስክ 54 ዓመት የሚደርሱ ነበሩ ። 

አዎ ቤት  መቀመጥ ፣ ስራን  ማጣት ከፍተኛ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ያመጣል። ኮሮና ቫይረስን ግን እንደ ልብ እንዲስፋፋ ከፈቀድንላት ግዳቱ ከዛም የከፋ ነው።

የቫይረሱን ባህሪ  በማናውቅበት ሁኔታ እና ክትባት በሌለበት ሁኔታ ስለ Herd Immunity  ማውራት ህዝብን በማደናገር የበለጠ ጥፋት ከምፍጠር ውጭ ሳይንሳዊ መሰረት የለውም።

አሁንም ያለው ብችኛ አማራጭ የ  ቫይረሱን መስፋፋት መጠን (Ro ) ለመቀነስ አካላዊ መራራቅን መፍጠር- ከቤት ባለመውጣት ፣ ሰው የሚበዛበት  ቦታ ላይ ባለመገኘት እና ደግሞ ወደ ራሳችን እና በቅርብ ወዳሉ ሰዎች መተላለፉን ለመቀነስ እጃችንን ሁልጊዜ በአግባቡ መታጠብ ነው። እንደ ቻይና እና ደቡብ ኮሪያ ያሉ አገራት ደግሞ በከፍተኛ ርብርብ ፣ ከቤት ባለመውጣት እና ሌሎች የመከላከል መርሆዎችን በመከተል በሽታውን ማሽነፍ እንደሚቻል አሳይተውናል። 

በጤና ጥበቃ የሚነገረንን መግለጫዎች  በአግባቡ እንከታተል።

ባለንበት ራሳችንን እንጠብቅ፡፡

የጤና ወግ

በመረጃ የተመሰረተ ሕክምና ብቻ ።  

………………………………………………………………………………………………………………………..

ይህ የጤና ወግ ድረ ገፅ ነው።
ስለ ጤንነታችሁ ማወቅ የምትፈልጉትን መረጃ የምታገኙበት ፣ በህክምና ባለሙያዎች የሚዘጋጅ የመረጃ ምንጭ ነው።
ሁልግዜም ከሀኪማችሁ ተማከሩ፣ ተጨማሪ መረጃ ከፈለጋችሁ የኛን ድረ ገፅ ጎብኙ።

በጥናት የተደገፈ መረጃ ብቻ እናቀርባለን።

የህክምና ባለሙያዎች ለህሙማኖቻችሁ የሚሆን የሚነበብ መረጃ ከፈለጋችሁ ይህን ግፅ ጠቁሟቸው። ህሙማኖቻችሁ እንዲያውቁት የምትፈልጉትን ነገር መረጃ ጠቅሳችሁ ፃፉልን፣ ስምችሁን ጠቅሰን እናወጣለን። የህክምና ተማሪዎች እንዲጽፉ እናበረታታለን።

በተጨማሪም በጤና ወግ ፖድካስት፣  በ ዩትዩብ ፣በ ትዊተር ፣ በ ፌስቡክ ፣ በቴሌግራም የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ገፆቻችን ታገኙናላችሁ ።