በእምነት የሻው በቅ/ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም የህክምና ኮሌጅ የ5ኛ ዓመት የህክምና ተማሪ
የወር አበባ ዑደት የምንለው የወር አበባ ከጀመረበት የመጀመሪያው ቀን አንስቶ የሚቀጥለው የወር አበባ እስከሚጀምርበት የመጀመሪያው ቀን ያለውን ነው፡፡
የወር አበባ ዑደት ዋና ተግባር በእንቁልጢ (የእንቁላል እጢ) ዉስጥ ከሚገኙት ያልበሰሉ እንቁላሎች በየወሩ (በየ 28 ቀኑ) አንዱን መርጦ በማብሰል ምናልባት የወንድ ዘር ፍሬ ወደ ማህፀን ቢገባ ፅንስ እንዲፈጠር ዝግጁ ለማድረግ ነዉ፡፡ ነገር ግን ይህ ሳይሆን ቢቀር ከማህፀን የሚፈስ ደም ሆኖ ወደ ዉጪ ይወጣል፡፡ ይህንንም የወር አበባ እንለዋለን፡፡ መደበኛዉ የወር አበባ ዑደት ከ 21 እስከ 35 ቀን ሲሆን የጊዜው ርዝመት እንደየሴቶቹ ይለያያል፡፡ ነገር ግን በአማካኝ 28 ቀንን መዉሰድ እንችላለን፡፡
የወር አበባ ዑደት ላይ ምን ይፈጠራል?
በእያንዳንዱ ዑደት መጀመሪያ ላይ ከሴቲቱ እንቁልጢ ዉስጥ ለጋ እንቁላሎች ተመርጠዉ ወደ ብስል እንቁላልነት ያድጋሉ በዚህ ጊዜ በበሰሉት እንቁላሎች ዙሪያ ያለው ሽፋን ኤስትሮጅን የሚባለዉን ሆርሞን ያመነጫል፡፡ በእነዚህ የበሰሉ እንቁላሎች የሚመነጨው ኤስትሮጅን ወደ ማህፀን ይሄድና የማህፀን የዉስጥ ግድግዳ እንዲወፍር ትዕዛዝ ይሰጠዋል፡፡ የማህፀን ዉስጣዊ ግድግዳ ይህን ትእዛዝ በመቀበል ቀድሞ ከነበረዉ ዉፍረት ይጨምራል፡፡
ይህንን ሂደት በ28 ቀን ዑደት ምስል ላይ ስናሰፍረዉ ከአንድ እስከ አስራ አራት ያለዉን ቀን ይይዛል፡፡
ቀን 1 _____↔________ቀን 14 _____________ ቀን 28
ስለዚህ በአስራ አራተኛዉ ቀን በእንቁልጢ ዉስጥ ጥቂት የበሰሉ እንቁላሎች ሲኖሩ በማህፀን ዉስጥ ደግሞ ዉስጣዊ ግድግዳዉ ወፍሮ ተዘጋጅቷል ማለት ነዉ፡፡ በዚህ ጊዜ አብዛኞቹ እንቁላሎች ይሞቱ እና አንዱ ብቻ ይቀራል፡፡
በወር አበባ ዑደት መካከል ላይ (አጋማሽ ላይ) ማለትም በ14ኛዉ ቀን አካባቢ የሚከተሉት ለውጦች ይደረጋሉ፡፡
- እንቁላሉ ከእንቁልጢ በመዉጣት በአስተላላፊ ቱቦ (Fallopian tube) በኩል አድረጎ ወደ ማህፀን አቅጣጫ መሄድ ይጀምራል፡፡
- እንቁልጢ ፕሮጀስትሮን ሚባል ሆርሞን ማምረት ይጀምራል፡፡
ይህ ፕሮጂስትሮን የሚባለዉ ሆርሞን ወደ ማህፀን በመሄድ ቀድሞ ወፍሮ የነበረዉን ግድግዳ በደምስሮች እና በእጢዎች እንዲበለፅግ ያደርገዋል፡፡ የዚህ ሁሉ የማህፀን ግድግዳ መዘጋጀት ዓላማዉ ዕንቁላሉ ከወንዴ ዘር ጋር ቢገናኝ (ሴቲቱ ሩካቤ ብትፈፅም) በዚህ የማህፀን ግድግዳ ላይ ተጣብቆ ወደ ፅንስነት ማደግ እንዲችል ነዉ፡፡
ይህንን ሂደት በ28 ቀን ዑደት ምስል ላይ ስናሰፍረዉ ከ14ኛዉ ቀን በኋላ ያለዉን ይይዛል፡፡
ቀን 1 ____________ቀን 14______↔__________ ቀን 28
በወር አበባ ዑደት ውስጥ ካሉት ቀናት መካከል በዚህ እንቁላሉ በሚለቀቅበት ጊዜ ግንኙነት ቢፈጸም እርግዝና የመፈጠር እድሉ ሰፊ ይሆናል፡፡ ይህም ብዙ ጊዜ ከሚቀጥለው የወር አበባ 12 እስከ 14 ቀን በፊት ያሉትን ቀናት ይመለከታል፡፡
የበሰለው እንቁላል ከተለቀቀበት ጊዜ አንስቶ ላሉት 2ቀናት ይቆይና ወንዴ ዘር ካልመጣና ካልተገናኘዉ ይሞታል፡፡ ይህ በአስተላላፊ ቱቦዎች ዉስጥ እያለ የሞተዉ እንቁላል በሰዉነታችን ነጭ የደም ህዋሳት ይበላል፡፡ በመጨረሻም እንቁልጢው ፅንስ ባለመፈጠሩ ምክንያት ፕሮጅስትሮን ማምረቱን ያቆማል፡፡ በዚህ ጊዜ ወፍሮና በደምስር በልፅጎ የነበረዉ ዉስጣዊ የማህፀን ግድግዳ ይሸረሽርና ከደም ጋር ይወጣል፡፡ ሴቲቱም የወር አበባ ይኖራታል ማለት ነዉ፡፡ ይህ ሁኔታ ለአምስት ቀናት አካባቢ ይቀጥላል፡፡ በጤነኛ ሴቶች ላይ ከ 20 እስከ 80 ሚሊ ሊትር ያህል ደም ይፈሳል፡፡
ይህ ሁሉ ባይሆን እና የወንዴ ዘር ከእንቁላል ጋር ቢገናኝ ግን ውሕደት (Fertilization) ይከሰታል፡፡ የተዘጋጀዉ የማህፀን ግድግዳ ላይም በሂደት የዳበረዉ እንቁላል ተጣብቆ ወደ ፅንስ እድገት ያመራል፡፡ የማህፀኑ ዉስጣዊ ግድግዳም አስፈላጊ በመሆኑ እንደበፊቱ የሚሸረሸር አይሆንም፤ ፕሮጅስትሮንም መመረቱን ይቀጥላል፡፡ በዑደቱ መጨረሻ ላይም ደም መፍሰሱ ይቀራል ማለት ነዉ፡፡ የወር አበባ መጥፋት የእርግዝና የመጀመሪያ ምልክት የሆነበትም ምክንያት በዚህ ነዉ፡፡