ቃልኪዳን ወንድወሰን (ማዩንግሰንግ የሕክምና ኮሌጅ የ4ኛ ዓመት ተማሪ)

By Kalkidan Wondwossen, C1 Student, Myungsung Medical College

Reviewed by- Dr Lidya Million, Pediatrician

 

በህጻናት ላይ የሚከሰት የተቅማጥ በሽታ

  • ተቅማጥ ምንድን ነው?

ተቅማጥ በ 24 ሰዓት ውስጥ ቢያንስ ሦስት ጊዜ የላላ ወይም ውሃማ ሰገራ ማስውገድን ያመለክታል፡፡

አብዛኛውን ጊዜ የአንጀት ውስጥ ኢንፌክሽን ምልክት ነው፡፡

ሦስት የተቅማጥ ዓይነቶች አሉ እነሱም፡-

  • አጣዳፊ ውሃማ ተቅማጥ – ለብዙ ሰዓታት ወይም ቀናት ይቆያል, እና ኮሌራን ያጠቃልላል
  • አጣዳፊ ደም የቀላቀለ ተቅማጥ (ዳይዘትሪ) – እና
  • የማያቋርጥ ተቅማጥ – ለ 14 ቀናት ወይም ከዚያ በላይ ይቆያል፡፡

በልጆች ላይ የተቅማጥ በሽታ ተጽእኖ?

  • የተቅማጥ በሽታ ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት ሞት ምክንያት ከሆኑ ነገሮች መካከል በሁለተኛነት ይጠቀሳል፡፡
  • በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ወደ 1.7 ቢሊዮን የሚጠጉ ህጻናት የተቅማጥ በሽታ ተጠቂዎች ይሆናሉ።
  • በዚህ በሽታ የዓመቱ ወደ 525,000 ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትን ህይወታጨቸውን ያጣሉ።
  • በልጆች የአካልና ዐዕምሮ ዕድገት ላይ ጎጂ ተጽእኖ ያስከትላል፡፡
  • ተቅማጥ ከአምስት አመት በታች ለሆኑ ህጻናት ቀዳሚው የተመጣጠነ ምግብ እጥረት መንስኤም ነው።

የተቅማጥ በሽታ መንስኤዎቹ  ምንድን ናቸው?

ተቅማጥ በዋናነት በተለያዩ የባክቴሪያ፣ የቫይረስ እና የጥገኛ ህዋሳት/ ፓራሳይት በሽታ አምጪ ተዋሕሲያን አማካኝነት የሚከሰት የኢንፌክሽን ምልክት ሲሆን አብዛኛዎቹ  በሰገራ በተበከለ ውሃ እና ምግብ  ውስጥ ይተላለፋሉ።

  • በጨቅላ እና በትናንሽ ሕፃናት ውስጥ ውሃማ ተቅማጥ መንስኤ በዋነኛነት ሮታ ቫይረስ ሲሆን በመቀጠል ክሪፕቶስፖሪዲየም  ነው፡፡
  • በትልልቅ ልጆች ላይ ደግሞ አጣዳፊ ውሃማ ተቅማጥ አብዛኛውን ጊዜ በ ኢንትሮቶክሲክ ኢ. ኮላይ ምክንያት ይከሰታል፡፡
  • ሺጌሎሲስ በታዳጊ ሀገራቶች ውስጥ ለሚኖሩ ህጻናት በጣም የተለመደ  ደም የቀላቀለ ተቅማጥ አምጪ ህዋስ ሲሆን ኢንትአሞይባ ሂስቶለቲካ የተባለው ፕሮቶዙአ ሌላው መንስኤ ነው፡፡
  • የደም የቀላቀለ ተቅማጥ የባክቴሪያ መንስኤዎች ሳልሞኔላ ኢንቴሪካ ፣ ካምፓይሎባክተር ፣ ኢንትሮሄሞራጂክ  ኢ. ኮላይ እና ኢንትሮኢንቫሲቭ ኢ. ኮላይ ይጠቀሳሉ፡፡
  • የአንድአንድ ምግቦች አለመመቸት (ምሳሌ፡-ወተት) ሌላው የተቅማጥ በሽታ መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

 

እንዴት ይተላለፋል?

  • አብዛኛዎቹ የተቅማጥ በሽታ አምጪ ጀርሞች ከአንድ ሰው ወደ ሌላው በሰገራ በተበከለ ውሃ፣ ምግብ ወይም እቃዎች ይተላለፋሉ። ይህ የሚሆነው፡-

◊ ሰዎች እና እንስሳት ሰዎች በሚጠጡት የውሃ ምንጮች ውስጥ ወይም አቅራቢያ ይጸዳዳሉ።

◊ የተበከለ ውሃ ሰብሎችን በመስኖ ለማልማት ይውላል።

◊ ምግብ አዘጋጆች ምግብ ከማብሰላቸው በፊት እጃቸውን አይታጠቡም።

◊ የተበከሉ እጆች ያላቸው ሰዎች እንደ የበር እጀታዎች ወይም የማብሰያ ዕቃዎችን ይነካሉ።

ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?

  1. የሰውነት ድርቀት እና የንጥረ ነገሮች መዛባት – ለሞት የሚዳርግ ዋነኛ ምክንያት ነው፡፡

ከሰውነት ፈሳሽ መሟጠጥ (ቢያንስ ከሚከተሉት ምልክቶች ሁለቱ)

  • ድካም እና የንቃተ ህሊና ማጣት
  • የሰረጎዱ አይኖች
  • በደንብ መጠጣት ወይም መጠጣት አለመቻል
  • የቆዳ መቆንጠጥ በጣም በዝግታ ይመለሳል (≥2 ሰከንድ)

የንጥረ ነገሮች መዛባት በዋናነት የፖታስየም ማነስ እና የሶዲየም ማነሰ ወይም መብዛትን ያጠቃልላል።

  1. የተመጣጠነ ምግብ እጥረት – ተደጋጋሚ ተቅማጥ ከተመጣጠነ ምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ ሊከሰት ይችላል፡፡ ቀደም ሲል በነበረ የተመጣጠነ ምግብ እጦት ላይ ሲከሰት ደግሞ የድርቀት ምልክቶች ይሸፈናሉ ፤ እንዲሁም ከኩፍኝ በኋላ ብዙም ሳይቆይ  ሲከሰት ወይም በነባር የቫይታሚን ኤ እጥረት  ላይ – ዓይነ ስውርነትን ያስከትላል፡፡
  2. የማዕከላዊው የነርቭ ሥርዓት ችግር – በተቅማጥ በሽታ መቼት ውስጥ የነርቭ ችግር መገለጫዎች የሚጥል በሽታ እና የአንጎል በሽታን ሊያካትት ይችላል ።

ብዙውን ጊዜ በሃይፖግላይሴሚያ(የደም ውስጥ ስኩአር መቀነስ)፣ የሶዲየም ማነስ ወይም በማጅራት ገትር በሽታ ምክንያት ይታያል።

 

እንዴት ሊታከም ይችላል?

አጣዳፊ ተቅማጥ ላለባቸው ሕፃናት የሚሰጥ ሕክምና የፈሳሽ እና የኤሌክትሮላይት መዛባትን ማስተካከል ፣ ተገቢውን የተመጣጠነ ምግብ መስጠት እና ተጓዳኝ ሁኔታዎችን/በሽታዎችን መቆጣጠርን ያጠቃልላል። ባስቀመጣቸው ጊዜ ከሰውነት የሚወጣውን ፈሳሽና ንጥረ ነገር የሚተካ Oral Rehydratin Salt (ORS) በተገቢው ልኬት በውሃ በመበጥበጥ ማጠጣት ያስፈልጋል፡፡
በአንዳንድ ሁኔታዎች የአንቲባዮቲክ ሕክምና አስፈላጊ ነው፡፡
አጣዳፊ ተቅማጥ እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በተያያዥነት ያለባቸው ህጻናት የሚሰጣቸው ፈሳሽ ም ሆነ ምግብ በጥንቃቄ ካልተመጠነ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። ስለዚህ እንደዚህ አይነት ህጻናት ለማገገም ልዩ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል፡፡
የተቅማጥ በሽታ ያለባቸው ህጻናት በተቻለ መጠን ከሌላው ጊዜ በተለየ ተጨማሪ ጡት መጥባት እና ፈሳሽ ምግቦች መውሰድ ይኖርባቸዋል ፡፡ በተጨማሪም የዚንክ ንጥረ ነገር ማሟያ መስጠት ይመክራል።
ልጆች በተቅማጥ በሽታ በተጠቁ ጊዜ አመጋገባቸው መቆጣጠር ቶሎ እንዲአገግሙ እና በሽታው እንዳይባባስ ይረዳል፡፡ ስለዚህ፡-

  • በቀን ውስጥ 3 ጊዜ ትልልቅ ምግቦችን ከመመገብ ትናንሽ ምግቦችን ቶሎቶሎ ቢመገቡ
  • ፓስታ ወይም ነጭ ሩዝ ፣ የበሰሉ አትክልቶች ፣ የበሰለ ስጋ እና እንቁላል  ፣ ከተጣራ ስንዴ የተዘጋጁ የዳቦ ምርቶችን ቢመገቡ ይመከራል፡፡

በአንፃሩ ደግሞ ህጻናት በዚህ ወቅት ከአንዳንድ  የምግብ አይነቶች መቆጠብ አለባቸው፡፡ እነሱም፡-

  • የተጠበሱ ምግቦች፣ ቅባት የበዛባቸው ምግቦች፣ የታሸጉ ምግቦች እና መጠጦች( ለስላሳ፣ጁስ…) ወዘተ
  • ወተት እና ሌሎች የወተት ተዋጽኦዎች ተቅማጥን የሚያባብሱ ወይም የሆድ መነፋት የሚያስከትሉ ከሆነ ልጅዎን ከነዚህ ምግቦች መከልከል ያስፈልጋል፡፡

እንዴት መከላከል ይቻላል?

  • የተቅማጥ በሽታን ለመከላከል የሚወሰዱ እርምጃዎች የሚከተሉትን ያካትታሉ:
  • ክትባት – የኩፍኝ፣ ሮታ ቫይረስ እና ኮሌራ ክትባት ተቅማጥን ለመከላከል ወሳኝ መሳሪያ ነው።
  • ጡት ማጥባት
  • እጅን በሳሙና መታጠብ
  • የታከመ የመጠጥ እና የምግብ ማብሰያ ውሃ መጠቀም
  • በቂ የንፅህና አጠባበቅ እና የቆሻሻ አወጋገድ
  • የተመጣጠነ ምግብ – የአመጋገብ ሁኔታን ማመቻቸት
  • በተቅማጥ በሽታ ምክኒያት የሚከሰት ሞትን ለመቀነስ፡-
  • ተገቢውን ህክምና ማድረግ
  • የጤና እንክብካቤ አቅራቢዎችን እና የማህበረሰብ ጤና ባለሙያዎችን በተቅማጥ ህክምና ላይ ማሰልጠን
  • እናቶች እና ተንከባካቢዎች የታመሙ ህፃናትን መንከባከብ እና የህክምና እርዳታ መቼ እንደሚፈልጉ ማሳወቅ
  • የላብራቶሪ ምርመራ አቅምን መገንባት እና የተቅማጥ መንስኤዎችን መለየት

 

Reference

1. https://www.uptodate.com/contents/approach-to-the-child-with-acute-diarrhea-in-resource-limited-settingshttps:

2. /www.cdc.gov/healthywater/pdf/global/programs/globaldiarrhea508c.pdf

3. https://www.who.int/news-room/fact-sheets/detail/diarrhoeal-disease