እንዴት ከረምኩ? እንዴትስ ከረማችሁ? 🙂
ከመጋቢት 4 ቀን በኋላም ከስጋቱና ከቢሮው ድባብ በስተቀር ስራ እንደወትሮው ነው፡፡ ሞተረኛችን ነበር በመጀመሪያ የነገረኝ፡-
“ሰማሽ ሀገር ውስጥ ገባ እኮ!”
“ምን?”
“የኮረና ቫይረስ አንድ ጃፓናዊ ተገኘበት! ”
“ኸረ? አልሰማሁም ነበር ያው የሚጠበቅ ነው”
“ወይኔ በቃ አለቀልን!”
“እንዴ! ገና በአንድ ሰው እንደዚህ ትላለህ? ስለጥንቃቄዎቹ ማንበብ መስማት መጠንቀቅ ነው፡፡ እና ተረጋጋ ደሞ ሰላምህን ጠብቀህ ሰላም እንደምትሰጠን ተስፋ አለኝ ፡)” ጮክ ብሎ በመናገርና ሁሌ “በመነጫነጭ ስለሚታወቅ” ነው እንደዛ መፎገሬ፡፡
አስራ አምስት ቀን ብቻ ያለፈ አይመስልም ክብድ ድብብ ያሉ ሁለት ሳምንታት፡፡ አብዛኛው ቀን የበዓል ማግስት ነው ሚመስለው፤ ሳንፈልግ እየተጎተትን የምንመጣበት ዓይነት፡፡ አንድ ሁለት ቀን በክፍሌ አብረውኝ ሚሰሩትን ልጆች እጃቸውን ያልታጠቡ እንዲታጠቡ አስታውስ ነበር አሁን መታጠቡ ልማድ ሆኖዋል፡፡ ሞተረኛችንማ ታጥቦም በአልኮል ይጠርጋል፡ መታጠብ እንደሚበቃው ባይሆን በብልቃጥ ቦርሳው ውስጥ ቢይዝ እንደሚጠቅመው ብነግረውም አልሰማ ብሎ ለደንበኛ ያስቀመጥነውን አልኮል እየፈጀ አስቸግሮ ነበር፤ ሰሞኑን ያነበብኳትን የሳሙና ኬሚስትሪ ስነግረው፡ አሁን አሁን እኔ ሳላየው ብቻ ነው ከታጠበ በኋላ በአልኮል ሚጠርገው ፡) የኔ ዶክተር እሷ ናት ይል ጀምሮዋል ፡)
የመጀመሪያው አንድ ሳምንት እሩቅ ያለ ግን የማይደርስብንን አሳዛኝ ወሬ እንደሰማን ነገር ቶሎ ቶሎ እጅ ከመታጠብ ባለፈ ሁሉም ነገር በአንፃራዊነት በደህነኛው ጊዜ እንደነበረው ተመሳሳይ ነበር፡፡ በእርግጥ አሁንም ያው ነው፡ የደንበኛውና የሰራተኛው መውጣት መግባት ፤ ዶክመንትና ወረቀት መቀባበሉ ፤ ገንዘብ መቀበል መክፍሉ፤ በአንዲት እስክሪፕቶ ደንበኛን ማስፍረሙ፤ በአንድ ስልክ ለሁለት ለሶስት መጠቀሙ፤ በሊፍት መንቀሳቀሱ፤ የምሳ ሰዓት አብሮነቱ ፤ በተጋጠሙ ጠረጴዛዎች አጠገብ ለአጠገብ መስራቱ ሌሎችም ያው እንደ ቀድሞ ናቸው፡፡ ባጠቃላይ ‘Ethio-twitter quarantine threads’ ከሌላ አለም የሚመጡ ነው ሚመስሉኝ እዚህ ሆኜ ሳያቸው ፡)
ሰሞኑንም የሰራተኛው ስጋት የሚነበብ እየሆነ ከመምጣቱ በስተቀር በተግባር ብዙም የተለየ ነገር አይታይም፡ ፤ብዙ ሰው ያገኘውን ዓይነት ማስክ መጠቀም ጀምሮዋል፤ ክሊኒካል ማሰክ ከገበያ ላይ በመጥፋቱ ባብዛኛው ከጨርቅ የተሰሩ ማስኮችን ነው ሚጠቀመው፡፡ አብዛኞቹ ማስኮች ደረጃቸው ዝቅተኛ ከመሆኑ ባሻገር በሁለቱም በኩል መልካቸው አንድ ዓይነትነው፡፡ ማስክ እንደዋዛ መጠቀሙ በራሱ ሌላ ስጋት ነው፤ በስራ ጫናና በደንበኞች መስተንግዶ ላይ ማስክ ሲለበስና ሲወልቅ ጥንቃቄ በጎደለው መልኩ ስለሚሆን ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ አንዱ የተጨራመተችዋን የጨርቅ ማስክ ከኪሱ አውጥቶ ሲለብሳት አይቼ አይ ዎዝ ሶ ሾክድ ላይክ ደምሴ ዳምጤ! …“ወይኔ ወይኔ! በራሱ ግብ ላይ! በራሱ ግብ ላይ!……” ………. ደረገመው!…… ዓይነት ፡) ኸረ እንዲያውም ብዙ ሰው መነጽር አናት ላይ የመስቀልን ያህል አቅልሎ ማስክ አገጩ ላይ ሚያንከራትተውና መልሶ ሚለብሰውስ ቢሆን ምን የሚሉት ነው?? እኔ በበኩሌ እንደ ቦንብ አምካኝ ነው ማስክ ቴክ ኬር ማደርገው ፡)
ሥራ ላይ በመሆኔ ከበሽታው ስጋት ባለፈ ይህን መሰሎችን አለማወቅና ‘ስህተት’ በየቀኑ ማየቱ የሚፈጥርብኝ distress ይብሳል፡፡ ከጥቂት በስተቀር የአብዛኛው ሰው ስራ ባጠቃላይ በሚባል መልኩ ማኑዋል ስለሆነ “ከቤታችሁ ሆናችሁ ስሩ” /home working/ ትልቅ ፈገግታ ትቸረናለች፡፡ኸረ በዛ ሁሉ ወረቀት ቅብብሎሽም “social distancing” እንኳን “ድሎት” ሆናብን ከርማለች፡፡ በስማም የምንቀባበለው የወረቀት ብዛት ግን! እንደዚህ መዓት መሆኑ አሁን ነው ያስታወቀኝ!! በዛ ላይ ካሸራችን የምታስፈርመኝ “አስቸኳይ” ቼኮች ምን ይሉታል? ተረጋግታ ለምን አንድ ጊዜ አትመጣም? ኸረ ደሞ ምን ሊሆኑ ነው ጁኔሮቹ ሺ ግዜ እኔ ጋር ሚመላለሱት? እስቲ ባካችሁ ጉዳያችሁን ሰብሰብ አድርጋችሁ አንዳችሁ በቀን ከአንድ ጊዜ በላይ ባትመጡብኝ፡ አይቻልም? ሞክሩ፡፡ በቀን አንድ ጊዜና ከዛ ባነሰ የመጣ ሽልማት አለው፡፡ ፡)
ከሰሞኑ ምንም እንኳን እኔ በ45/50 ደቂቃ ዎክ ቢሮ መግባትን ልማድ ባደርግም አብዛኛው ሰው በህዝብ ትራንስፖርት ነው ሚንቀሳቀሰው፤ ታክሲ አሁንም የኋላ ወንበር ላይ 4 ሰው መሆኑን ሰምቼ በ “physical distancing” ተስፋ ቆርጫለሁ፡፡ የአብዛኛው ሰራተኛ ስጋትም ቢሮ ካለው ሁኔታ ይልቅ ፐብሊክ ትራንስፖርት ነው፡፡
So, what solution I’m left with? “Working from home”? 😉 unless we minimize paper money and automate our routines somehow, that is far to fetch. ወደ ቤት ይዤ መሄድ ሚኖርብኝ ሰነድ በአይሱዙ ሚጫን ነው ሚሆነው ፡)
ለጊዜው የጋራ ህንፃችንን የጋራ መንግስታችን አንድ ቢልልን ጥሩ ነበር፡፡ ብዙ መስሪያቤቶችና የገበያ ማዕከሎች ስራ ላይ ስላሉ በየቀበሌው በዚህ ጉዳይ የሚሰራ አካል ካለ ከመገናኛ ብዙሃን ባለፈ በር ለበር ጉብኝት ቢደረግና በየህንፃው ቢደረጉ የሚበረታቱ ነገሮችን ግንዛቤ ማስጨበጥ ቢሰራ የሚጠቅም ይመስለኛል፡፡