Written By Anan Assefa, C2 Student at Jimma University

Reviewed by Dr Gelila Sintayehu, Internist

አቶርቫስታቲን

ሰውነታችን ከምግብ ከሚያገኘው የስብ መጠን በተጨማሪ በራሱ ኮሌስትሮል የተባለ ስብን ያመርታል ። እነዚህም LDL ፣ TAG እና HDL ናቸው ። በደም ውስጥ የሚገኘው LDL እና TAG መጠን ከተገቢው በላይ ሲበዛ ሃይፐርሊፒዴሚያ የሚባል የሰውነት ስብ መብዛት ችግርን ያመጣል ። ለዚህ ሃይፐርሊፒዴሚያ ለተባለ ችግር ህክምና ከሚውሉ መድኃኒቶች መሀከል አቶርቫስታቲን አንዱ ነው ።

አቶርቫስታቲን በሰውነት ውስጥ የሚመረተውን የኮሌስትሮል መጠን በመቀነስ የስብ መጠንን ዝቅ ያደርጋል ። በዚህም LDL እና TAG የተባሉትን የስብ አይነቶችን ይቀንሳል በአንፃሩም HDL የተባለውን ጥሩ የስብ አይነት ደግሞ ይጨምራል ። በዚህ ምክንያት የደምስር ውስጥ ስብ እንዳይከማች በማድረግ ለልብ እና የደም ስር ህመሞች ያለንን ተጋላጭነት ይቀንሳል።

በአሁኑ ወቅት አቶርቫስታቲን ከሃይፐርሊፒዴሚያ በተጨማሪ የስኳር ህመም ላለባቸው እና እድሜያቸው ከአርባ በላይ ለሆነ ህሙማን ይሰጣል ።ከዚህም ሌላ የልብ ህመም ላለባቸው እና የጭንቅላት የደም መፍሰስ ላጋጠማቸው የተወሰኑ ህሙማንም አገልግሎት ላይ ይውላል ።

ይህ መድኃኒት በአፍ በሚዋጡ ክኒኖች መልክ በተለያየ ግራም ተዘጋጅቶ በመድኃኒት መደብሮች በሀኪም ትዕዛዝ ይሸጣል ።

የጎንዮሽ ጉዳቶች

አቶርቫስታቲን ከሚያስከትላቸው የጎንዮሽ ጉዳቶች መሀከል የጡንቻ ህመም ተጠቃሽ ነው ። በተጨማሪም የጉበት ህመም ያለባቸው ሰዎች ላይ የጉበት ህመሙ እንዲባባስ ሊያደርግ ይችላል ። በጥቂት ሰዎች ላይ ደግሞ ጉንፋን መሰል የአፍንጫ መታፈን ፣ ማቅለሽለሽ ፣ ማስመለስ ፣ የሆድ ህመም እና ማስቀመጥ ሊያስከትል ይችላል ። የጎንዮሽ ጉዳት ካስተዋሉ ሁልጊዜም ሀኪምዎን ያማክሩ።

ከምግብ እና ሌሎች መድኃኒቶች ጋር ያለው መስተጋብር

የወይን ጭማቂ በደም ውስጥ የሚኖረውን የአቶርቫስታቲን መጠን በመጨመር ለጎንዮሽ ጉዳት ሊያጋልጥ ስለሚችል አብሮ መውሰድ አይመከርም።በተጨማሪም የአልኮል መጠጦችን መቀነስ አስፈላጊ ነው ። የHIV/AIDS ወይም የ ሄፓታይተስ መድኃኒት የሚወስዱ ፣ የተለያዩ የፈንገስ መድኃኒቶች የሚወስዱ ፣ የሪህ መድኃኒት ፣ የ TB መድኃኒት እና የእርግዝና መከላከያ ኪኒን የሚወስዱ ሰዎች ይህንን አስቀድመው ለሃኪምዎ ያሳውቁ። ምክንያቱም እነዚህ መድኃኒቶች ከአቶርቫስታቲን ጋር ሲወሰዱ መጠናቸውን በማስተካከል ከተጨማሪ ጉዳት ለመከላከል ነው ።

እርጉዝ ሴቶች መውሰድ ይችላሉ?

ይህ መድኃኒት በእርግዝና ወቅት ከተወሰደ በፅንሱ ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል ። በመሆኑም አቶርቫስታቲን በእርግዝና ወቅት እንዲወሰድ አይመከርም ።

አቶርቫስታቲን ከሃኪም ትዕዛዝ ውጪ መወሰድ የለበትም ። ሃኪም ባዘዘሎት መልኩ መድኃኒቶን መውሰድ ከዘነጉ እና ያስታወሱበት ሰአት ከ12 ሰአታት በታች ከሆነ ባስታወሱበት ሰአት ይውሰዱ ። ነገርግን ያስታወሱበት ሰአት መድኃኒቶን መውሰድ ከነበረብዎት ሰአት  ከ12  ሰአታት በላይ ከሆነው ቀጣዩን የመውሰጃ ሰአት ጠብቀው ይውሰዱ እንጂ ተጨማሪ አይውሰዱ ።

እንደ ማንኛውም መድኃኒት አትሮቫስታቲንን ህፃናት ከማይደርሱበት ቦታ ያስቀምጡ ።

 

 

Reference

Bertram G.katzung 14th edition

www.webmd.com