የመሃከለኛ ጆሮ ክፍል ኢንፌክሽን (ኦታይቲስ ሚዲያ-Otitis media)

Written By: Nabil Girma – 5th Year Medical student at Jimma University

Reviewed By: Dr.Lidya Million,  (Assistant Professor of Pediatrics and Child Health )

 

የመሃከለኛ ጆሮ ክፍል ኢንፌክሽን ብዙ ጊዜ በአፍንጫ እና በጉሮሮ ውስጥ በሚገኙ ባክቴሪያዎች ምክንያት የሚፈጠር በሽታ ነው። በልጆች ላይም በይበልጥ የተለመደ ሲሆን የጆሮ  ህመም፣ ትኩሳት ጊዜያዊ የመስማት ችሎታ መቀነስ   የምግብ ፍላጎት መቀነስ እና መነጫነጭ የመሳሰሉ ምልክቶችን ሊያስከትል ይችላል። 

ኦታይቲስ ሚዲያ በአብዛኛው 6 እስከ 24 ወር ባሉ ህጻናት ላይ ይከሰታል፣ 5 አመት በኋላ የመከሰት እድሉ በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ ይሄዳል።ከ4 ህጻናት ውስጥ 3 የሚሆኑት እስከ 3 አመት እድሜያቸው ውስጥ ቢያንስ አንድ ጊዜ በበሽታው ይጠቃሉ።

 

የበሽታው መንስኤ

የጆሮ ኢንፌክሽኖች ብዙውን ጊዜ የሚከሰቱት ከመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽኖች(ለምሳሌ ጉንፋን) በኋላ ነው።እነዚህ ኢንፌክሽኖች በአፍንጫ እና በጉሮሮ ውስጥ ያለውን የውስጠኛውን ክፍል (mucous membranes) እብጠትን ሊያስከትሉ ይችላሉ።ከዚህም በተጨማሪ የሰውነታችንን ባክቴሪያን ከአፍንጫ የማጽዳት ስራን በማስተጓጎል በአፍንጫ ውስጥ ያለውን የባክቴሪያ መጠን ይጨምራሉ። 

የመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽኖች Eustachian tube (የመሃከለኛ ጆሮን ከጉሮሮ አካባቢ ጋር የሚያገናኝ ትቦ) ተግባርንም ሊጎዱ ይችላሉ። መደበኛ Eustachian tube ተግባር በጆሮው ውስጥ ያለውን መደበኛ ግፊት መጠበቅ ነው።የተዳከመ Eustachian tube ተግባር በመሃከለኛ ጆሮ ክፍል ውስጥ ያለውን ግፊት ይለውጣል (ልክ አውሮፕላን ውስጥ ሲበሩ እንደሚሰማዎት)

ይህ ቱቦ በትክክል በማይሰራበት ጊዜ በመሃከለኛ ጆሮ ውስጥ ያለውን ፈሳሽ በአግባቡ እንዳይወገድ ያደርጋል። ይህም በጆሮ ውስጥ ፈሳሽ እንዲከማች ያደርጋል። በዚህ ጊዜ በጆሮው ውስጥ ባክቴሪያዎች እና ቫይረሶች እንዲበራከቱ በማድረግ በሽታው እንዲከሰት ያደርጋል።   

የጆሮ ኢንፌክሽን ምልክቶች

  • ትኩሳት  
  • አብዝቶ ጆሮን መጎተት
  • መነጫነጭ፣ የእንቅልፍ እጦት( በህመሙ ምክንያት)
  • የእንቅስቃሴ መቀነስ እና የድካም ስሜት
  • የምግብ ፍላጎት ማጣት ወይም የመመገብ ችግር
  •  ማስታወክ ወይም ተቅማጥ
  •  ከውጭ ጆሮ የሚወጣ ፈሳሽ
  •  

  ለጆሮ ኢንፌክሽን  አጋላጭ ሁኔታዎች

  •  6 እስከ 12 ወር  የእድሜ ክልል 
  • በጀርባ አስተኝቶ ማጥባት 
  • የላንቃ ክፍተት ያለባቸው ህፃናት
  • በህጻናት መዋያ ውስጥ የሚቆዩ ህጻናት
  • ለሲጋራ ጭስ ወይም የተበከለ አየር የተጋለጡ  ህጻናት 
  • ኤች አይ ኤድስ (HIV-AIDS) 
  • ዳውን ሲንድረም (DOWN SYNDROME) እና ተመሳሳይ በሽታዎች

የጆሮ ኢንፌክሽን የሚከተሉትን ሊያስከትል ይችላል

  • ቋሚ የመስማት ችግር
  • የጆሮ ታምቡር መበሳት
  • ኢንፌክሽኑ ተዛምቶ በዙሪያው ያሉትን አጥንቶች ሊያጠቃ ይችላል
  • የማጅራት ገትር( Meningitis)

 ምን ምን ምርመራዎች ሊታዘዙ ይችላሉ?

ከተሟላ የህክምና ታሪክ እና የአካል ምርመራ በኋላ የህክምና ባለሙያው አጠቃላይ የደም ምርመራ ሊያዝ ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ ኦቶስኮፕን ( Otoscope )በመጠቀም የውጪውን የጆሮ ክፍል እና ታምቡር ይመረምራል። ኦቶስኮፕ  የህክምና ባለሙያው የጆሮውን የውስጥ ክፍል እንዲያይ የሚያስችል ብርሃን ያለው መሳሪያ ነው።

 የጆሮ ኢንፌክሽን ህክምና 

  • በህክምና ባለሙያ በታዘዙ ጸረ ባክቴሪያዎች(antibiotics) እና ህመም ማስታገሻ መድሃኒቶች ሊታከም ይችላል።

የጆሮ ኢንፌክሽንን እንዴት መከላከል ይቻላል?

  • ህጻናትን በወቅቱ ማስከተብ
  • በአግባቡ ጡት ማጥባት
  • ከሲጋራ ጭስ እና መሰል ነገሮች ልጆችን ማራቅ

  

 ማጣቀሻዎች

  • https://www.uptodate.com/contents/acute-otitis-media-in-children-clinical-manifestations-and-diagnosis?search=otitis%20media%20children&source=search_result&selectedTitle=2~150&usage_type=default&display_rank=2
  • https://www.uptodate.com/contents/acute-otitis-media-in-children-epidemiology-microbiology-and-complications?search=otitis%20media%20children&source=search_result&selectedTitle=4~150&usage_type=default&display_rank=4
  • https://next.amboss.com/us/article/Mj0MaT?q=acute+otitis+media#Zbaf62b3f0ef4064ca2e6087d86fa0801p

   

የጤና ወግ 

ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።

የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።

https://linktr.ee/Yetena_Weg