በዶ/ር ስምዖን ፍትሐአምላክ
(በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊንየም ሜዲካል ኮሌጅ እጩ ሐኪም)

Reviewed by- Dr. Lemma Zewde, Internal Medicine

 

የማጅራት ገትር በሽታ ምንድን ነው?

የማጅራት ገትር በሽታ የሌፕቶሜኒንግስ ማለትም በአንጎል እና በህብለ ሰረሰር ዙሪያ ያሉ ሕብረ ሕዋሳት የመቆጣት በሽታ ሲሆን በሽታው ልዩ የሚያረገው በአብዛኛዎቹ በሽተኞች በአንጎል እና በህብለ ሰረሰር ዙሪያ ባለው ፈሳሽ (ሲኤስኤፍ) ውስጥ መደበኛ ያልሆነ ነጭ የደም ሴሎች (WBCs) ተለይቶ መገኘቱ ነው። አንጎል እና ህብለ ሰረሰር ዙሪያቸውን የሚሸፍኑ ሦስት ንብርብሮች አሉ እነሱም በጠቅላላው ማኒንግስ ተብለው ሲጠሩ፤ ሶስቱ ንብብሮች ደግሞ፡ ፒያ፣ አራክኖይድ እና ዱራ ማተርስ ተብለው ይጠራሉ። በማጅራት ገትር በሽታ የሚጠቃው የአራክኖይድ ክፍል እና ከዚህ በታች የሚንቀሳቀሰው በአንጎል እና በህብለ ሰረሰር ዙሪያ የሚገኘው ፈሳሽ(ሲኤስኤፍ) ነው።

2 ዋና ዋና የማጅራት ገትር ዓይነቶች አሉ። ባክቴሪያዎች የባክቴሪያ ማጅራት ገትር በሽታን ያስከትላሉ። ቫይረሶች የቫይረስ ማጅራት ገትር በሽታ ያስከትላሉ፤ እሱም አሴፕቲክ ማጅራት ገትር ይባላል። ሁለቱም የማጅራት ገትር በሽታ ዓይነቶች ተመሳሳይ ምልክቶችን ሊያስከትሉ ይችላሉ።

 

የበሽታው መንስኤ ምንድነው?

የማጅራት ገትር በሽታ በተለያዩ የባክቴሪያ፣ ቫይረሶች፣ ፈንገሶች እና ጥገኛ ተውሳኮች ሊከሰት ይችላል። አብዛኞቹ ኢንፌክሽኖች ከሰው ወደ ሰው ሊተላለፉ ይችላሉ። አንጎል ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች, ካንሰሮች እና መድሃኒቶች በአነስተኛ ቁጥር ማጅራት ገትር በሽታን ያስከትላሉ። በባክቴሪያ ምክንያት የሚከሰት የማጅራት ገትር በሽታ በጣም የተለመደ እና አደገኛ የማጅራት ገትር አይነት ሲሆን በ24 ሰአት ውስጥ ገዳይ ሊሆን ይችላል። በባክቴሪያ ምክንያት የሚከሰት የማጅራት ገትር በሽታ በአራት ዋና ዋና ባክቴርያዎች ሊከሰት ይችላል።

  • Neisseria meningitidis (meningococcus)
  • Streptococcus pneumoniae (pneumococcus)
  • Haemophilus influenzae
  • Streptococcus agalactiae (group B streptococcus)

እነዚህ ባክቴሪያዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ በማጅራት ገትር በሽታ ከሚሞቱት ከግማሽ በላይ ለሚሆኑት ሞት ተጠያቂ ሲሆኑ እንደ ሴፕሲስ እና የሳምባ ምች ያሉ ሌሎች ከባድ በሽታዎችን ያስከትላሉ። ሌሎች ባክቴሪያዎች ለምሳሌ፣ Mycobacterium tuberculosis፣ ሳልሞኔላ፣ ሊስቴሪያ፣ ስትሬፕቶኮከስ እና ስታፊሎኮከስ፤ ቫይረሶች እንደ ኢንትሮቫይረስ እና መንፕስ፤ ፈንገሶች፣ በተለይም ክሪፕቶኮከስ እና እንደ አሜባ ያሉ ጥገኛ ተውሳኮች ሌሎች የማጅራት ገትር በሽታ መንስኤዎች ናቸው።

 

በበሽታው ምን ያህል ሰዎች ይጠቃሉ?

በአለም አቀፍ ደረጃ የማጅራት ገትር በሽታ ከ100,000 ሰዎች ውስጥ በ20ዎቹ ላይ እንደሚከሰት ይገመታል። ይህም ማለት ወደ 1.2 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች እንደማለት ነው። በሽታው በአለም ደረጃ በየዓመቱ ወደ 171,000 የሚሆኑ ሞቶችን ያስከትላል።

በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች ለማጅራት ገትር በሽታ ተጋላጭ ናቸው ነገር ግን በሽታው በከፍተኛ ሁኔታ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሃገራት ውስጥ ተሰራጭቶ ይገኛል። ይህም ‘’የአፍሪካ የማጅራት ገትር ቀበቶ’’ የሚል ልዩ ስያሜ አግኝቷል። ይህ ቀበቶ በከፊል ወይም በሙሉ እነዚህ ሃገራትን ማለትም (ከምዕራብ እስከ ምስራቅ)፣ ጋምቢያ፣ ሴኔጋል፣ ጊኒ-ቢሳው፣ ጊኒ፣ ማሊ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ጋና፣ ኒጀር፣ ናይጄሪያ፣ ካሜሩን፣ ቻድ፣ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኡጋንዳ፡ ኬኒያ፡ ኢትዮጵያ፡ ኤርትራን ይይዛል። በአፍሪካ ውስጥ ያሉ ሌሎች በርካታ አገሮችም ወረርሽኙ ያጋጥማቸዋል፣ ነገር ግን ብዙም ያልተደጋገሙ እና እርስ በርስ የሚዛመቱ አይደሉም። በቀጠናው በጣም የተጎዱት ቡርኪናፋሶ፣ ቻድ፣ ኢትዮጵያ እና ኒጀር ናቸው። ቡርኪናፋሶ፣ ኢትዮጵያ እና ኒጀር ብቻቸውን 65% የሚሆነውን በአፍሪካ የማጅራት ገትር በሽታ ቁጥር ይይዛሉ።

ኢትዮጵያ ከሰሃራ በስተደቡብ ካሉት የማጅራት ገትር ቀበቶ ሀገራት መካከል ሁለተኛዋ ትልቅ ህዝብ (≈94 ሚሊዮን እ.ኤ.አ. በ2013) አላት። ነገር ግን፣ እ.ኤ.አ. በ2001-2010 ባሉት ዓመታት፣ በአማካኝ በዓመት 1,056 የተጠረጠሩ የማጅራት ገትር ኬዞች ለዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ተደርገዋል። በሃገራችን ትልቆቹ የማጅራት ገትር ወረርሽኞች እ.ኤ.አ. በ1981 እና 1989 የተከሰቱ ሲሆን በዚህም ምክንያት ≈45,000 እና ≈50,000 ሰዎች ተይዘዋል።

 

ለበሽታው ተጋላጭ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ምንድነው?

ምንም እንኳን የማጅራት ገትር በሽታ በሁሉም ዕድሜዎች ላይ የሚከሰት ቢሆንም፣ ልጆች ለአደጋ የተጋለጡ ናቸው። ጭቅላ ሕፃናት በተለየ መልኩ በGroup B streptococcus የመጠቃት ዕድላቸው በጣም ከፍተኛ ነው። ትናንሽ ልጆች ደግሞ በmeningococcus, pneumococcus and Haemophilus influenzae ለመያዝ የበለጠ ተጋላጭ ናቸው። በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች እና ጎልማሶች በተለይ በmeningococcus ለሚከሰት የማጅራት ገትር በሽታ የተጋለጡ ሲሆኑ አረጋውያን ደግሞ በpneumococcus ለሚከሰት የማጅራት ገትር በሽታ ይጋለጣሉ። ከፍ ያለ ስጋት የሚታየው ሰዎች በቅርበት ሲኖሩ ለምሳሌ በጅምላ በሚሰበሰቡበት፣ በስደተኞች ካምፖች፣ በተጨናነቀ ቤተሰቦች ውስጥ ወይም በተማሪ ዶርሚቶሪዎች፣ ወታደራዊ ካምፖች እና ሌሎች የስራ ቦታዎች ላይ ሲሆኑ ነው። እንደ ኤችአይቪ ኢንፌክሽን፣ የምግብ እጥረት፣ የስኳር በሽታ፣ የበሽታ መከላከል አቅም ማነስ እና ሲጋራ ማጨስ ያሉ የበሽታ የመከላከል አቅም ድክመቶች ለማጅራት ገትር በሽታ ተጋላጭነትን ይጨምራሉ።

ሌሎች ለበሽታው ተጋላጭነትን የሚጨምሩ ነገሮች፦

  • የቅርብ ጊዜ ኢንፌክሽን (በተለይ የመተንፈሻ አካላት ወይም የጆሮ ኢንፌክሽን)
  • የማጅራት ገትር በሽታ ካለበት ሰው ጋር በቅርብ መገናኘት
  • የመርፌ አደንዛዥ መድሃኒት መጠቀም
  • የቅርብ ጊዜ የጭንቅላት ጉዳት
  • በጆሮ በኩል ወይም በአፍንጫ በኩል የሚወጣ ፈሳሽ
  • የቅርብ ጊዜ ጉዞ (ለምሳሌ የሃጅ ጉዞ)

 

በሽታው እንዴት ከሰው ወደ ሰው ይተላለፋል?

የመተላለፊያው መንገድ እንደየተዋህሲያኑ ይለያያል። የማጅራት ገትር በሽታን የሚያስከትሉ አብዛኛዎቹ ባክቴሪያዎች እንደ meningococcus፣ pneumococcus እና Haemophilus influenzae በሰው አፍንጫ እና ጉሮሮ ውስጥ ይገኛሉ። በመተንፈሻ አካላት ጠብታዎች ወይም በጉሮሮ ፈሳሾች ከሰው ወደ ሰው ይተላለፋሉ። Group B streptococcus ብዙውን ጊዜ በሰው አንጀት ወይም በሴት ብልት ውስጥ የሚገኝ ሲሆን በወሊድ ጊዜ ወቅት ከእናት ወደ ልጅ ሊተላለፍ ይችላል።

 

ህመምተኛው ምን ምን ምልክቶችን ያሳያል?

በቫይረሶች ወይም በባክቴሪያ የሚመጡ የማጅራት ገትር ዓይነቶች ተመሳሳይ ምልክቶች ሊኖራቸው ይችላል። በአንዳንድ የማጅራት ገትር በሽታ ምልክቶች ከሌሎቹ በበለጠ ጠንከር ያሉ እና የተለየ ህክምና የሚያስፈልጋቸው ሊሆኑ ይችላሉ።

በባክቴሪያ ምክንያት የሚከሰት የማጅራት ገትር በሽታ ምልክቶች ብዙውን ጊዜ በድንገት ስለሚጀምሩ ሰዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ በጣም ሊታመሙ ይችላሉ። በባክቴሪያ ምክንያት የሚከሰት የማጅራት ገትር በሽታ 3 ዋና ዋና ምልክቶች፡-

  • ትኩሳት – ነገር ግን አንዳንድ ሰዎች ከትኩሳት ይልቅ የሙቀት መጠን ዝቅተኛ መሆን ምልክቱ ነው።
  • ራስ ምታት
  • የማጅራት መገተር – ይህ በብዛት በአዋቂዎችና በልጆች ላይ ይከሰታል። ጭቅላ ህጻናት ላይ አይታይም። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች እንደሚከተሉት ያሉ ሌሎች ምልክቶች ሊኖራቸው ይችላል።
  • ማቅለሽለሽ ወይም ማስታወክ
  • ግራ መጋባት ወይም ለመንቃት ከባድ መሆን
  • ብርሃን መኖሩ የበሽተኛውን አይን ማስጨነቅ
  • በቆዳ ላይ ቀይ ወይም ወይንጠጃማ ነጠብጣብ የሚመስል ሽፍታ መከሰት እና ሲነካ የማይጠፋ ሲሆን
  • መጣል እና ማንቀጥቀጥ

በባክቴሪያ ምክንያት የሚከሰት የማጅራት ገትር በሽታ አምጪ ተህዋሲያን በደም ውስጥ በሚዘዋውሩበት ወቅት(ሴፕቲኬሚያ) ሌሎች ምልክቶችን ሊያስከትሉ ይችላሉ ፣ ይህም በፍጥነት ወደ ሴፕሲስ ሊመራ ይችላል ፣ ከእነዚህም መካከል

  • ቀዝቃዛ እጆች እና እግሮች
  • የመገጣጠሚያዎች እና የጡንቻ ህመም
  • ከወትሮው በበለጠ ፍጥነት መተንፈስ
  • ተቅማጥ

ጨቅላ ህጻናት ሌሎች ምልክቶችም ሊኖራቸው ይችላል፡ ከነዚህም ውስጥ፡-

  • ከወትሮው የበለጠ እንቅልፍ ወይም መበሳጨት
  • በደንብ አለመመገብ
  • በራስ ቅላቸው ላይ የተወጠረ ለስላሳ ቦታ መኖር
  • በጭንቅላታቸው ውስጥ ለስላሳ ቦታ (ፎንቴኔል) እብጠት

 

ምን ምን ምርመራዎች ይታዘዛሉ?

የማጅራት ገትር በሽታ በመጀመሪያ ደረጃ ሊታወቅ የሚችለው በምልክቶቹ እና ከጀርባ ብኩል ፈሳሽ በመውሰድ ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ አንድ ዶክተር ቀጭን መርፌን ወደ ታችኛው ጀርባ በማስገባት ትንሽ የአንጎል እና የህብለ ሰረሰር ፈሳሽ ይወስዳል። ይህ ፈሳሽ ላይ የላብራቶሪ ምርመራዎች ያደርጋሉ።

አንድ ሰው በጭንቅላት ውስጥ የሚገኝ እጢ ወይም ከፍ ያለ የጭንቅላት ውስጥ ግፊት(ICP) ያለው እንደሆነ የሚያስጠረጥሩ ነገሮች ልክ እንደ የቅርብ ጊዜ የጭንቅላት ጉዳት፣ የታወቀ የበሽታ መቋቋም ስርዓት ችግር ወይም የነርቭ ምልክቶች ካሳየ የአንጎል እና የህብለ ሰረሰር ፈሳሽ ከመወሰዱ በፊት ሲቲ ወይም ኤምአርአይ ስካን ማድረግ ይመከራል።

ከዚህ በተጨማሪም አንድ ሰው የማጅራት ገትር በሽታ እንዳለበት ከተጠረጠረ፣ ለሰውነት መቆጣት ምልክቶች (ለምሳሌ C-reactive protein፣ ሙሉ የደም ቆጠራ(complete blood count)) እንዲሁም የደም ተዋህሲያን ማራባት(blood cultures) አይነት የደም ምርመራዎች ይከናወናሉ። በከባድ የማጅራት ገትር ዓይነቶች፤ የደም ኤሌክትሮላይቶችን መከታተል አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ, hyponatremia በባክቴሪያ የማጅራት ገትር በሽታ ወቅት የተለመደ ነው።

 

በበሽታው ምክንያት የሚመጡ መዘዞች ምንድነው?

ህክምና ያልተደረገለት የባክቴሪያ ማጅራት ገትር በሽታ ሁል ጊዜ ገዳይ ነው። እንደ የዓለም ጤና ድርጅት የባክቴሪያ ማጅራት ገትር በሽታ ህክምና እየተሰጠ እንኳን 16.7% አጠቃላይ የሞት መጠን አለው። የቫይራል ማጅራት ገትር በአንጻሩ በራሱ የሚፈታ እና አልፎ አልፎ ለሞት የሚዳርግ ነው።
ሕክምና የተሰጠው የባክቴሪያ የማጅራት ገትር በሽታ ሞት የማስከተል ዕድሉ፡ በታካሚው ዕድሜ እና በበሽታው መንስኤ ላይ የተመሠረተ ነው። አዲስ ከተወለዱ ሕፃናት ውስጥ 20-30% የሚሆኑት በባክቴሪያ ማጅራት ገትር በሽታ ሊሞቱ ይችላሉ። ይህ ቁጥር በዕድሜ ከፍ ባሉ ልጆች ላይ በጣም ያነሰ ነው፣ የሟችነት ዕድላቸው 2% ገደማ ነው። ነገር ግን በአዋቂዎች ውስጥ እንደገና ወደ 19-37% ያድጋል።

በባክቴሪያ ምክንያት በሚከሰት የማጅራት ገትር በሽታ ከተያዙ ከ5 ሰዎች አንዱ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ የድህረ-ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል። ከእነዚህ ድህረ-ተፅዕኖዎች መካከል የመስማት ችግር፣ የሚጥል በሽታ፣ የእጅና እግር ድክመት፣ የእይታ, የንግግር, የቋንቋ, የማስታወስ እና የመግባባት ችግር፣ እንዲሁም ከሴፕሲስ በኋላ ጠባሳ እና እግር መቆረጥ ናቸው። እነዚህ ድህረ-ተፅዕኖዎች 15% የሚሆኑ ከሞት የሚተርፉ ልጆች ላይ ይከሰታሉ። አንዳንድ በልጆች ላይ የሚከሰት የመስማት ችግር ሊቀለበስ ይችላል። በአዋቂዎች ውስጥ ደግሞ ዋነኞቹ ችግሮች የመስማት ችግር (በ 14%) እና የግንዛቤ እክል (በ 10%) ናቸው።

 

ህክምናው ምን ይመስላል?

የማጅራት ገትር በሽታ ድንገተኛ ከሚባሉት የበሽታ አይነቶች ነው። የማጅራት ገትር በሽታ በ24 ሰዓታት ውስጥ ገዳይ ሊሆን ይችላል እና አስቸኳይ የህክምና ክትትል ይጠይቃል። በሽታውን በቤት ውስጥ ተከታትሎ ማዳን አይቻልም። አንድ ታካሚ የበሽታውን ምልክቶች ካሳየ እና የማጅራት ገትር በሽታ ጥርጣሬ ካለ፤ ለምርመራ ከአንጎል እና የህብለ ሰረሰር ፈሳሽ ከተወሰደ በኋላ አልያም ከሱ በፊት ሲቲ ስካን የሚነሳ ከሆነ የደም ተዋህሲያን ማራባት(blood cultures) ናሙና ከሰጠ በኋላ የፀረ-ተህዋሲያን ሕክምና ወዲያውኑ ማስጀመር ይመከራል። ነገር ግን የሚሰጠው የፀረ-ተህዋሲያን ሕክምና ጠቅላላ ለሁሉም የበሽታው አምጪ ተዋህሲያን የሚሆን ነው። ይሄም የመድኃኒት ምርጫ በታካሚው ዕድሜ እና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች ላይ በመመርኮዝ በጣም የታሰበ ነው። ከአንጎል እና የህብለ ሰረሰር ፈሳሽ ከተወሰደ ናሙና በሚገኘው መረጃ መሠረት የፀረ-ተህዋሲያን ሕክምናው ሊቀየርና ሊሻሻል ይችላል። አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ የፀረ-ተህዋሲያን ሕክምናው ከተጀመረ ብዙም ሳይቆይ ወይም በተመሳሳይ ጊዜ dexamethasone የተባለ መድኃኒት ሊሰጥ ይገባል።

 

የበሽታው መከላከያ መንገዶች ምን ምን ናቸው?

ክትባቶች ለተለመደው የባክቴሪያ ማጅራት ገትር በሽታ ጥሩ መከላከያ መንገዶች ናቸው። በmeningococcus፣ pneumococcus እንዲሁም haemophilus influenzae type b (Hib) ከሚከሰት የባክቴሪያ ማጅራት ገትር በሽታ የሚጠብቁ ክትባቶች አሉ።

የባክቴሪያ እና የቫይረስ ገትር በሽታ ከሰው ወደ ሰው ሊሰራጭ ይችላል። ስለዚህም የማጅራት ገትር ካለበት ሰው ጋር የሚኖሩ ከሆነ ወይም የቅርብ ግንኙነት ከነበርዎት የሚከተሉትን ማድረግ አለብዎት፦

  • ከሐኪምዎ ጋር ይነጋገሩ
  • እጅዎን አዘውትረው ይታጠቡ፤ በተለይም ከመብላትዎ በፊት።
  • አላግባብ ቅርበትን፤ ኩባያዎችን፣ መገልገያዎችን ወይም የጥርስ ብሩሾችን መጋራትን ማቆም

 

ዋቢዎች

  • https://www.who.int/news-room/fact-sheets/detail/meningitis#:~:text=Meningitis%20is%2
    0the%20inflammation%20of,%2C%20viruses%2C%20fungi%20and%20parasites.
  • UpToDate 2024
  • https://en.wikipedia.org/wiki/Meningitis
  • https://www.ncbi.nlm.nih.gov/pmc/articles/PMC4696686/#:~:text=Ethiopia%20has%20th
    e%20second-largest,World%20Health%20Organization%20(2)