በዶክተር ሜሮን ሀሰን

የህፃናት ህክምና እስፔሻሊስት

By Dr. Meiron Hassen, MD

Pediatrics and child health specialist

 

 

በተፈጥሮ አጀብ ከሚያሰኙ ሂደቶች ውስጥ የሰው ልጅ ከልጅ ወደ አዋቂነት የሚሸጋገርበት ሂደት ነው። አስቡት እስኪ ባንድ ወቅት ቴዲ አፍሮ እንኳን ገጥሞ ሊዘፍንልን “ጉጉ ጋጋ” ሲል እናቱ ተፍነክንካ ነበር፣ ደራርቱ ቱሉ እንዲህ ሮጣ ወርቅ በወርቅ ልታደርገን ቆማ እንድትሄድ የሰፈር ሁሉ ሰው “ዳዴ” እያለ ሲጎትታት ነበር ፣ ዲያቆን ሮዳስም እንዲህ ጠፈርን ሊያብራራልን ባንድ ወቅት በእጁ ተሸፍኖ አየሁህ ያለውን ሰው ከየት እንደመጣ ተገርሞ ሲደሳሰት ነበር። ስራው ግሩም ነው።

የሰው ልጅ ከጊዜ ወደጊዜ ለመኖር አስፈላጊ የሆኑ ለውጦችን በማህበረሰቡ፣ በአካባቢው እንዲሁም በውልደት በሚያገኛቸው ማንነት ላይ ተመርኩዞ ያሳያል። ይህ ሂደት በህፃናት ላይ በተለይም በመጀመሪያዎቹ አምስት አመታት በአስገራሚ ፍጥነት እንዲሁም ይዘት ይከናወናል። ሂደቱንም በህፃናት ህክምና ሳይንስ እድገት (growth) እና ብስለት (development) ብለን ይጠናል።

እድገት አካላዊ ሲሆን የአንድን ልጅ ክብደት፣ ቁመት እና የጭንቅላት ዙሪያን በመለካት ለእድሜ እንደሚመጥን ማወቅ ይቻላል። ይሄንንም ሃኪሞች በእድሜ እና በፆታ በአለም ጤና ድርጅት የተዘጋጁ ግራፎችን በመጠቀም ማወቅ ይችላሉ።

ብስለት ልጆች በእድሜ የተለያዩ ተግባራትን ለማከናዎን ሲሉ የሚያታዩት ለውጦች ናቸው። ይህንንም የተለያዩ ደረጃዎችን በጥልቀት በመገምገም ማወቅ ይቻላል። ለእያንዳንዱ ህፃን የብስለት ደረጃን ለመለየት በጡንቻው ማከናወን የሚችላቸው ተግባራት፣ የማየት እንዲሁም የመስማት ክህሎት፣ የቋንቋ ክህሎት እና ነገሮችን የማገናዘብ ችሎታ አንፃር ይታያል።

የአንድ ህፃን በተገቢው የእድገት እና የብስለት ደረጃ አለመገኘት በጥልቀት ሊመረመር እና ምክንያቱም ሊታወቅ ይገባል። ከወላጅ በተጨማሪ ሁላችንም እውይ ብለን የሚያማምሩ ጉንጫቸውን ከመሳም በዘለለ ለእድገታቸው እንዲሁም ለብስለት ደረጃቸው ትኩረት መስጠትና ተገቢውን እርዳታ እንዲያገኙ መልእክተኛ መሆን አለብን።

መከታተል ለምን አስፈለገ?

በዋናነት የአንድ ህፃን የደረጃ ዝግመት መንስኤ የተለያዩ በሽታዎችና የጤና እክሎች ሊሆኑ ይችላሉ። ይህም በጊዜ ችግሩን እንድናውቅ እና ለህፃናት ተገቢውን እርዳታ እንድናደርግ ይጠቅማል። ዝግመት እንደምልክት የምናይባቸውን የጤና እክሎች ከብዙ በጥቂቱ ለመጥቀስ ያክል

  • የምግብ እጥረት
  • ደም ማነስ
  • የተለያዩ የረጅም ጊዜ ኢንፌክሽኖች (ቲቢ ኤች አይ ቪ)
  • የልብ ህመም
  • ኦቲዝም
  • የተለያዩ የጡንቻ ስንፈቶች
  • የሆርሞን መዛባት እና ወዘተ ናቸው።

ከኛ ምን ይጠበቃል?

ለህፃናት እድገትና ብስለት ትኩረት መስጠት፣ የበለጠ ማወቅ እንዲሁም ላላወቁ ማሳወቅና ዝግመት ከታየ በሃኪም ምርመራ ማስደረግ።

ህፃናት የሚጠበቅባቸውን የእድገት ደረጃ እንዲበቁ ከተመጣጠነ ምግብና የጤና እርዳታ በተጨማሪ ጨዋታ፣ ፍቅር ቅርርብ እንደሚያስፈልጋቸው ማወቅና ማሳወቅ ፤ መተግበርም።

ህፃናት በተለያየ ፍጥነት ሊያድጉ ይችላሉ። ነገር ግን ሶስት ነገሮች ሊያሳስቡን ይገባል።

  • ለውጥ አለማሳየት
  • ከነበራቸው ደረጃ መቀነስ እና
  • ከእኩያቸው በከፍተኛ ደረጃ ዝቅ ማለት።

አሳሳቢ የዝግመት ምልክቶች

እድገትን ስንገመግም

ከህፃኑ/ኗ እድሜና ፆታ አንፃር ክብደቱ/ቷ ፣ ቁመቱ/ቷ ወይንም የጭንቅላቱ/ቷ ልኬት በፊት ከነበረው አለመሻሻል፣ መቀነስ ወይንም በሶስት ስታንዳርድ ከአማካዩ መቀነስ ( ሃኪም አማክሮ ማረጋገጥ ይቻላል)

ብስለትን ስንገመግም

በግርድፉ የጡንቻ ተግባራት ስንገመግም

በአራት ወሩ አንገቱ ራሱን መሸከም ካቃተው

በዘጠኝ ወሩ ያለድጋፍ መቀመጥ ካቃተው

በ12 ወሩ ተደግፎ ካልቆመ

በ18 ወሩ ራሱን ችሎ ካልሄደ

የጥቃቅን ጡንቻ ተግባራትን እንዲሁም የእይታ ክህሎቱን ስንገመግም

በ3 ወሩ የምታሳዩትን እቃ በአትኩሮት አይቶ ካልተከተለ

በ 6 ወሩ የምታሳዩትን እቃ ለመድረስ ካልጣረ

በ9 ወሩ በአንድ እጁ ያለን እቃ ወደ ሌላኛው ማቀበል ካቃተው

በ12 ወሩ ወለል ላይ የወደቁ ጥቃቅን ነገሮችን በጣቶቹ ቆንጥጦ ማንሳት ካቃተው

የማህበራዊ ብስለታቸውን ስንገመግም

በ8 ሳምንት ፈገግታ ካላሳዩ

በአስር ወራቸው ባዳ ካልፈሩ

በ18 ወራቸው በማንኪያ ራሳቸውን መመገብ ካልቻሉ

ከ ሁለት እስከ ሶስት አመታቸው በጋራ ለመጫወት ፍላጎት ካላሳዩ

የመስማትና የመናገር ብስለታቸው ሲገመገም

በ7 ወራቸው ድምፅ ማውጣት ካልጀመሩ

በ 18 ወራቸው 6 ትርጉም ያላቸው ቃላት ካልመሰረቱ

በ 2 ዓመታቸው ሁለት ቃላት እንዲሁም በ 3 አመታቸው ሶስት ቃላት መመስረት ካልቻሉ

እንግዲህ ስራ ላበዛባችሁ ነው። ህፃነትን ስታቅፉ ያንን ውብ ፈገግታቸውን ስታዩ ማር ማር የሚለውን አንደበታቸውን ስትሰሙ እያስተዋላችሁ። አንድን ህፃን ማሳደግ መንደር ሙሉ ሰው ርብርብ ያስፈልጋል። ምን አልባትም እድገቱ ህይወቱን የሚታደግ ምልክት እየሰጣችሁ ይሆናል። ስለ ልጅነት እና ሂደቱ ይህን ካወቁ ያሳውቁ ፣ የማህበረሰባዊ ግዴታዎን ይወጡ።

 

#አሳዳጊ ነን

የጤና ወግ

ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።

የጤና ወግን በነዚህሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።

https://linktr.ee/Yetena_Weg