Written by-  Dr. Bethlehem Tesfasilassie Kibrom

Reviewed by-  Dr. Yodit Abraham Yaynishet. Radiologist AAU Department of Radiology

 

አንድ ሰው ታሞ ለህክምና ወደ ጤና ተቋም በሚሄድበት ጊዜ ስለበሽታው ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት እና በአይን የማይታዩትን የውስጥ ሰውነት አካላት ለማየት የተለያዩ መመርመሪያ መሳሪያዎች በሀኪሙ ወይም በጤና ባለሙያው ይታዘዛሉ። ከነዚህም ውስጥ አልትራሳውንድ፣ ራጅ (ኤክስ ሬይ/X-ray)፣ ኤም አር አይ (MRI) እና ሲቲ ስካን (CT Scan) ናቸው።

 

ራጅ (ኤክስ-ሬይ/X-ray )

 

  • በጣም የተለመደ እና ከብዙ አመታት በፊት የነበረ የመመርመሪያ መሳሪያ ነው።
  • የአጥንትን እና የተወሰኑ የአካል ክፍሎችን ምስል ለማንሳት አነስተኛ መጠን ያለው ጨረር ይጠቀማል።
  • የሚጠቀመው ጨረር አነስተኛ ከመሆኑ የተነሳ የመመርመር ጥቅሙ ከጉዳቱ ይበልጣል።
  • የምርመራ ሂደቱ ፈጣን ነው ፤ አብዛኛውን ጊዜ ጥቂት ሰከንዶች ብቻ ይወስዳል።
  • የኤክስሬይ ማሽኑ ምስሉን በሚያነሳበት ጊዜ መቆም ወይም መተኛት ሊኖርብዎ ይችላል።

 

አልትራ ሳውንድ (Ultrasound)

  • አልትራሳውንድ የሰውነትዎ የውስጠኛውን ክፍል ምስል ለመፍጠር የድምፅ ሞገዶችን ይጠቀማል።
  • አልትራሳውንድ አብዛኛውን ጊዜ በእርግዝና ወቅት ጥቅም ላይ ይውላል። በተጨማሪም እንደ ጉበት፣ ኩላሊት እና ልብ ያሉ የአካል ክፍሎችን ለመመልከት ጠቃሚ ነው።
  • የምርመራ ሂደቱ ምንም ህመም የለውም። ምርመራው የሚያስፈልግበት ቦታ ቆዳዎ ላይ የሚቀባ ቅባት መሰል ፈሳሽ (ጄል) እና ትራንስዱሰር የሚባል ትንሽ መሳሪያ በመታገዝ የሚደረግ ምርመራ ነው።
  • አልትራሳውንድ ጨረር ስለማይጠቀም ብዙውን ጊዜ ለነፍሰ ጡር ሴቶች እና ህፃናት ተመራጭ ነው።

 

ኤም አር አይ(MRI)

 

  • ስለ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎች እና ነርቮች ጠለቅ ያለ ምስል እና መረጃን ለማግኘት ኃይለኛ ማግኔቶችን እና የሬዲዮ ሞገዶችን ይጠቀማል።
  • አንጎል፣ ህብረ ሰረሰርን፣ አከርካሪ አጥንትን፣ ጡንቻዎችን እና መገጣጠሚያዎች ለመመልከት ተስማሚ ነው።
  • የምርመራ ሂደቱ ከ 30 ደቂቃ እስከ አንድ ሰዓት ሊወስድ ይችላል። ቱቦ በሚመስል ማሽን ውስጥ ሳይንቀሳቀሱ መተኛት ያስፈልግዎታልት። የሚረብሽ ድምፅ ከማሽኑ ሊወጣ ስለሚችል አይጨነቁ። ድማፁን የሚቀንሱ ጆሮ ላይ የሚደረጉ መሳሪያዎች ይሰጥዎታል። ለአንዳንድ ለህፃናት እና ታካሚዎች ምርመራው በትክክል አንዲጠናቀቅ የሚያረጋጉ መድሀኒቶች ሊሰጡም ይችላሉ።
  • የበለጠ ጥራት ያለው ምስል እንዲገኝ ምርመራው ከተጀመረ በኋላ አይንቀሳቀሱ።
  • እንደአስፈላጊነቱ ከምስሉ የሚገኘውን መረጃ ለመጨመር የሚሰጡ መድሀኒቶች (contrast) አሉ።
  • አደጋን ለመከላከል ብረት ነክ የሆኑ ጌጣጌጦች እና በተለያዮ የበሽታ ምክንያት ከብረት የተሰሩ የህክምና ቁሶች በሰውነቶ ውስጥ ካለ ይህን ምርመራ ከማድረጎ በፊት ለህክምና ባለሙያዎት ያሳውቁ።

 

ሲቲ ስካ (CT Scan)

  • ይህ መሳሪያ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ብዙ የኤክስሬይ (ራጅ) ምስሎችን ወስዶ አንድ ላይ በማጣመር ጥልቅ የሆነ ሰውነት ምስሎችን ይፈጥራል።
  • ከራጅ አንፃር የበለጠ ጨረርን ይጠቀማል።
  • ከኤም አር አይ አንፃር የትቦ መሰል አካሉ የወደውስጥ ስፋት አጠር ያለ ነው።
  • የምርመራ ሂደቱ ጥቂት ደቂቃዎችን ብቻ ይወስዳል። መተኛት ይኖርቦታል።
  • የበለጠ ጥራት ያለው ምስል እንዲገኝ ምርመራው ከተጀመረ በኋላ አይንቀሳቀሱ።
  • እንደአስፈላጊነቱ ከምስሉ የሚገኘውን መረጃ ለመጨመር ምርመራው ከመጀመሩ በፊት ወይም ከተጀመረ በኋላ የሚሰጡ መድሀኒቶች (contrast) አሉ።

 

አንዳንድ የምርመራዎች ፅንስ ላይ ከሚያመጡት ጉዳት የተነሳ ለነፍሰጡር ሴቶች አይመከሩም። ምርመራው እጅግ አስፈላጊ ከሆነ ተገቢ ጥንቃቄ ተደርጎ ይከናወናል። ስለዚህም ከእርግዝና ጋር የተያያዘ መረጃ ለጤና ባለሙያ ማሳወቅ ይገባል።  በመጨረሻም ምርመራ በሚደረግበት ጊዜ በጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ መመሪያዎችን መከተል አስፈላጊ ነው ። ምርመራዎቹ በሚታዙበት ወቅት ለሚኖረው ማንኛውም ጥያቄ የህክምና ባሙያዎትን ያማክሩ።