Written by – Mahtot Leykun Sisay (Optometrist)
Reviewed/Approved by: Alemayehu Woldeyes,MD,MSc(Consultant ophthalmologist)
Myopia: A Silent and Growing Epidemic
በርቀት የማየት ችግር ፡ ጸጥ ያለ እና እያደገ የመጣ ወረርሽኝ
👉 ከርቀት የማየት ችግር / Myopia /Shortsightedness/ ምንድን ነው ?
ከሩቅ የማየት ችግር የምንለው ቅርብ ያሉ ነገሮችን በጥሩ ሁኔታ ማየት መቻል ነገር ግን ሩቅ ያለውን ለማየት መቸገር ወይም መደብዘዝ ማለት ነው፡፡ይህ የሚከሰተውም የአይን መጠን ወይም የብርሃን አቅጣጫ የማስቀየር ሃይል ከፍተኛ ሲሆን ተንጸባርቆ የመጣውን የብርሃን በተፈለገው መጠን ረቲና ላይ/ብርሃንን ተቀብሎ ምስልን ወደ አእምሮ የሚልክ የአይን አካል/ ላይ ባለማረፉ ነው፡፡
ወደ ዓይን ውስጥ የሚገቡት የብርሃን ጨረሮች አእምሮ ላይ ምስል ለመፍጠር ከሬቲና ላይ ማረፍ አለባቸው፡፡ በርቀት የማየት ችግር ያለባቸው ሰዎች ላይ ግን ምስል ረቲና ፊት ለፊት ላይ ይፈጠራል። ይህ ብዙውን ጊዜ የዓይን ኳስ ከፊት ወደ ኋላ በጣም ስለሚረዝም፣ ወይንም ከመጠን በላይ በተጠማዘዘ የአይን ብሌን እና/ወይም ከፍተኛ ሃይል ያለው የአይን ሌንስ ሊከሰት ይችላል።በሌላ ስምም በቅርብ የማየት ችሎታም ተብሎ ይጠራል።
👉 በርቀት የማየት ችግር ምን ያህል ሰው ያጠቃል ?
ከርቀት የማየት ችግር በአለም ላይ እያደገ መምጣቱን የሚያሳዩ መረጃዎች እየጨመሩ ሲሆን በቅርቡ በተደረገ ጥናት በአማካይ በአለም ላይ 30 በመቶው የዚህ ችግር ሰለባ እንደሆነ እና እ.ኤ.አ በ 2050 በርቀት የማየት ችግር ያለባቸው ሰዎች 4.8 ቢሊዮን (49.8% የዓለም ሕዝብ) ይደርሳል ተብሎ ይገመታል።
ይህ ችግር የግለሰቦችን የኑሮ ጥራት እና ኢኮኖሚያዊ ጤንነት የሚጎዳ ጸጥ ያለ እና እየጨመረ የመጣ አሳሳቢ የአለም ወረርሽኝ ጉዳይ እየሆነ ነው። በተሰራጨው መረጃ እና በአለም አቀፍ ደረጃ ካለው የህዝብ ብዛት አንጻር ሲታይ ይህ የርቀት እይታ ችግር በ 2050 ከአለም ህዝብ ግማሽ ያህሉን እንደሚያጠቃ ይገመታል፡፡
በ2006 እ.ኤ.አ የተሰራው ሃገራዊ ጥናት እንደሚያሳየው የዓይነ ስውርነት ስርጭት በሀገራችን ኢትዮጵያ 1.6% (1.1% ለከተማ እና 1.6% ለገጠር ህዝብ) ሲሆን ይህም ማለት ከ100 ስዎች መካከል ወደ 1.6 የሚሆኑት 3 ሜትር ርቀት ላይ ሆነው ጣት መቁጠር የማይችሉበት ደረጃ ላይ ናቸው ማለት ነው፡፡ ዝቅተኛ እይታ(low vision) ያላቸው ስዎች ስርጭት ደግሞ 3.7% (2.6% ለከተማ እና 3.8% ለገጠር ህዝብ) ነው ይህም ማለት ከ100 ስዎች መካከል ወደ 4 የሚጠጉት ዝቅተኛ የእይታ ደረጃ ዓላቸው ማለት ነው።
👉 የበሽታው መንስኤ ምንድነው ?
- የዓይን ኳስ፣ የአይን ብሌን/ ትልቅ መሆን
- በዘር የሚተላለፍ ወይም የቤተሰብ ውርስ / ይህ በብዛት የሚታየው ከ8-12 አመት የእድሜ ክልል ውስጥ ነው
- እድሜ እየጨመረ ሲሄድ
- ያለጊዜው መወለድ
- የአይን ብሌን/ ኮርኒያ በጣም ጠመዝማዛ መሆን/steeper cornea/
👉 ለርቀት የማየት ችግር ተጋላጭ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው ?
- የጄኔቲክ ምክንያቶች/ በቤተሰብ የሚተላለፍ
- ለረዥም ሰአት የቅርብ ስራዎችን ማከናወን
- በወጣትነት ጊዜ ከቤት ውጭ እንቅስቃሴዎች አለመኖር
- የከተማ መስፋፋት እና አመጋገብን ጨምሮ (ከፍ ያለ የሳቹሬትድ ስብ እና ኮሌስትሮል መመገብ)የአካባቢ ሁኔታዎች በማይዮፒያ እና በአይምሮአዊ ግስጋሴ ውስጥ ስላላቸው ሚና ተመርምረዋል።
👉 ህመምተኛው ምን ምን ምልክቶችን ያሳያል?
- ከሩቅ ያሉ ነገሮችን ሲያዩ መደብዘዝ
- ብዥ ያለ የርቀት እይታ.
- ልጆች ከቴሌቭዥን እና ከኮምፒዩተር ጋር ተቀምጠው ወይም የንባብ ቁሳቁሶችን በቅርበት ሲይዙ ይስተዋላል
- ለማየት ሲሞክሩ የአይን ቆብን ማርገብገብ ወይም በከፊል መዝጋት
- ራስ ምታት
- ተሽከርካሪ በሚያሽከረክሩበት ጊዜ የማየት ችግር (በተለይ ማታ)
👉 ስንት አይነት በርቀት የማየት ችግር አይነቶች አሉ ?
በዲግሪ (በመጠን) መሰረት፣ ዝቅተኛ በርቀት የማየት ችግር (–2 diopter እና ያነሰ )
መካከለኛ በርቀት የማየት ችግር (በ -2 እና -6 diopter መካከል)
ከፍተኛ በርቀት የማየት ችግር(High myopia)-6 diopter እና ከዚያ በላይ እንዲሁም በየአመቱ የሚጨምር
በእድሜ መሰረት፡የተወለደ በርቀት የማየት ችግር(congenital Myopia) (በተወለደበት እና በጨቅላነታቸው ጊዜ የሚቆይ)
የወጣትነት በርቀት የማየት ችግር (ከ 20 አመት በታች)
የአዋቂዎች በርቀት የማየት ችግር (ከ20 – 40 አመት)
ዘግይቶ የሚጀምር የማየት ችግር (ከ 40 አመት በላይ)
👉 ምን ምን ምርመራዎች ይታዘዛሉ ?
በተለያዩ የእይታ ማጣሪያ ሂደቶች ማለትም በተለመደው የዓይን ምርመራ ወይም የእይታ ምርመራ ወቅት /vision screening/ የማየት ችሎታ ሲቀንስ ይስተዋላል፡፡
ምንም እንኳን እንደ photo-screening እና Auto-refraction ያሉ የእይታ ማጣሪያ ቴክኒኮች ርቀት የማየት ችግር ለይተው ማወቅ ቢችሉም የመነጸር ማዘዣው በትክክል ሊሰላ የሚችለው ግን ሪፍራክሽን በመጠቀም ነው።
👉 ህክምናው ምን ይመስላል ?
- ሩቅ የማየት ችግር ለማከም ምረመራ ከተደረገ በኋላ የሚታዘዙ የአይን መነፃሮች
- በአይን ውስጥ የምትደረግ ሌንስ ማድረግ (contact lenses)
- ቀዶ ህክምና
👉 ባልተስተካከለ ርቀት የማየት ችግር ምክንያት የሚመጡ መዘዞች ምንድን ናቸው ?
- ዝቅተኛ እይታ(low vision)
- የሬቲና መላቀቅ/(Retinal Detachment)
- ማኩላር ዲጄነሬሽን (የዕይታ ድራብ መሳሳት)
- ዓይነ ስውርነት/loss of vision/ ሊያስከትል ይችላል
👉 የበሽታው መከላከያ መንገዶች ምን ምን ናቸው?
- ስልክና ኮምፒዩተር የመሰሉ የቅርብ ዕይታ መቀነስ
- ልጆች በቂ ፀሐይ እንዲያገኙ ወይም ከቤት ውጪ እንዲጫወቱ ማድረግ።
- መነጽር በማድረግ እንዳይባባስ ማድረግ ይቻላል።
‘’የዓይናችን እይታ የህይወትን ውበት እንድናይ የሚያደርግ ትልቅ ስጦታ ነው፤ የአይንዎን ጤና እንደ ቀላል ነገር አይውሰዱ’’
ዋቢ
https://www.ncbi.nlm.nih.gov/pmc/articles/PMC8759558/
https://www.ncbi.nlm.nih.gov/pmc/articles/PMC4675264/
https://www.aaojournal.org/article/s0161-6420(16)00025-7/fulltext
The Basic and Clinical Science Course (BCSC) Retina and Vitreous, Clinical optics 2021 edition
https://www.medscape.com/viewarticle/977201
American academy of Ophthalmology -Eyewiki, https://aao.org/