Written by አናን አሰፋ(ጅማ ዩኒቨርሲቲ C2 ተማሪ)
Reviewed by ዶ/ር ሰላማዊት ሙሉቀን ( Dermatologist)
ቲንያ ምንድነዉ?
ቲንያ የፈንገስ ኢንፌክሽን አይነት ሲሆን በፈንገስ አማካኝነት ይከሰታል ። በዋናነት ቆዳን ፣ ፀጉርን እና ጥፍርን ያጠቃል ። ይህ የቆዳ በሽታ የሚከሰትባቸው የሰውነት ክፍሎች ላይ በመመስረት የተለያዩ ስያሜዎች አሉት ። ለምሳሌ :- በጭንቅላት ቆዳ እና በፀጉር ላይ የሚከሰተው ቲንያ ካፒቲስ ይባላል ።በሀገራችን ቆረቆር በመባል ይታወቃል ። ቲንያ ኮርፖሪስ ደግሞ በሰውነት ቆዳ ላይ የሚከሰት ነው ። ጭርት ተብሎ በተለምዶ የሚጠራው በሽታ ነው ። በጥፍር ላይ የሚከሰተው የቲንያ አይነት ደግሞ ቲንያ አንገም ወይም በተለምዶ ጥፍረ መጥምጥ ተብሎ የሚጠራው ነው። ሌላው የቲንያ አይነት ደግሞ ቲንያ ክሩሪስ በመባል ይታወቃል ።ይህም በጭን እና በብልት አካባቢ በሚገኘው ቆዳ ላይ የሚወጣ ነው ።ከሌሎች የቲንያ አይነቶች፡ ቲንያ ፋሼ – ፊትን የሚያጠቃ ፤ ቲኒያ ባርቤ – ጺምን የሚያጠቃ ፤ ቲኒያ ፔዲስ – የእግር ጣቶችን መካከል እና ዉስጥ እግርን የሚያጠቃ፤ ቲኒያ ማነም – የእጅ መዳፍን የሚያጠቃ ተጠቃሾች ናቸው፡።
በበሽታው ምን ያህል ሰዎች ይጠቃሉ?
ይህ የቆዳ ፈንገስ በሽታ በአለም ላይ በስፋት ይገኛል ።በዋናነት ግን ሞቃት እና እርጥበታማ የአየር ንብረት ያላቸው ቦታዎች ላይ ተንሰራፍቶ ይገኛል ። በሀገራችን ኢትዮጵያም አብዛኛዎቹ ክፍሎች ይገኛል ። ከቲንያ አይነቶች መሀከል ቲንያ ካፒቲስ ወይም ቆረቆር በዋናነት እድሜያቸው ለትምህርት የደረሰ ህፃናት( ከ ስት እስከ አስራ አምስት የሆኑ ህጻናት) ላይ በስፋት እንደሚታይ ጥናቶች ያመለክታሉ ።
የበሽታው መንስኤ ምንድን ነው?
የዚህ በሽታ ዋነኛ መንስኤ ደርማቶፋይት የተባለ የፈንገስ ዝርያ ነው ። ደርማቶፋይት በሚባለው ፈንገስ የላይኛዉን የቆዳ ክፍሎች ማለትም ቆዳን ራሱን፣ ጸጉርን እና ጥፍርን በሚያጠቃ ሲሆን ይህ ፈንገስ በአፈር ውስጥ ፣ በእንስሳት እና በሰዎች ላይ ሊገኝ ይችላል ። እንደ አብዛኞዎቹ የፈንገስ ዝርያዎች ደርማቶፋይት ሞቃት እና እርጥበት ያለበትን ቦታ ይመርጣል ። በሰውነት ላይም በእግር ጣቶች መሀከል ፣ በጭን አካባቢ ያሉ ቦታዎችን ይመርጣል ።ከዚህም በተጨማሪ በርካታ የሰውነት ክፍሎችን በተናጥል ወይም በጋራ ሊያጠቃ ይችላል ።
ለበሽታው ተጋላጭ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ምንድናቸው?
ይህ የቆዳ በሽታ ማንኛውንም ሰው ሊያጠቃ ይችላል ። ነገር ግን የሰውነት በሽታን የመከላከል አቅም የሚያደክሙ ህመሞች ያለባቸው ሰዎችን በይበልጥ ሊጎዳ ይችላል ። ከእነዚህም መሀከል የስኳር ህሙማን እና ከHIV/AIDS ጋር የሚኖሩ ሰዎች ተጠቃሽ ናቸው ።ከዚህ በተጨማሪ እድሜ ፣ ዝቅተኛ የኑሮ ህኔታ ፣ የተፋፈገ እና ሰው የበዛበት የኑሮ ሁኔታ ፣ የግል ንህጽናን ያለመጠበቅ እና የሰውነት በሽታ የመከላከል አቅም የሚቀንሱ መድሃኒቶች ለቲንያ ያጋልጣሉ።
ምልክቶቹ ምንድናቸው?
ይህ በሽታ እንደሚያጠቃው የሰውነት ክፍል አይነት የተለያየ ምልክት ሊያሳይ ይችላል ።
ቲንያ ኮርፖሪስ – ጭርት :- በሰውነት ቆዳ ላይ ሲከሰት ማሳከክ ፣ የቆዳ መላላጥ እና መድረቅ ፣ መሃሉ እየጠፋ ዳሩ እየሰፋ የሚሄድ ክብ ቅርፅ የያዘ ቀይ ወይም ነጣ ያለ የቆዳ ምልክት ማውጣትን ሊያሳይ ይችላል ።
ቲንያ ካፒቲስ – ቆረቆር :- የፀጉር መሳሳት ፣ መነቃቀል ወይም መርገፍ ፣ ማሳከክ እና የቆዳ መፈርፈር ፣ የጭንቅላት ቆዳ ቁስለት እና አልፎ አልፎ ደግሞ ጊዜያዊ እና ቋሚ ጠባሳ ሊያስከትል ይችላል።
ቲንያ ካፕቲስ በምልክቶች ላይ በመመስረት ለአራት አይነት ይከፈላል
እንዚህም፡
– ኬሪዮን ፡ የጓጎሉ እና ቀላ ያሉ እብጠቶች በራስ ቅል ላይ ያስከትላል። መግል የሚይዝ ሲሆን ሲድን ቋሚ የሆነ ጠባሳ ሊያስከትል ይችላል
– ግሬይ ፓች ፡ ይህ በአብዛኛው የምንመለከተው አይነት ሲሆን፣ ነጫጭ የሚፈረፈሩ የቆዳ ለውጦችን ራስ ቅል ላይ ያስከትላል። በተጫማሪ የተጎዳው ቦታ ላይ የጸጉር መሳሳት እና መመለጥ ሊኖር ይችላል።
– ብላክ ዶት፡ ይህ የቲንያ አይነት ጸጉርን በመነቃቀል እና ጥቋቁር ነጠብጣቦችን በመፍጠር ይታወቃል
– ፋቨስ ፡ ጸጉርን የሚያጣብቅ እና ቢጫ ደረቅ ክርታስ የሚፈጥር አይነት ነው።
ቲንያ ፔዲስ :- በእግር ላይ የሚከሰተው ይህ የቲንያ አይነት በእግር ጣቶች መሀከል እና በዉስጥ እግር አካባቢ የቆዳ መላላጥ የቆዳ መድረቅና መሰነጣጠቅ ምልክቶቹ ናቸው ።
ቲንያ ፋሼ :- የፊት ቆዳን የሚያጠቃ የቲንያ አይነት ነው ። ምልክቶቹም የቆዳ መቅላትና መላላጥ ፣ ክብ የሆነ የሚያሳክክ የቆዳ ሽፍታ፣ ፀሀይ ሲነካው የመቆጥቆጥ ስሜት፣ ነጣ ብሎ የራሰ ቁስለት እና መጥፎ ጠረን ናቸው ።
ቲንያ አንጉየም – ጥፍረ መጥምጥ :- የጥፍርን ተፈጥሮአዊ ይዘት እና ቀለም በመቀየር ከመጠን በላይ የጠነከረ እና ወፍራም እንዲሆን ያደርጋል ።
የቲንያ ምርመራ እና ህክምና
ቲንያ የቆዳ ፈንገስ በሽታ በቀላል ምርመራ መታወቅ ይችላል ።አብዛኛውን ጊዜ ሀኪሞች ህመምተኛው ካሳያቸው ምልክቶችእና በ አካላዊ ምርመራ በመነሳት በሽታውን በቀላሉ ይለያሉ ። በተጨማሪም ከታመመው የሰውነት ክፍል ላይ የቆዳ /የፀጉር ወይም የጥፍር ናሙና በመውሰድና ኬ ኦ ኤች (KOH) የተባለ ኬሚካል በመጠቀም በአጉሊ መነጽር ፈንገሱን በመመልከት ማረጋገጥ ይቻላል ።
ለዚህ በሽታ ህክምና የሚውሉ መድኃኒቶች በተለያየ መልኩ ተዘጋጅተው ይገኛሉ ።ለምሳሌ የሚቀባ ክሬም ፣ የሚዋጥ ክኒን ወይም ጸረ-ፈንገስ የሆኑ የፀጉር መታጠቢያ ሻምፑዎች ተጠቃሽ ናቸው ።እንደ ቆዳ ሃኪሙ ዉሳኔ ህክምናው እነደተከሰተበት ቦታ እና መጠን ሊለያይ ይችላል። ብዙ ጊዜ ቲኒያ ክካፒቲስ እና ቲኒያ አንገም በሚዋጥ ኪኒን መታከም ይኖርባቸዋል።
የበሽታው መተላለፊያና መከላከያ መንገዶች
የሆነ የሚያሳክክ የቆዳ ሽፍታ
የቲንያ መተላለፊያ መንገዶች በአይነቱ ላይ ተመስርቶ ይለያያሉ፣ አብዛኛውን ጊዜ የሚስተዋሉት የመተላለፊያ መንገዶች ፡ የቆዳ ንክኪ፣ ልብስ፣ ማበጠሪያ ፣ኮፊያ እና ትራስን መጋራት ፣ ጫማ እና ካልሲ መጋራት ናቸው።
በመሆኑም በተቻለ መጠን እንደዚህ አይነት ስፍራዎችን ባለመጠቀም ፣ ንፁህ ፎጣዎችን በመጠቀም ና ከሌሎች ሰዎች ጋር ባለመጋራት ከበሽታው ራስን መከላከል ይቻላል ። በተጨማሪ ደግሞ የግል እና የአካባቢ ንፅህናን መጠበቅ ፣ ሰውነትን ከታጠቡ በኋላ በተለይም በመገጣጠሚያ አካባቢዎችና በጣቶች መሀከል በሚገባ ማደራረቅ ለፈንገሱ ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጠር ያደርጋል ። ከዚህ ሌላ የበሽታውን ምልክቶች ሲመለከቱ የህክምና ባለሙያ ጋር በመቅረብ ተገቢውን ህክምና መውሰድ አስፈላጊ ነው ።
Reference
Davidson’s principles and practice of medicine 23rd edition
www.ncbi.nlm.nih.gov