በዶክተር ቤተልሄም ተስፋስላሴ(ጠቅላላ ሀኪም) By Dr.Bethlehem Tesfaselassie General Practitioner

Reviewed by Dr Gelila Sintayehu, Internist

 

 

ሌራ(Cholera) ምንድን ነው?

  •  ኮሌራ ቪብሪዮ ኮሌራ በሚባል መርዛማ ባክቴሪያ የሚመጣ የአንጀት ኢንፌክሽን ሲሆን አጣዳፊ ተቅማጥ ያስከትላል።
  • በአለም ዙሪያ ከ1.3 እስከ 4 ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎች በየአመቱ በኮሌራ ይያዛሉ ። ከ21,000 እስከ 143,000 የሚደርሱ ሰዎች ደግሞ በዚህ በሽታ ይሞታሉ።

 

ኮሌራ እንዴት ይተላለፋል?

  • ኮሌራ የሚተላለፈው በኮሌራ ባክቴሪያ የተበከለ ውሃ ስንጠጣ ወይም ምግብ ስንመገብ ሲሆን ይህም የሚከሰተው የምንጠቀመው ውሃና ምግብ በበሽታው በተያዘ ሰው ሰገራ ሲበከል ነው።
  • ኮሌራ የውሃ እጥረት እና የንፅህና ጉድለት ባለባቸው ቦታዎች የመከሰቱና የመዛመት እድሉ ሰፊ ነው።

 

የኮሌራ ምልክቶች ምንድን ናቸው?

የኮሌራ በሽታ ያለባቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ ቀለል ያሉ ምልክቶች ያሳያሉ ወይም ምንም ምልክት አይኖራቸውም። ነገር ግን ኮሌራ ከባድ ሊሆን ይችላል። በግምት ኮሌራ ከያዛቸው 10 ሰዎች ውስጥ አንዱ ከባድ ምልክት ያሳያል። አንድ ሰው የተበከለ ምግብ ከበላ ወይም ውኃ ከጠጣ በኋላ ምልክቶቹን ለማሳየት ከ12 ሰዓት እስከ 5 ቀናት ይፈጅበታል።

ምልክቶቹም

  • በዋናነት ተቅማጥ እና ማስመለስ ሲሆኑ ከባድ የሆነ የኮሌራ ህመም የያዛቸው ሰዎች መጥፎ ጠረን ያለውና የ”ሩዝ ውሃ” የመሰለ ተቅማጥ ይኖራቸዋል።
  • ተቅማጥና ትውከቱ ቀጣይነት ያለው ከሆነ ደግሞ ከፍተኛ የሰውነት ፈሳሽ መሟጠጥ፣ ፈጣን የልብ ምት፣ ዝቅተኛ የደም ግፊት፣ከዚህም ጋር ተያይዞ የኩላሊት መጎዳት፣ ንቃት መቀነስ (አለመንቃት) እና ሞት ያስከትላል።
  • አልፎ አልፎ የሆድ ቁርጠት ቢኖራቸውም ብዙዎቹ በኮሌራ የተያዙ ሰዎች ትኩሳት አይታይባቸውም።

 

የኮሌራ ምርመራ ምን ይመስላል?

  • የኮሌራ በሽታን በላብራቶሪ በሚደረግ የሰገራ ምርመራ መለየት ይቻላል።
  • የላብራቶሪ ምርመራ በሌለባቸው አካባቢዎች የአለም ጤና ድርጅት ባወጣው መስፈርት መሰረት ታካሚው በሚያሳያቸው ምልክቶች እና በአካባቢው ባለው የበሽታው ስርጭት በግምት ውስጥ በማስገባት ህክምናው ይደረጋል።

እኔ ወይም የማውቀው ሰው ከታመመ ምን ማድረግ አለብኝ?

  • እርስዎ ወይም የቤተሰብዎ አባል ኮሌራ እንዳለብዎ ካሰቡ ወዲያውኑ የህክምና እርዳታ ያግኙ። የሰውነት ፈሳሸ መሟጠጥ ፈጣን ሊሆን ስለሚችል ፈሳሽ በመውሰድ መተካት አስፈላጊ ነው።
  • ORS(ኦራኤስ) ካለዎት ወዲያውኑ መውሰድ ይጀምሩ። የሕክምና እርዳታ እስከሚያገኙ ድረስ ORS መጠጣትዎን ይቀጥሉ።
  • አንድ ከረጢት ORS(ኦራኤስ) ፈልቶ በቀዘቀዘ ንፁህ ወይም የታሸገ 1ሊትር ውሃ ውስጥ በመበጥበጥ ማዘጋጀት ይችላሉ።
  • አንድ ህፃን ተቅማጥ ካለበት ጡት ማጥባትዎን ይቀጥሉ።

 

ህክምናዎቹ ምንድን ናቸው? 

  • ኮሌራ በልጆችም ሆነ በአዋቂዎች ላይ ጉዳት የሚያደርስ ከመሆኑም በላይ በበሽታው ተይዘው ከፍተኛ ተቅማጥ ያላቸውን ሰዎች ሕክምና ካልተደረገላቸው በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ሊገድል ይችላል። ነገር ግን ቶሎ ሕክምና ሲደረግላቸው አብዛኛውን ጊዜ ዘላቂ ጉዳት ሳያስከትልባቸው ያገግማሉ።
  • የኮሌራ ዋነኛው ህክምና የሰውነትን ፈሳሽ መተካት ነው። ይህም በORS(ኦራኤስ) ወይም አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ በደም ስር በሚሰጡ ፈሳሾች ይከናወናል።
  • ከባድ ምልክት ላላቸው ሰዎች ፀረ-ባክቴርያ መድሀኒቶች ሊሰጡ ይችላሉ።
  • ከ 5 አመት በታች ላሉ ህፃናት የዚንክ እንክብል ይሰጣቸዋል። ይህም የበሽታውን ጊዜ ለማሳጠር እና ከሌሎች የተቅማጥ በሽታዎች ለመከላከል ይጠቅማቸዋል።
  • የኮሌራ ሕሙማን አብዛኛውን ጊዜ ከሕመማቸው ካገገሙ በኋላ የኮሌራ ባክቴሪያ ተሸካሚዎች ባይሆኑም እንደገና ከተጋለጡ ይታመማሉ።

 

ኮሌራን እንዴት መከላከል ይችላሉ?

  • እጅዎን ምግብ ከማብሰልዎ በፊት፣ ልጆችዎን ከመመገብዎ በፊት፣ ሽንት ቤት ከተጠቀሙ በኋላ (ወይም ልጅዎን ሽንት ቤት አስጠቅመው ካጸዳዱ በኋላ) ፣ የታመመን ሰው ከተንከባከቡ እና/ወይም ከነኩ በኋላ በሳሙና እና በንፁህ ውሃ ይታጠቡ።
  • ንጹህ ውሃ መጠጣት እና መጠቀምዎን ያረጋግጡ።
  • ውሃዎ ደህንነቱ የተጠበቀ ላይሆን ይችላል ብለው የሚያስቡ ከሆነ በውሃ ማከምያ ኬሚካሎች አክመው ይጠቀሙ።
  • ምግብን በደንብ ያብስሉ፣ ይሸፍኑ ፣ በትኩሱ ይመገቡ።
  • ያልበሰሉ ምግቦችን አይመገቡ።
  • የውሃ ማከሚያ ምርት ከሌለ ማፍላት ውሃን አስተማማኝ ለማድረግ ውጤታማ መንገድ ነው። ውሃውን ለ 1 ደቂቃ ያህል በማፍላት በንፁህ እቃ አጠራቅመው በ24 ሰዓታት ውስጥ ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ ጥቅም ላይ ያውሉ።
  • ከቧንቧ የሚወጣ ውሃ እና በከረጢት የሚሸጡት በረዶዎች የተበከሉ ሊሆን ስለሚችሉ አክሞ መጠቀም ወይም ፈፅሞ አለመጠቀም።
  • የሽንት ቤት ንፅህናን መጠበቅ። ባክቴሪያው እንዳይሰራጭ ለመከላከል ከታመሙ እና ከሌሎች ሰዎች የሚወጣው የሽንት ቤት ፍሳሽና ቆሻሻ አካባቢን፣ ውኃንና ምግብን እንዳይበክል በጥንቃቄ ማስወገድ።

 

ምንጮች

Cholera – Vibrio cholerae infection | Cholera | CDC

Cholera (who.int)

 

የጤና ወግ

ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።

የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።

https://linktr.ee/Yetena_Weg