የስኳር በሽታ የሚያመጣውን የኩላሊት ህመም መከላከልን በተመለከተ  ፡ 10 ጥያቄዎች እና መልሶቻችው

የኩላሊት ስራ ማቆምና (ሙሉ ለሙሉ መድከም ) ከሚያመጡ ምክንያቶች ዋነኛው የስኳር ህመም ነው ። ዲያሊሲስ ወይም የኩላሊት ንቅለ ተከላ ከተደረግላቸው ሰዎች ውስጥ 44 % ያህሉ የኩላሊት ህመማቸው ምክንያት የስኳር ህመም ነው።

 የስኳር ህመም በተለይ በአግባብ ካልታከሙት በጊዜ ሂደት የኩላሊት ስር መድከምን ያመጣል። ይህም ማለት ኩላሊቶች ከዚህ ቀደም ያካሂዱ በነበረው መልኩ አላስፈላጊ የሆኑ ንጥረነገሮች እና ፈሳሽን የማጣራት ስራቸውን  መተግበር ባለመቻላቸው እነዚህ ንጥረነገሮች በሰውነት ውስጥ ሲጠራቀሙ ሌሎች የሰውነት ክፍሎችን ይጎዳሉ፡፡

1)  መንሰኤው ምንድን ነው?

የስኳር በሽታን ተከትሎ የሚመጣ የኩላሊት ህመም መንስኤዎች ውስብስብ እና  ከብዙ ምክንያቶች ጋር የተዛመደ ነው ፡፡ አንዳንድ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት የስኳር ህመም ትናንሾቹ የኩላሊት ማጣሪይያዎች ላይ የስራ ጫና በመፍጠር በቀላሉ ለጉዳት አንዲጋለጡ ያደርጋል።

2)      አንዳንድ ሰዎች የስኳር ህመምን ተከትሎ ለሚመጣው የኩላሊት በሽታ ተጋላጭነታቸው ሰፊ ነው ወይ? 

አዎ!  የደም ግፊት መጨመር ያለባቸው፣ የስኳር ህመማቸው በአግባቡ ያልታከሙ፣ በተፈጥሮ ተጋላጭነታቸው የጨመረ አንዳንድ ሰዎች ፣ ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ ለበሽታው የመጋለጥ እድልን ከፍ ከሚያደርጉት ምክንያቶች  ናችው፡፡

3)      የስኳር ህመም አለብኝ ፡፡  ኩላሊቶቼ እንደታመሙ እንዴት ላውቅ እችላለሁ?

በመጀመሪያ ደረጃዎች ላይ ምንም አይነት ምልክት ላይታይ ይችላል ፡፡  የኩላሊት ተግባር እየቀነሰ በሄደ መጠን ግን የሰውነታችን ተረፈ ምርቶች በሰውነት ውስጥ እየተጠራቀሙ ይሄዳሉ  በመሆኑም ህመምተኞች በመጀመሪያ የሆድ ህመም እንደ ማቅለሽለሽ፣ ወደላይ ማለት፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ ፣ ስቅታ እንዲሁም በፈሳሽ መጠራቀም ምክንያት የሚመጣ ክብደት መጨመር ያጋጥማቸዋል፤ ይህን ሳይታከሙ ከቆዩ በሽተኞች የልብ ድካም እና በሳንባዎቻቸው ውስጥ ፈሳሽ መከማቸት ይፈጠራል ፡፡   

4)       የኩላሊት በሽታ እንዳለብኝ ለማወቅ የሚረዱ ምርመራዎች አሉ?

  አዎ! ምርመራው በሽንት ውስጥ ያልተለመደ የፕሮቲን መጠን መኖር ላይ የተመሠረተ ነው ፡፡  አንድ ሰው የኩላሊት በሽታ ካለበት ለማወቅ የተለያዩ ምርመራዎች ሊደረጉ ይችላሉ።  በአብዛኛው ጥቅም ላይ የዋሉት ሴረም ክሪያትኒን እና ቢዩኤን (የደም ዩሪያ ናይትሮጂን) ናቸው።  እነዚህ ምርመራዎች የኩላሊትን መጎዳትን በአፋጣኝ የሚያገኙ አይደሉም ፡፡ በሽተኛው የበለጠ ከባድ በሽታ እስኪፈጠር ድረስ መለወጥ አይጀምሩም ፡፡ ሌሎች ምርመራዎችእንደ -የክርያቲኒን መጣራት ልኬት ፣ ግሎሜሩላር ማጣሪያ ልኬት (ጂኤፍአር) እና የሽንት አልቡሚን መጠን በይበልጥ አመልካች ናቸው ፡፡

በልጅነት የሚጀምር የስኳር አይነት (ዓይነት 1 ) የስኳር በሽታ ባለባቸው ህመምተኞች ላይ ፣ የኩላሊት ህመም ምርመራ በሽንት ውስጥ በጣም አነስተኛ መጠን ያለው ፕሮቲን (ማይክሮ አልቡሚንዩሪያ) መኖር ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይችላል ፡፡  እነዚህን አነስተኛ ፕሮቲን ለመለካት ለየት ያሉ ዘዴዎች ያስፈልጋሉ ፡፡  በመደበኛ ምርመራዎች ግን  በሽንት ውስጥ ያለው ፕሮቲን መጠን በዝቶ ሲገኝ በሽተኛው  የስኳር በሽታ የሚያመጣው የኩላሊት ህመም ምልክቶችን ማየት ጀምሮ ሊሆን ይችላል፡፡

5)       ኩላሊቶቼን በሽታው  እስኪጎዳችው ምን ያህል ጊዜ ይወስዳል?

በአንደኛው አይነት የስኳር ህመም ካለባቸው ታካሚዎች አብዛኛዎቹ የተወሰነ የኩላሊት ተግባር መቀነስ ከሁለት እስከ አምስት አመት ባለው ጊዜ ውስጥ ያሳያሉ፡፡ ከ 30 እስከ 40 በመቶኛ  የሚሆኑት አደገኛ ወደሆነ የኩላሊት በሽታ መባባስ ከ 10 እስከ 30 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ሊያጋጥማቸው ይችላል። የሁለተኛው አይነት ስኳር ታማሚዎች (የአዋቂ) የስኳር በሽታ በደንብ ባይታወቅም ፣ ከሚከሰትበት እድሜ ገፋ ያለ ከመሆን በቀር ተመሳሳይ የሆነ አካሄድ እንደሚከተል ይታመናል፡፡

6)  የኩላሊት በሽታን ለመከላከል ምን ማድረግ እችላለሁ?

የስኳር ህመምተኞች በደም ውስጥ የሚገኝን  የስኳር መጠን በመቆጣጠር የኩላሊት በሽታን ለመከላከል እንደሚችሉ  መረጃዎች ያሳያሉ ፡፡ የሐኪምዎን ትዕዛዝ በአግባቡ በመከተል  የግሉኮስ ለመጠንዎን ለመቆጣጠር የሚረዳ አመጋገብ እና መድኃኒቶችን በትክክል መውሰድ አስፈላጊ ነው፡፡   

7)      ኩላሊቶቼ ቀድሞውኑ ከተጎዱ፤ እንዳይባባስ ማድረግ እችላለሁ?

 የኩላሊት በሽታ መባባስን መከላከል ወይም ማዘግየት ይቻላል ፡፡  ከፍተኛ የደም ግፊት ካለ የስኳር ህመምተኞች ላይ የኩላሊት በሽታን ሊያባብስ ይችላል ከሚባሉ ዋና ዋና ጉዳዮች ውስጥ ስለሆነ ከፍተኛ የደም ግፊት ካለብዎ የደም ግፊትዎን ክኒኖች በአግባቡ መውሰድ አስፈላጊ ነው ፡፡ ሀኪምዎ በተጨማሪም ኩላሊቶችዎ የሚያደርጓቸውን የሥራ ብዛት የሚቀንስ ዝቅተኛ-ፕሮቲን አመጋገብ እንዲከተሉ ይመክርዎታል ፡፡  እንዲሁም የስኳር ታካሚ አመጋገብ መከተልዎን እና የታዘዙልዎትን መድሃኒቶች ሁሉ መውሰድዎን መቀጠል አለብዎት፡፡

8)       እኔን ሊረዱኝ የሚችሉ አዳዲስ ህክምናዎች አሉ?

 አዎ. አንዳንድ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ኤሲኤ ኢንሂቢተርስ (ACEI or ARB)  የተባሉ የደም ግፊት መድሃኒቶች የስኳር ህመም ተከትሎ ለሚመጣው የኩላሊት በሽታ እድገትን ለመከላከል ወይም ለማዘግየት ሊረዱ ይችላሉ የሚሉ መረጃዎች አሉ ፡፡  እነዚህ መድኃኒቶች በሰውነትዎ ውስጥ የደም ግፊትን ይቀንሳሉ ፣ እናም በኩላሊት ማጣሪያዎች ውስጥ ያለውን የስራ ጫና/ ግፊት ሊቀንሱ ይችላሉ ፡፡  በተጨማሪም ከደም ግፊት ለውጦች ጋር የማይዛመድ ጠቃሚ ተፅእኖዎች ያመጣሉ ፡፡  እነዚህን መድሃኒቶች የሚወስዱ ታካሚዎች በሽንት ውስጥ አነስተኛ ፕሮቲን ይኖራቸዋል ፡፡  እነዚህ መድሃኒቶች ሊረዱዎት ይችሉ እንደሆነ ለማየት ከሐኪምዎ ጋር መነጋገር ይችላሉ፡፡

በቅርብ የወጡ ጥናቶች ደግሞ ኤስጂ ኤል 2 (SGLT2I) የሚባሉ መድኃኒቶች የስኳር መድኃኒቶች  የኩላሊት ህመም እንዳይባባስ እንደሚረዱ ያሳያሉ። ለእርስዎ ጠቃሚ እንደሆነ ለማወቅ ሀኪምዎን ያማክሩ ። 

 9)   ምን ያህል የሚሆኑት የስኳር ህመም የሚያመጣው የኩላሊት በሽታ ታካሚዎች የኩላሊት ተግባር ማቆም ያጋጥማቸዋል? 

አንደኛው አይነት የስኳር  በሽታ ካለባቸው ሰዎች 30 ከመቶ የሚሆኑት እና ከ 10 እስከ 40 ከመቶ የሚሆኑት ሁለተኛው የስኳር በሽታ  ካለባቸው ሰዎች ውስጥ የመጨረሻ ደረጃን የኩላሊት ተግባር ውድቀት ያጋጥማቸዋል ፣ ህይወታቸውን ለማቆየትም ህክምና ያስፈልጋቸዋል ፡፡ 

10) የኩላሊት ተግባር ማቆም ካጋጠመኝ ምን ማድረግ እችላለሁ? 

ኩላሊቶችዎ ስራችውን ካቆሙ  የዲያሊሲስ ሕክምና ማግኘት ወይም ለኩላሊት ነቅሎ ተከላ እጩ ሊሆኑ ይችላሉ ፡፡  ሁለት ዓይነት የዲአሊሲስ አይነቶች አሉ፤ – ሄሞዳያሊሲስ እና ፐሪቶኒያል ዲያሊሲስ።  ሐኪምዎ እነዚህን የሕክምና አማራጮች ከእርስዎ ጋር ይወያያል ፡፡ የትኛው ሕክምና ለእርስዎ የተሻለ ነው የሚሆነው ውሳኔ በእርስዎ የጤና ሁኔታ ፣ በአኗኗር ዘይቤዎ እና በግል ምርጫዎ ላይ የተመሠረተ ይሆናል ፡፡

በዶ/ር ቤዛዊት አለሙ። 

ትዊተር  @bezzawitt
Source : The National Kidney Foundation