የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፡ ስለ አካል ብቃት እንቅስቃሴ ማወቅ ያለብን


የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በብዙ ምክንያቶች ጠቃሚ ነው፡፡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረጋችን ምን እንጠቀማን?
 ጤናማ የሰውነት ክብደት እንዲኖር ያደርጋል

 የስኳር ህመምን፣ የልብ ህመምን፣ የኩላሊት በሽታን ጨምሮ ሌሎች የተለያዩ በሽታዎችን ይከላከላል

 የደም ግፊትን እና ኮሌስትሮልን ለመቆጣጠር ይረዳል

 ጥንካሬንና ፅናትን ለመገንባት ይረዳል

 ጉዳትን ይከላከላል

 በራስ መተማመንን ይገነባል

 ጥሩ እንቅልፍ እንዲኖር ያደርጋል


ለጤናዬ ምን ዓይነት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ይጠቅመኛል?


ለጤናችን ጠቃሚ የሆኑ ብዙ ዓይነት የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ፡-
 መራመድ

 የቤት ውስጥ ስራዎችን መስራት

 አትክልቶችን መንከባከብ

 በስፖርታዊ ውድድሮችና እንቅስቃሴዎች ውስጥ መሳተፍ

 የኤሮቢክ እንቅስቃሴዎች ማድረግ (በዝግታ መሮጥ፣ መዋኘት፣ ብስክሌት መጋለብ፣ ደረጃዎችን መዝለል፣ የእግር ጉዞ)

ማንኛውም ሰው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ይችላል?


አዎ፡፡ ማንኛውም ሰው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ይችላል፡፡ ነገር ግን የምናደርገው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለኛ
ትክክለኛ መሆኑን ማወቅ ይገባል፡፡ ትክክለኛነቱን ከሚከተሉት አንፃር ማየት አለብን፡-
 ዕድሜ

 የተክለሰውነት ሁኔታ

 ያለን አቅም
ስር የሰደደ ህመም ካለብን ማንኛውንም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መስራት ከመጀመራችን በፊት ሀኪም ማማከር አለብን፡፡


የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በምን ያህል ጊዜ ማድረግ አለብን?


ለብዙ ጊዜ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አድርገን የማናውቅ ከሆነ በቀን ከ 10 እስከ 15 ደቂቃ መለስተኛ እንቅስቃሴዎችን
በመስራት መጀመር አለብን፡፡ በሂደት ጠንከር ወደሚሉ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች እንሸጋገራለን፡፡ ለምሳሌ፡- የኤሮቢክ እንቅስቃሴዎችን መስራትና በሳምንቱ ቀናት ውስጥ እንቅስቃሴ የምንሰራበትን ጊዜ ከ 30 እስከ 60 ደቂቃ ከፍ እንዲል
ማድረግ፡፡


ኤሮቢክ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ምን ማለት ነው?


የኤሮቢክ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሲሆን የሚከተሉትን ለማድረግ ይረዳል፡-
 የልብ ምትን ይጨምራል

 በጥልቀት እንድንተነፍስ ያደርጋል

 ትልልቅ ጡንቻዎች እንዲዳብሩ ይረዳል


የኤሮቢክ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የተወሰኑ ምሳሌዎች፡-

 በእርምጃ መሄድ

 መደነስ ወይም መጨፈር

 በዝግታ መሮጥ

 ብስክሌት መጋለብ

 መዋኘት


የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከማድረግ በፊትና በኋላ አካልን መዘረጋጋት ጠቃሚ ነው?


አዎ፡፡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከመስራት በፊትና በኋላ ሰውነትን መዘረጋጋት ጉዳቶችን ለመከላከል እንዲሁም ጡንቻዎቻችንና አጥንቶቻችን እንዲጠነክሩ ያደርጋል፡፡


ጊዜ የለኝም፡፡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የማደርግበት ጊዜ እንዴት አገኛለሁ?


ማንኛው ሰው የተወሰኑ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን በቀኑ መርሀ ግብር ውስጥ መስራት ይችላል፡፡ ብዙ የአካል ብቃት
እንቅስቃሴዎችን በቤታችን ውስጥ ከቤታችን ውጪ ወይም በስራ ቦታ መስራት እንችላለን፡፡ የሚከተሉትን ማየት እንችላለን፡-


 ቴሌቪዢን እየተመለከትን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መስራት፡- አካላችንን በመዘረጋጋት ወይም ክብደት የሌላቸው ቁሳቁሶችን ወይም ብስክሌት በመጠቀም እንቅስቃሴ ማድረግ እንችላለን፡፡

 በመኖሪያ አካባቢያችን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መስራት፡- ወደ ሱቅ ብስክሌት በመጋለብ መሄድ፣ በአታክልት ጋርደን ውስጥ በመስራት፣ ሳር በመከርከም ወይም ኳስ ከልጆች ጋር በመጫወት
 በስራ ቦታ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መስራት፡- ወደ መስሪያ ቤታችን መዳረሻ ስንደርስ የ10 ደቂቃ የእግር
ጉዞ ማድረግ፣ ሊፊት ከመጠቀም ይልቅ መወጣጫ ደረጃዎችን መጠቀም፣ በምሳ ሰዓት በእርምጃ መሄድ ወይም
ድርጅታችን በስፖርታዊ መዝናኛ ውድድሮች ላይ የሚካፈል ከሆነ በመሳተፍ እንቅስቃሴ ማድረግ እንችላለን፡፡


የአካል ብቃት እንቅስቃሴን እንዴት ልማድ ማድረግ እንችላለን?


 መስራት የምንወደውን እንቅስቃሴ መምረጥ

 አብሮን ሊሰራ የሚችል ጓደኛ መፈለግ

 የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻችንን መቀያየር፡- አንድ ቀን ከተራመድን በሚቀጥለው ቀን መደነስ ወይም መጨፈር

 የአካል ብቃት እንቅስቃሴያችንን አስደሳች ማደረግ፡-በቡድን መንቀሳቀስ ወይም ከሙዚቃ ጋር መስራት

 ቀና ሆኖ መጠበቅ፡-ማንኛውንም ለውጥ ለማወቅ ሳምንታት ሊፈጅ ስለሚችል ወዲያውኑ ለውጥ ባናይ መጨነቅ የለብንም  ሂደታችንን መፈተሸ፡-የድካም ስሜት ሳይሰማን ረጅም ርቀት በእግራችን መጓዝ እንደምንችል ወይም ለረጅም ጊዜ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደምንችል ማየት

Source : The National Kidney Foundation.

ይህን የጤና መረጃ ከአሜሪካን የኩላሊት ህክምና ማህበር ድረ ገፅ ላይ ምንጭ አድርገን ስናቀርብ ፅሁፉን በመተርጎም የ ተባበረችንን መቅደስ ገበየሁን   / Twitter: @Mekdi_G ከልብ እናመሰግናለን ።