ዶ/ር ትንሳኤ አለማየሁ ; የህፃናት ህክምና ስፔሻሊስት እና የህፃናት ተላላፊ በሽታዎች ህክምና ሰብ-ስፔሻሊስት
በብዙ ሀገራት የኮቪድ19 (COVID19) መከላከያ እቅዶች የአካል ጉዳተኞችን ደህንነት የዘነጉ ናቸው፡፡ በዚህ አጭር ጽሁፍ የአካል ጉዳተኞች ሁኔታ ባገናዘበ መንገድ የኮቪድ19ን (COVID19) መስፋፋት እንዴት እንቀንስ የሚለውን እናያለን፡፡
- የማየት ችሎታቸው የቀነሰባቸውን ሰዎች መርዳት
ባለፈው ወር (ማርች 2020) የታተመ ጥናት እንደሚያሳየው ከፊል ወይም ሙሉ ለሙሉ የማየት ችግር ያጋጠማቸው ኢትዮጵያውያን ከአጠቃላይ ህዝቡ 5.3% ድርሻ አላቸው (ወደ 5.8 ሚሊየን የሚጠጋ ህዝብ)፡፡ በህብረተሰቡ ውስጥ የኮቪድ19 (COVID19) ታማሚዎች በበዙ ቁጥር እነዚህን ዜጎች በህመሙ እንዳይጠቁ ለማድረግ ተገቢ ፖሊሲዎች መቀረጽ አለባቸው፡፡ ቀላል ግን ልብ ካልናቸው ህመሙ ማየት ወደማይችል ወገናችን እንዳይተላለፍ የሚረዱ ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፡፡
- መንገድ ላይ ማየት ለማይችል ሰው እርዳታ ከመዘርጋታችን በፊት የእጃችንን ንጽህና ልብ እንበል፡፡ በአልኮሆል ወይም ሳኒታይዘር እጃችንን አሻሽተን ወይም ትንሽ ጊዜ ካለን በሳሙና እና በውሀ ታጥበን ወደሚፈልጉት አቅጣጫ ለመምራት እርዳታ ካስፈለገ እንጠይቅ፡፡
- ሊያስነጥሰን ወይም ሊያስለን ከሆነ ለሌላው ሰው ከምናደርገው ጥንቃቄ የበለጠ ትኩረት በመስጠት ርቀታችንን ጠብቀን አፍና አፍንጫችንን እንሸፍን፡፡
- ባሁኑ ጊዜ ህዝብ የተሰበሰበበት ቦታ ላይ ማስክ ማድረግ በህክምናው የሚመከር ነው፡፡ የህዝብን መሰብሰብ እና መራራቅ ለመለየት ስለሚቸገሩ በማንኛውም ሰአት የማየት ችሎታቸው የቀነሰ ሰዎች ማስክ ግድ ማድረግ አለባቸው፡፡
- የሚይዙት አቅጣጫ ጠቋሚ ዱላ ለመርዳት በሚመጡ ሰዎች ብዙ ጊዜ ስለሚነካካ የሚፀዳበትን አልኮሆል ወይም ሳኒታይዘር በበቂ ማየት ከሚችሉ ወገኖች ቀድመው ማግኘት አለባቸው፡፡
- በሚድያዎች የሚታዩ ማስተማርያ ፕሮግራሞች የመልእክታቸው ይዘት መስማት እና ማየት ለሚቸግራቸው ወገኖች አይደርስም፡፡ ስለዚህም በኮቪድ19 (COVID19) ህመም ለመጠቃት በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ ይሆናሉ፡፡ እያንዳንዱ የህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ መልእክት በንግግር የታጀበ እንዲሆን አስገዳጅ መመርያዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ድምፃዊ ማብራርያ የሌላቸው ምስላዊ የበሽታ መከላከያ መልእክቶች ማየት የማይችሉ ወገኖችን አያገናዝቡም፡፡ ስለዚህም መሻሻል አለባቸው፡፡
2. መስማት የተሳናቸውን መርዳት
የአለም የጤና ድርጅት እንደሚጠቁመው ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ከሚኖሩት ህዝቦች 15.7% የሚሆኑት በተለያየ ደረጃ ያለ የመስማት ችግር ያላቸው ናቸው፡፡ ከታች የተዘረዘሩትን ማድረግ በተወሰነ እነዚህ የህብረተሰባችን ክፍሎች ከኮቪድ19 (COVID19) ህመም ሊታደግ ይችላል፡፡
- በሚድያዎች የሚታዩ ማስተማርያ ፕሮግራሞች የመልእክታቸው ይዘት መስማት እና ማየት ለሚቸግራቸው ወገኖች አይደርስም፡፡ ስለዚህም በኮቪድ19 (COVID19) ህመም ለመጠቃት በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ ይሆናሉ፡፡ እያንዳንዱ የህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ መልእክት በምልክት ቋንቋ እንዲተላለፍ አስገዳጅ መመርያዎች ያስፈልጋሉ፡፡
- ባሁኑ ጊዜ ህዝብ የተሰበሰበበት ቦታ ላይ ማስክ ማድረግ በህክምናው የሚመከር ነው፡፡ ማስክን እንዳለንበት አካባቢ ማድረግ አለማድረግን መወሰን ብንችልም የመስማት ችሎታቸው የቀነሰ ሰዎች የሚያስነጥስ ወይም የሚያስልን ታማሚ ባቅራብያ መኖሩን ለመስማት ስለሚቸገሩ በማንኛውም ሰአት ማስክ ግድ ማድረግ አለባቸው፡፡
3. መራመድ ወይም ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ የሚያስቸግራቸውን መርዳት
- የኮቪድ19 (COVID19) ወረርሽኝን ለመከላከል የትራንስፖርት አቅርቦት ከወትሮውም የበለጠ ስለሚቀንስ መራመድ ወይም ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ የሚያስቸግራቸውን መርዳት ሰዎች ለበሽታው ሲጋለጡ ደውለው የሚያሳውቁበት የተለየ ቁጥር ቢኖር ጥሩ ነው፡፡ ቀጥሎም መመርመር ወይም የሆስፒታል እርዳታ ካስፈለጋቸው ቅድሚያ በመስጠት የአምቡላንስ አገልግሎት ማዘጋጀት እና ወደጤና ተቋም ሳይመጡ ያሉበት ድረስ በመሄድ መርዳት ያስፈልጋል፡፡
- ለመንቀሳቀስ የሚጠቀሙት ዊልቼይር ለመርዳት በሚመጡ ሰዎች ብዙ ጊዜ ስለሚነካካ የሚፀዳበትን አልኮሆል ወይም ሳኒታይዘር በበቂ ቀድመው ማግኘት አለባቸው፡፡
- ዊልቼይር ለመግፋት እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች እርዳታ ከመዘርጋታችን በፊት የእጃችንን ንጽህና ልብ እንበል፡፡ በአልኮሆል ወይም ሳኒታይዘር እጃችንን አሻሽተን ወይም ትንሽ ጊዜ ካለን በሳሙና እና በውሀ ታጥበን ወደሚፈልጉት አቅጣጫ መምራት ይኖርብናል፡፡
- ከላይ የተጠቀሱት የአካል ጉዳት ያለባቸው እና የተረጋገጠ የኮቪድ19 (COVID19) ኢንፌክሽን ያለባቸው ህመምተኞች ከሆስፒታል ሰራተኞች የተወሰኑት ተመድበውላቸው ንጽህናቸው ባግባቡ መጠበቁን እና ለሌሎች ታማሚዎች ወይም ሰራተኞች ተጋላጭ አለመሆናቸው መረጋገጥ አለበት፡፡
4. የአካል ጉዳት ያለባቸውን የህክምና ባለሙያዎች ከኮቪድ19 (COVID19) እንዴት መከላከል ይቻላል?
በሀገራችን የተለያየ የአካል ጉዳት ያለባቸው የህክምና ባለሙያዎች ይገኛሉ፡፡ የስራ ፀባያቸው ካላቸው የአካል ጉዳት ጋር ተደምሮ ከሌሎች የህክምና ባለሙያዎች የበለጠ የኮቪድ19 (COVID19) ህመም ሊተላለፍባቸው ስለሚችል የመከላከያ አልባሳት [Personal protective equipment (PPE)] ቅድሚያ ማግኘት አለባቸው፡፡
የጤና ወግ
በመረጃ የተመሰረተ ሕክምና ብቻ ።
………………………………………………………………………………………………………………………..
ይህ የጤና ወግ ድረ ገፅ ነው።
ስለ ጤንነታችሁ ማወቅ የምትፈልጉትን መረጃ የምታገኙበት ፣ በህክምና ባለሙያዎች የሚዘጋጅ የመረጃ ምንጭ ነው።
ሁልግዜም ከሀኪማችሁ ተማከሩ፣ ተጨማሪ መረጃ ከፈለጋችሁ የኛን ድረ ገፅ ጎብኙ።
በጥናት የተደገፈ መረጃ ብቻ እናቀርባለን።
የህክምና ባለሙያዎች ለህሙማኖቻችሁ የሚሆን የሚነበብ መረጃ ከፈለጋችሁ ይህን ግፅ ጠቁሟቸው። ህሙማኖቻችሁ እንዲያውቁት የምትፈልጉትን ነገር መረጃ ጠቅሳችሁ ፃፉልን፣ ስምችሁን ጠቅሰን እናወጣለን። የህክምና ተማሪዎች እንዲጽፉ እናበረታታለን።
በተጨማሪም በጤና ወግ ፖድካስት፣ በ ዩትዩብ ፣በ ትዊተር ፣ በ ፌስቡክ ፣ በቴሌግራም የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ገፆቻችን ታገኙናላችሁ