በ ሀይማኖት ግርማ  ( የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ)

ህዳር 24, 2015 የአካል ጉዳተኞች ቀን በአለም አቀፍ ደረጃ ለ 31ኛ ጊዜ በሃገራችን ደግሞ ለ30ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል፡፡የአካል ጉዳተኞችን መሠረታዊ ፍላጎት ተረድቶ ኃላፊነት የተሞላው አገልግሎቶችን በምላሹ ለመስጠት የአካል ጉዳት ምንድነው የሚለውን መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ሰዎች አካል ጉዳትን እና ስነትን የሚረዱበት መንገድ እንደሚኖሩበት አካባቢ እና ባህል ይለያያል፡፡

 

አካል ጉዳት ምንድነው?

 

አካል ጉዳት (Disability) ማለት የአእምሮ፣ የስሜት ህዋሳት እና የአካል መጎዳት ሲሆን ግለሠቡን በማህበረሰቡ ውስጥ እኩል ተሳትፎ እንዳያደርግ የሚገድብ ሁኔታ ነው፡፡ ስነት (impairment) ደግሞ በአእምሮ ፣ በስሜት ህዋሳት እና በአካል ላይ የሚደርስ ጉዳት ሆኖ ውጤቱም ያንን አካል በመጠቀም ማከናወን ይቻል የነበረው ተግባር ላይ ውስንነት (Activity limitation) መኖር ነው ፡፡

 

የጤና አገልግሎቶችን ተደራሽ ማድረግ ማለት አካል ጉዳተኞች በእኩል መልኩ በጤና አገልግሎቶች ተጠቃሚ እንዳይሆኑ የሚያደርጉ ሁኔታዎችን ማስወገድ እና ሊቀርቡ የሚገቡ አገልግሎቶችን እንደየአካል ጉዳት አይነታቸው የተመቻቸ እንዲሆን ማድረግ ነው ፡፡

 

የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ የሚያግዱ ተግዳሮቶች

  •  በአካል ጉዳት ዙሪያ ያለው አመለካከት በቂ አለመሆን (Attitudinal barrier)
  •  የመረጃ ልውውጥ በቂ አለመሆን ( Communication barrier)
  •  የመጓጓዣ መንገዶች በበቂ ሁኔታ አለመኖር (transportation barrier)
  •  ተቋማዊ ሁኔታዎች በቂ አለመሆን (Institutional barrier)
  •  የተቀረፁ  ፖሊሲዎች ላይ የሚታይ የአተገባበር ክፍተት (Policy barrier)
  •  መልክኣምድራዊ እና አካባቢያዊ አቀማመጥ ላይ የሚታዩ ተግዳሮቶች ( Environmental and physical barrier)

 

የጤና አገልግሎትን ለአካል ጉዳተኞች እንዴት ተደራሽ ማድረግ ይቻላል?

 

መራመድ ወይም ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ለሚያስቸግራቸውን ሠዎች የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ

 

  •  የውጭ እና የውስጥ መግቢያ በሮች እንዲሁም መስኮቶች ማንኛውም አገልግሎት ፈላጊ ያለምንም ችግር ሊገባባቸውና ሊወጣባቸው በሚችል መልኩ የተዘጋጁ እንዲሆኑ ማድረግ
  •  አገልግሎት መስጫ ክፍሎች የአካል ጉዳተኛ ተገልጋዮች በሚመጡበት ጊዜ ምቹ የሆኑ እና ለዊልቸር ተጠቃሚዎች በቀላሉ መንቀሳቀስ እንዲችሉ በጠፍጣፋዎች ላይ የሚደረጉ የከርብ ቁራጮች እና በቂ የሆነ የመዘዋወሪያ ቦታ ያላቸው እንዲሆኑ ማድረግ
  •  ራምፖች በጎንና በጎን የእጅ መደገፊያ እንዲኖራቸው ማድረግ
  •  በምርመራ እና በሌሎች አገልግሎት መስጫ ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ የመመርመሪያ አልጋዎች፣ ወንበሮችና ጠረጴዛዎች ከፍ ወይም ዝቅ በማድረግ አካል ጉዳተኞች በቀላሉ ሊወጡባቸው፣ ሊተኙባቸውና እንዲወርዱ የሚያስችላቸው ማድረግ

 

ለአይነ ስውራን እና መስማት ለተሳናቸው ሠዎች  የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ

 

  •  በግቢ ውስጥ የሚለጠፉ አቅጣጫ ጠቋሚዎችና ሌሎች መረጃ ሰጪዎች በከፊል ጎላ ጎላ አድርጎ መፃፍ
  •  አሳንሰሮች በድምፅና በብሬል መረጃዎችን እንዲሰጡ ማድረግ ማስቻል
  •  በምርመራ ክፍሎችም ሆነ በሌሎች ክፍሎች በሮች ላይ የሚለጠፉ መረጃዎች ጎላ አድርጎ መፃፍ
  •  በራሪ ወረቀቶች ላይ የሚፃፉ መረጃዎችን ጎላ ጎላ አድርጎ መፃፍ በብሬል ማዘጋጀት ወይም በድምፅ መልክ ቀይሮ ማስተላለፍ
  •  ለመስማት የተሳናቸው ተገልጋዮች መረጃን ተደራሽ ለማድረግ እንዲያስችለን የጤና ባለሙያዎችን የምልክት ቋንቋ ማሰልጠን እና ከፊል መስማት ከተሳናቸው ታካሚዎች ጋር መረጃ በምንለዋወጥበት ወቅት ድምፅን ከፍ አድርጎ ማውራት

 

ለአካል ጉዳተኞች አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የሚሰሩ  የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እና እርምጃዎች የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ትኩረት እና ተሳትፎ የሚጠይቁ ተግባራት ናቸው፡፡ ስለዚህ ለአካል ጉዳተኞች መብት፣ ተካታችነት እና እኩልነት በሁሉም ቦታ ድምጽ በመሆን ኃላፊነታችንን እንወጣ!

 

References (ዋቢ)

 

https://www.cdc.gov/ncbddd/disabilityandhealth/            

https://www.cdc.gov/ncbddd/disabilityandhealth/disability-barriers.html         

https://disabilitycreditcanada.com/healthcare-accessibility-disability

 

የጤና ወግ 

ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።

የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።

https://linktr.ee/Yetena_Weg