By Jochebed Kinfemichael Suga, 4th year medical student at Myungsung Medical College

ጆኬቤድ ክንፈሚካኤል ሱጋ (ሚዩንግሱንግ ህክምና ኮሌጅ የ፬ አመት ተማሪ)

Reviewed/Approved by: Alemayehu Woldeyes,MD,MSc(Consultant ophthalmologist)

 

 

በአለማችን ላይ የአይነ-ስውርነት ዋነኛ ምክንያት ከሆኑት ውስጥ የአይን ሞራ በቀዳሚነት ይገኛል፡፡ የአይን ሞራ በተለምዶ ጠርቶ የሚገኘዉን የአይን ሌንስ ላይ ጭጋጋማ (foggy) ሽፋን መገኘት ነው፡፡ አይናችን እንዲያይ ብርሀን በጠራ ሌንስ ዉስጥ መተላለፍ አለበት፡፡ ይህም የጠሩ ምስሎች በውስጠኛዉ የአይናችን ክፍሎች ውስጥ እንዲተላለፍ ይረዳል፡፡ የአይን ሞራ በሚኖርበት ጊዜ ግን የአይናችን ክፍል ላይ ጭጋጋማ (foggy) ሽፋን ስለሚኖር የምናያቸዉ ነገሮች መደብዘዝ ብሎም እይታን ሙሉ በሙሉ እስከመከልከል ይደርሳል፡፡ ይህም በአንድ ጊዜ የሚፈጠር ሳይሆን ቀስ በቀስ በሂደት የሚፈጠር ነገር ነው፡፡

 

የአይን ሞራ እንዴት ይፈጠራል?

የአይናችን ሌንስ በተለምዶ ውሀ እና ፕሮቲኖችን ይዞ ይገኛል፡፡ በጊዜ ሂደት የእነዚህ ፕሮቲኖች መሰባበር የፕሮቲኖች ስብርባሪ ክምችት በአይናችን ሌንስ ላይ እንዲፈጠር ያደርገዋል፡፡ ይህም ክምችት በአይናችን ሌንስ ላይ ጭጋጋማ ሽፋንን ስለሚፈጥር ብርሀን በቀላሉ በመግባት የጠሩ ምስሎች መፈጠር እንዳይችሉ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህ ተፈጥሯዊ ሂደት እድሜ ሲገፋ(በተለይ በ50 እና 60 አመታት ላይ) በበለጠ መፈጠር ይጀምራል።

 

የአይን ሞራ ምልክቶች

የእይታ መቀነስ ወይም መጥፋት

ከነፀብራቅ ጋር የተገናኙ ችግሮች (በማታ መንዳት መቸገር፣ ሃሎስ)

ቀለማትን በቀላሉ ለመለየት መቸገር (ነጭ ነገሮች ቢጫ ሆነው መታየት)

እይታ ተደምሮ/ በዝቶ መታየት (double vision)

ጨረሮችን በምንመለከትበት ጊዜ ክብ ሆኖ መታየት (halo)

በተደጋጋሚ የአይን መነፅር መቀያየር ሲያስፈልግ

 

የአይን ሞራ ተጠቂ ማን ነዉ?

የአይን ሞራ በአብዛኛዉ ጊዜ ከ50-60 አመት ገደማ መፈጠር የሚጀምር ሲሆን አብዛኛው ሰው ምልክት ማየት የሚጀምረው ከ60 አመት ገደማ በኋላ ነው፡፡ የአይን ሞራ በጊዜ የመፈጠር እና ዘግይቶ የመፈጠር ጉዳይ እንጂ በማንኛዉም ሰዉ ላይ የሚፈጠር ነገር ነው፡፡ በሴቶች እና በወንዶችም ላይ የመፈጠር ሂደቱ ምንም ልዩነት የሌለዉ ሲሆን ሁለቱንም ፆታዎች እኩል ያጠቃል፡፡

ባልተለመደ ሁኔታ ህፃናቶች ሲወለዱ ወይም በልጅነት ጊዜያቸዉ የአይን ሞራ ሊኖራቸዉ ይችላል፡፡ ይህም በወላጆቻቸዉ በኩል በዘር የወረሱት ወይም በእናቶቻቸዉ ማህፀን ዉስጥ እያሉ ለኢንፌክሽን ሲጋለጡ ነዉ፡፡ አንዳንድ ጊዜም የአይን ሞራ በልጅነት ሲፈጠር ለሌሎች በሽታዎች እንደ አንድ ምልክት ሆኖ ሊገኝ ስለሚችል ጥልቅ ምርመራዎችን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

 

ለአይን ሞራ መፈጠር አስተዋፆ የሚያደርጉ ነገሮች

እድሜ እየጨመረ ሲሄድ የአይን ሞራ የመፈጠር እድሉ ይጨምራል፡፡ ከዛም በተጨማሪ ለአይን ሞራ ከሚያጋልጡ ምክንያቶች ውስጥ የሚከተሉት ዋነኞቹ ናቸዉ፡፡

የስኳር በሽታ

ማጨስ

አብዝቶ መጠጣት

መድሃኒቶች (እስቴሮይድ፤…)

በቤተሰብ ዉስጥ የአይን ሞራ ያለበት ካለ

ለረጅም ጊዜ ለፀሀይ ጨረር መጋለጥ

ከዚህ በፊት አይን ላይ የደረሰ ጉዳት ካለ ወይም ቀዶ ጥገና ከተደረገለት

በማህፀን ዉስጥ ለአይን ሞራ ለሚያጋልጡ ኢንፌክሽኖች መጋለጥ ለምሳሌ፡ ሩቤላ( rubella)

 

የአይን ሞራ አይነቶች

የአይን ሞራ ከሚገኝባቸው ቦታዎች ላይ በመመስረት በ3 እንከፍላቸዋለን፡፡

የመሀከለኛዉ የአይን ሌንስ ክፍል ላይ የሚገኝ የአይን ሞራ (Nuclear cataract)፡ ይህ የአይን ሞራ አይነት በመጀመሪያ የአጭር እይታ መቀነስ ወይም ጊዜያዊ የንባብ እይታ መሻሻል ሊያሳይ ይችላል፡፡ በጊዜ ሂደት ግን የአይን ሌንሱ ወደ ቢጫ ወይም ቡናማ ቀለም ይቀየራል፡፡ ይህም ቀለማትን መለየት እንድንቸገር ያደርገናል ማለትም ነጭ ነገሮች ቢጫ ሆነው ሊታዩ ይችላሉ፡፡ ስለሆነም የእይታ ሽፋንን ይጨምራሉ፡፡

የአይን ሌንስ ጠርዝ ላይ የሚፈጠር የአይን ሞራ(cortical cataract)፡ይህ የአይን ሞራ አይነት ሲጀምር ነጭ እና ሽብልቅ ቅርፅ ወይም ርዥራዥ ጭጋግ በሌንሱ ጠርዝ ላይ ይፈጥራል፡፡ ቀስ በቀስ ወደ መሀከለኛዉ የአይን ሌንስ ክፍል በመግባት የብርሀን መግቢያ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደር ይጀምራል፡፡

ከአይን ሌንስ ጀርባ የሚፈጠር የአይን ሞራ(Posterior subcapsular cataract)፡ ይህም የአይን ሞራ አይነት ብርሀን በሚተላለፍበት የአይን ሌንስ የጀርባ ክፍል ላይ ትንንሽ ጭጋጋማ ነጠብጣብ በመፍጠር ይጀምራል፡፡ ይህ የአይን ሞራ አይነት አብዛኛውን ጊዜ የንባብ እይታ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ ደማቅ ብርሀኖችን ለማየት እና የብርሀን ጨረሮችን ለማየት መቸገርን ያመጣል፡፡ ከነዚህ በተጨማሪም ይህ የአየን ሞራ አይነት ከሌላዉ የአይን ሞራ አይነት የሚለየዉ ከአንዱ ደረጃ ወደ ሌላ ደረጃ የሚተላለፍበት ሂደት የፈጠነ በመሆኑ ነው፡፡

 

የአይን ሞራ እንዴት ይታወቃል?

ከላይ ለመጥቀስ የተሞከሩት የአይን ሞራ ምልክቶችን ሲያስተውሉ ወደ አይን ሀኪሞ በመሄድ የአይን የውስጥ ክፍሎችን አጉልቶ በሚያሳይ መሳሪያ ሊታዩ ይገባል፡፡ የአይን ሀኪሞ የተሻለ እይታን ለመፍጠር የሚያስችልን የአይን ጠብታ መጠቀም ሊያስፈልገዉ ይችላል፡፡

 

የአይን ሞራ እንዴት ይታከማል?

የአይን ሞራ መጠኑ መለስተኛ ከሆነ የእይታ መጠኑ እንደ አዲስ ተለክቶ በአዲስ መነፅር ብቻ ሊከታተሉት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን የአይን ሞራ በጊዜ ሂደት መጠኑ የሚጨምር በመሆኑ ውሎ አድሮ ቀዶ ጥገና ማስፈለጉ አይቀሬ ነው፡፡

ብዙን ጊዜ የአይን ሞራ እይታን መከልከል እና የእለት ተዕለት የኑሮ እቅስቃሴዎችን መከልከል ሲጀምር በቀዶ ጥገና (surgery) የአይን ሞራን በማስወጣት ሰዉ ሰራሽ (artificial) ሌንስ መግጠም ያስፈልገዋል፡፡ ከየትኛውም ለአይን ሞራ ከሚደረጉ ህክምናዎች ውስጥ ዘለቄታዊ ውጤት የምናገኘዉ ከቀዶ ጥገና (surgery) በኋላ ነው፡፡

 

ከአይን ሞራ ቀዶ ጥገና በኋላ ሊፈጠሩ የሚችሉ ሁኔታዎች

ለአይን ሞራ ለሚደረግ ቀዶ ጥገና የስኬት መጠኑ 97-99% እንደሆነ ማስረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከአይን ሞራ ጋር ተያይዞ የሚመጡ የህክምና ውስብስቦች(complications) በብዛት ባይስተዋሉም አይፈጠሩም ማለት ግን አይቻልም፡፡ ሊከሰቱ ይችላሉ ከሚባሉት ውስብስቦች ውስጥ

ኢንፌክሽን (infection)

የአይን መቆጣት (inflammation)

አይን ዉስጥ መድማት (bleeding)

ሰው ሰራሽ (artificial) ሌንስ ቦታ መልቀቅ

ግላኮማ (glaucoma)

የአይን ሞራ ድጋሚ መከሰት (secondary cataract)

የሬቲና ቦታ መልቀቅ (retinal detachment)

የአይን የውስጠኛው ክፍል ውስጥ ውሃ ማቆር

የአይን እይታ መቀነስ/መጥፋት (loss of vision)

የአይን ሽፋን መውረድ (eyelid dropping)

 

የአይን ሞራን መከላከል ይቻላል?

በአይናችን ላይ የአይን ሞራ መፈጠር ሁሉም ሰዉ ላይ የሚፈጠር ከእድሜ ጋር ተያይዞ የሚመጣ ተፈጥሯዊ ሂደት ሲሆን በአንዳንድ ሰው ላይ ቶሎ በአንዳንድ ሰዉ ላይ ደግሞ ዘግይቶ የሚፈጠር ነው፡፡ የአይናችንን ጤንነት በመጠበቅ ግን ይህን የአይን ሞራ የመፈጠር ሂደት በተወሰነ መልኩ ልናዘገየው እንችላለን፡፡ በተጨማሪም ለአይን ሞራ መፈጠር አስተዋፆ ከሚያደርጉ ነገሮች ራስን ማራቅ አስፈላጊ ነዉ፡፡

 

የጤና ወግ 

ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።

የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።

https://linktr.ee/Yetena_Weg