በሜላት መስፍን (ጎንደር ዩ/ህ/ጤ/ሳ/ኮ የህክምና ተማሪ፡ C2)

ኮቪድ 19 አለም አቀፍ ወረርሽኝ ሆኖ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ለብዙዎች የህልፈትና የጤና መታወክ ምክንያት ሆኗል፤ በተጨማሪም ለተለያዩ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ስነልቦናዊ ቀውሶች ብዙዎችን ዳርጓል(1)። ወረርሽኙ ካስከተላቸው የስነልቦና ቀውሶች መካከል ጭንቀትና ድባቴ በዋናነት ይጠቀሳሉ(2,3,4)።

የጭንቀት ህመም ገና ባልተፈጠረና ባልታወቀ ነገር ላይ ይሆናል ብሎ አብዝቶ በመጨነቅ የሚመጣ ነው(5)። መጠነኛ የሆነ ፍርሃትና ጭንቀት እንደ ኮቪድ 19 ያሉ ህይወታችን ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ሁኔታዎች ሲገጥሙን የምንሰጠው ጤናማ ምላሽ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ግን ይህ ፍርሃትና ጭንቀት ከመጠን ካለፈ የአዕምሮ ጤና መታወክ ምልክት ሊሆን ይችላል።

በተጨማሪም እንደ ድባቴ ያሉ የአዕምሮ ህመም በወረርሽኙ ወቅት በብዛት ይስተዋላሉ። ድባቴ ሁል ጊዜ የሀዘን ስሜት እንዲሰማን ወይም በፊት ፍላጎት ለነበረን ነገሮች ላይ የነበረንን ፍላጎት እንድናጣ ሊያደርግ ይችላል። ይህ የጤና እክል በአመት ውስጥ ከ15 ሰዎች አንዱን ያጠቃል። በህይወት ዘመን ሲለካ ከ6 ሰዎች አንዱን ያጠቃል(5)። ይህ ቁጥር በወረርሽኙ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ ያሻቀበ ሲሆን ለዚህም እንደ ምክንያትነት ወረርሽኙ እንዳይዛመት የተወሰዱ እርምጃዎች ማለትም ከቤት መውጣት አለመቻል፣ የትምህርት ቤቶች መዘጋት፣ ከወዳጅ ዘመድ ጋር መገናኘት አለመቻል፣ ከስራ ገበታ መፈናቀል፣ ወረርሽኙ ያስከተላቸው ኢኮኖሚያዊ ውጥረቶች፣ በበሽታው የመያዝ፣ የመሞት ወይም የሚወዱትን ሰው የማጣት ፍርሀት በዋናነት ይጠቀሳሉ። እንዲሁም ወረርሽኙ በአእምሮ ጤና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል(2,3,4)።

ለድባቴ አጋላጭ ከሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ በአዕምሮአችን ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ንጥረ ነገሮች መጠን መዛባት፣ በበሽታው የተጠቃ የቅርብ የቤተሰብ አባል መኖርና በውጥረት ከልክ በላይ መረበሽ ይጠቀሳሉ(5)።

የድባቴ ምልክቶችም:- የድብርት ስሜት ወይም ለተከታታይ ቀናት ደስተኛ መሆን አለመቻል፣ የመደ’በር ስሜት፣ ከዚህ ቀደም እናደርጋቸው ከነበሩና እና ደስታ ለሚሰጡን የዕለት ተዕለት ተግባራቶቻችን ፍላጎት ማጣት፣ እንቅልፍ ማጣት ወይም እንቅልፍ ማብዛት፣ የድካም ስሜት፣ ትኩረት ማጣት እና መወሰን አለመቻል፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ ወይም መጨመር፣ ከፍተኛ የሆነ የጥፋተኝነት ስሜት መኖር፣ በእንቅስቃሴዎቻችን መዝገም ወይም መቅበዝበዝና ተደጋጋሚ የሆነ ራስን የማጥፋት ሃሳብ ወይም ሙከራ ናቸው(5)።

ከላይ ከተጠቀሱት 9 ምልክቶች 5 ወይም ከዚያ በላይ ምልክቶች እና ከ5ቱ አንዱ የድብርት ስሜት ወይም የፍላጎት መቀነስ ለተከታታይ 2 ሳምንታት አንድ ሰው ላይ ከታየበት እንዲሁም በዚህ ምክንያት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቹ ላይ ተፅዕኖ ካደረሰበት ድባቴ ገጥሞታል ማለት ነው(5)።

ድባቴ ከአብዛኞቹ  የአዕምሮ ህመሞች የተሻለ  ሊታከም የሚችል ህመም ነው። ለቀላል ድባቴ ሳይኮቴራፒ በባለሙያ የሚሰጥ ሲሆን ይህ ህክምና ህመምተኛው የተዛቡ ሀሳቦቹን እንዲገነዘብ በማድረግ እና ሀሳቡን እና ድርጊቱን እንዲያስተካክል ይረዳል። ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ ለሆነ ድባቴ ደግሞ ከፀረ-ድባቴ መድሃኒት ከሳይኮቴራፒ ጋር አንድ ላይ ይሰጣል(5)።

ምንም እንኳን ወረርሽኙ በአዕምሮ ጤና ላይ ከፍተኛ ጫና ቢያሳድርም በዚህ ወቅት የአእምሮ ጤናን ለመጠበቅ መወሰድ ከሚገባቸው እርምጃዎች መካከል ስለ ወረርሽኙ ከታማኝ ምንጮች መረጃን በማግኘት ሀሰተኛ መረጃዎች እኛ ላይ የሚፈጥሩትን አላስፈላጊ ውጥረት መቀነስ፣  በወረርሽኙ ምክንያት ከሰዎች ጋር በአካል መራራቅ ቢኖርም በስልክና በሌሎች የመገናኛ ዘዴዎች ማግኘት፣ የሰውነት እንቅስቃሴን ማዘውተር  እና የጭንቀትና የድባቴ ምልክቶችን ሲያስተውሉ ደግሞ የባለሙያ እርዳታን መፈለግ አስፈላጊ ነው።

ዋቢ

  1. World Health Organization. COVID-19 weekly epidemiological update, edition 58, 21 September 2021
  2. Disasa B, Teshome E. The Impact of the COVID-19 Epidemic on Mental Health Among Residents of Assela Town. Psychology Research and Behavior Management. 2021;14:957
  3. Usher K, Durkin J, Bhullar N. The COVID‐19 pandemic and mental health impacts. International Journal of Mental Health Nursing. 2020 Jun;29(3):315
  4. Bueno-Notivol J, Gracia-García P, Olaya B, et al. Prevalence of depression during the COVID-19 outbreak: a meta-analysis of community-based studies. Int J Clin Heal Psychol. 2021;21
  5. The Diagnostic and Statistical Manual of Mental Disorders, Fifth Edition (DSM‐5)

 

ይህ ፅሁፍ በዶ/ር ሄርሞን አማረ (የስነ አዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስት) እና የጤና ወግ ኤዲተሮች የተገመገመ ነው።