ዶ/ር ትንሳኤ አለማየሁ ; የህፃናት ህክምና ስፔሻሊስት እና የህፃናት ተላላፊ በሽታዎች ህክምና ሰብ-ስፔሻሊስት
የአለም የጤና ድርጅት ሪፖርት እንደሚያሳየው በአንድ ሀገር ከሚኖሩ ከ 1000 ነዋሪዎች ውስጥ ሲሰላ:
- ከፍተኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት (high income countries) ባመት 32.6 የደም ዩኒቶች
- ከአማካይ ከፍ ያለ ገቢ ባላቸው ሀገራት (upper middle income countries) ባመት 15.1 የደም ዩኒቶች
- ከአማካይ ዝቅ ያለ ገቢ ባላቸው ሀገራት (lower middle income countries) ባመት 8.1 የደም ዩኒቶች
- ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት (low income countries) ባመት 4.4 የደም ዩኒቶች ይለገሳሉ::
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሀገራት ውስጥ ከሚሰጡ የደም ልገሳዎች ደግሞ ግማሹ እድሜያቸው ከ 5 አመት በታች ላሉ ህፃናት የሚሰጡ ናቸው ::
ኢትዮጵያን ጨምሮ 78 ሀገራት 90% የደም ልገሳዎቻቸውን የሚሰበስቡት ከበጎ ፍቃደኞች ሲሆን ከሀገራችን አመታዊ የደም ልገሳ ፍላጐት (100,000 ዩኒቶች) እ.ኤ.አ. በ 2014 አ.ም. የተለገሰው 43% ነበር :: በተለይ ባለፉት ጥቂት አመታት የመንግስት እና የግል መስርያ ቤቶች, የእግር ኳስ ክለቦች ደጋፊ ማህበራት, የመሳሰሉት በበጎ ፍቃድ ለሚሰበሰበው የደም ልገሳ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ::
የCOVID19 ወረርሽኝ ታህሳስ 22 ተከስቶ ወደ ሀገራችን መጋቢት 4 ገብቷል :: ታድያ መስርያ ቤቶች ሰራተኞቻቸውን ከቤት እያሰሩ ባለበት እና እንቅስቃሴ ለህክምና ካልሆነ በስተቀር በተገደበበት ጊዜ የCOVID19 ህመም የደም ልገሳ ላይ ተጽእኖ እንዳያሳድር የሚከተሉትን ጥያቄዎች መልሰናል ::
- የCOVID19 ህመም በደም ንክኪ ይተላለፋል?
ባጠቃላይ የመተንፈሻ አካላት ህመሞችን የሚያመጡ እንደ ኮሮና ያሉ ቫይረሶች በደም ንክኪ አይተላለፉም :: እስከዛሬም በደም ንክኪ የተላለፈ የCOVID19 ህመም ሪፖርት አልተደረገም ::
- በዚህ ባልታሰበ ወረርሽኝ ጊዜ ደም ብለግስ ጤናዬን ይጎዳል?
ደም እንዳይለግሱ የሚከለክል ሁኔታ እስከሌለ ድረስ ያለጉዳት መለገስ ይቻላል ::
- ባጠቃላይ ደም ልገሳ እንዳይቀንስ ምን ይደረግ ?
- የኢትዮጵያ የደም ባንክ አገልግሎት የቤት ለቤት የደም ልገሳዎችን ከበጎ ፍቃደኞች መሰብሰብ ይችላል ::
- የሚድያ ተቋማት ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት እና ማስተማር አለባቸው ::
- የኢትዮጵያ የደም ባንክ አገልግሎት በጎ ፍቃደኞች ለመለገስ ሲመጡ የCOVID19 ህመም መከላከያ ስራዎች ማሟላት አለበት ::
- ከCOVID19 ህመም ያገገሙ በጎ ፍቃደኞች ደም መለገስ ይችላሉ?
አንድ የCOVID19 ታማሚ ሙሉ ለሙሉ ከዳነ/ች (ደም እንዳይለግሱ የሚከለክል ሁኔታ እስከሌለ ድረስ) ደም መለገስ ይችላሉ :: ሙሉ ለሙሉ መዳን የሚገለፀው ሁሉም ከታች ያሉት ተሟልተው
- የሆስፒታል ቆይታ እና የኦክስጅን እርዳታ ሳያስፈልግ ሁሉም የCOVID19 ህመም ምልክቶች ከጠፉ በኋላ
- በ24 ሰአት ልዩነት የተሰሩ ሁለት ተከታታይ የCOVID19 ምርመራዎች ታማሚው ከህመሙ ነፃ እንደሆነ ካሳዩ በኋላ
- በደረት ራጅ ላይ የሳንባ ጉዳት ምልክቶች መሻሻላቸው ከተረጋገጠ በኋላ
ከዛም ከሆስፒታል ወጥተው ተጨማሪ 14 ቀናት በቤታቸው ከቆዩ በኋላ ነው፡፡
የጤና ወግ
በመረጃ የተመሰረተ ሕክምና ብቻ ።
………………………………………………………………………………………………………………………..
ይህ የጤና ወግ ድረ ገፅ ነው።
ስለ ጤንነታችሁ ማወቅ የምትፈልጉትን መረጃ የምታገኙበት ፣ በህክምና ባለሙያዎች የሚዘጋጅ የመረጃ ምንጭ ነው።
ሁልግዜም ከሀኪማችሁ ተማከሩ፣ ተጨማሪ መረጃ ከፈለጋችሁ የኛን ድረ ገፅ ጎብኙ።
በጥናት የተደገፈ መረጃ ብቻ እናቀርባለን።
የህክምና ባለሙያዎች ለህሙማኖቻችሁ የሚሆን የሚነበብ መረጃ ከፈለጋችሁ ይህን ግፅ ጠቁሟቸው። ህሙማኖቻችሁ እንዲያውቁት የምትፈልጉትን ነገር መረጃ ጠቅሳችሁ ፃፉልን፣ ስምችሁን ጠቅሰን እናወጣለን። የህክምና ተማሪዎች እንዲጽፉ እናበረታታለን።
በተጨማሪም በጤና ወግ ፖድካስት፣ በ ዩትዩብ ፣በ ትዊተር ፣ በ ፌስቡክ ፣ በቴሌግራም የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ገፆቻችን ታገኙናላችሁ