አሜሲያስ ዘውዴ (በአ.አ.ዩ ህ/ጤ/ሳ/ኮ የ5ኛ አመት የህክምና ተማሪ)

Amesiyas Zewude, 5th year medical student at Addis Ababa University, College of Health Science.

Reviewed/Approved by: Dr. Gelila Sintayehu(Internist)

 

ሀንግ ኦቨር (ያደረ ስካር) አልኮል መጠጥን አብዝተው ከጠጡ በኋላ ባለው ጊዜ በሰውነታችን ስርአት ውስጥ የሚታዩ ለውጦች ምልክት ነው:: ቀደም ብለው የተሰሩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት አብዝተው አልኮል ከሚጠጡ ሰዎች ውስጥ ቢያንስ ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑት በአንድም ሆነ በሌላ ጊዜ ሀንግ ኦቨር ያጋጥማቸዋል።

ከምልክቶቹ መካከል ከፍተኛ የራስ ህመም/ማዞር ፣ ማቅለሽለሽ ፣ ማስመለስ ፣ የድካም ስሜት ፣ በድምፅ እና ብርሃን መረበሽ፣ የአፍ መድረቅ ድብርት፣ ጭንቀት እና ትኩረት ማጣት የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው:: ምልክቶቹ ከሰው ሰው እንዲሁም እንደተወሰደው የአልኮል መጠጥ አይነትና መጠን ይለያያሉ::

 

ሀንግ ኦቨር ለምን ይከሰታል?

አልኮል ወደ ደም ዝውውር ስርአታችን በመግባት ጤናማውን ሂደት የማወክ ባህርይ አለው:: በዚህም አዕምሮአችንን ጨምሮ ያሉንን ሌሎች የሰውነት ስርአቶች በትክክል እንዳይሰሩ ያደርጋል::

አልኮል ከሚያዛባቸው የሰውነት ስርአቶች መካከል የሰውነት ውሃን፣ ኤሌክትሮላይት እና የስኳር ምጠና ሂደትን በዋናነት ይጎዳል:: አልኮል ኩላሊታችን የማጣራት ስራውን ከሰራ በኋላ መልሶ ወደሰውነት የሚወስደውን የውሃ መጠን የሚቆጣጠሩ ሆርሞኖችን ስራ በማስተጓጎል ከሌላው ጊዜ በጨመረ ሁኔታ ውሃ ከሰውነታችን በሽንት መልክ እንዲወገድ ያደርጋል:: ውሃን ተከትለው የተለያዩ ኤሌክትሮላይቶችም ይወጣሉ:: በዚህም የተነሳ ከላይ የጠቀስናቸው ራስ ማዞር እና የድካም ወይም የመዛል ስሜት የመሳሰሉት ምልክቶች ይስተዋላሉ:: በተያያዥነት በሚከሰቱ የሆርሞን ለውጦችም የደም የስኳር መጠን ይቀንሳል:: የስኳር መጠን መቀነስ የድካም ስሜትን፣ የአዕምሮ ስርአት መዛባትን ፣ የትኩረት ማጣት፣ የባህርይ መለዋወጥ አለፍ ሲልም ራስን መሳት ሊያመጣ ይችላል።

 

መፍትሄ

በመፍትሄዎቹ ዙሪያ ብዙ ጥልቀት ያላቸው ጥናቶች ባይኖሩም ለመከላከል ማድረግ የምንችላቸው ነገሮች ግን አሉ::

አልኮልን አለማብዛት ወይንም አዘውትሮ አለመጠቀም፣ በሚጠቀሙበት ግዜ መጥኖ በሀላፊነት መውሰድ ዋነኛው መፍትሄ ነው::

ከመጠጣት በፊት ወይንም በመጠጣት ጊዜ ምግብን መመገብ ከአልኮል ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን የደም የስኳር መጠን መቀነስን በመጠነኛ ሁኔታ ለመቀነስ ይረዳል::

የአልኮል መጠጥ በሚጠቀሙ ሰዓት ውሀን አብሮ በመጠጣት በአልኮል ምክንያት ከሰውነታችን ከሚወጣው ፈሳሽ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱትን ምልክቶች መከላከል ይቻላል።

ሌላው የስኳር መጠናቸው ዝቅተኛ የሆኑ ወይንም ከስኳር ነፃ የሆኑ መጠጦችን መምረጥም ይረዳል::

ሃንግኦቨር ከተከሰተ በኋላ በበቂ መጠን ውሃን መጠጣት እና እንደ ፖታሲየም እና ሶዲየም ያሉ ኤሌክትሮላይቶችን ለመተካት ORS ወይም RL የመሰሉ ፈሳሾች ያግዛሉ:: በቂ እረፍት ማድረግም ቶሎ ለማገገም ይረዳል::

በተጨማሪም የህመም ማስታገሻ መድሀኒቶች በተወሰነ መጠን እንደ ራስ ህመም ያሉትን ምልክቶች ያስታግሳሉ::

ተያይዝው ሊከሰቱ የሚችሉ ደረት አካባቢ ማቃጠል እና ቃር የመሳሰሉትን ምልክቶች አንቲአሲድ በመጠቀም ማስታገስ ይቻላል። ነገር ግን እንዚህን መድሀኒቶች ያለ ህክምና ባለሙያ ምክር መውሰድ አደጋ ስለሚያስከትል የጤና ባለሙያን ማማከር ያስፈልጋል::

እንደ ቫይታሚን ቢ ያሉ የጉበትን መርዛማ ኬሚካሎች የማስወገድ ሂደት የሚያግዙ መድሀኒቶችም ሊታዘዙልን ይችላሉ::

 

የተሳሳቱ አመለካከቶችና መላምቶች 

በሰዎች ዘንድ ብዙውን ጊዜ የሚጠቀሱና የሚዘወተሩ ቡና መጠጣት እና በቀዝቃዛ ውሃ ሰውነትን መታጠብ የመሳሰሉ መፍትሄ ተብለው የሚጠቀሱ ሀሳቦች ዙሪያ ጠለቅ ያለ ጥናታዊ መረጃ የለም::

የጤና ወግ 

ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።

የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።

https://linktr.ee/Yetena_Weg