በዶክተር ገመቺስ አብዲሳ ቡርካ (የውስጥ ደዌ ህክምና ሬዚደንት)

By Dr. Gemechis Abdissa Burka, first year internal medicine resident at Adama Medical College

Reviewed by Dr. Mahlet Mitiku Desalegn Final year Resident at St. Paul’s Hospital Millennium Medical College 

 

ብዙ ሰዎች በሃገራችን ዓይናቸው ቢጫ በሚሆን ጊዜ “የወፍ በሽታ” ወይም “ወፌ ያዘኝ” ይላሉ። የወፍ በሽታ በሌሊት ወፍ የሚከሰት የጉበት ሕመም እንደሆነም ያስባሉ። በተለምዶም የሌሊት ወፍ ሸንታበት ነው ተብሎ የሚታሰብ ሲሆን ወፏን መመገብም እንደ መድሀኒትነት ይጠቅማል እየተባለም ይነገራል። ስለዚህም በዚህ በሽታ የተያዙ ሰዎች ብዙ ጊዜ መፍትሔ ለማግኘት በቅድሚያ ወደ ባሕል ሕክምና ይሔዳሉ።

 

በርግጥ የጉበት ህመም ሚከሰተው በሌሊት ወፍ ሽንት ነውን?

ጉበት በሰውነት ውስጥ ካሉት ትላልቅ እና በጣም አስፈላጊ ከሚባሉት የሰውነት አካል ክፍሎች አንዱ ነው። ይህ አካል መርዛማ ንጥረ ነገሮችን (አልኮልን ጨምሮ) እና መድኃኒቶችን ሰባብሮ ከሰውነት ለማስወገድ ፣ የምግብ መፈጨት እና እንዲሁም የደም መርጋት ሂደት ውስጥ የጎላ ድርሻ አለው።

 

“ሄፐታይተስ(“hepatitis”) ምንድን ነው?

ሄፐታይተስ የሚለው ቃል የጉበት ጉዳትን ለመግለጽ የሚያገለግል ሲሆን፤ ሄፐታይተስ በቀላሉ “የጉበት መቆጣት” ማለት ነው::

ሄፐታይተስ በተለያዩ ተላላፊ ቫይረሶች እና ተላላፊ ባልሆኑ ችግሮች የሚከሰት በሽታ ነው። ይህ በሽታ ለተለያዩ የጤና እክሎች የሚዳርግ ሲሆን አንዳንዴም እስከ ሞት ሊያደርስ ይችላል።

ሄፐታይተስ አጣዳፊ ወይም ሥር የሰደደ በመባል ለሁለት ይከፈላል። ሄፐታይተስ አጣዳፊ የሚባለው የጉበት ጉዳት ጊዜው ከስድስት ወር በታች ሲሆን ነው። ሥር የሰደደ ሄፐታይተስ ሚባለው ደግሞ የጉበት ጉዳት ቢያንስ ለ6 ወራት ሲቀጥል ነው።

 

የሄፐታይተስ መንስኤዎች ምንድን ናቸው?

ብዙ የሄፐታይተስ መንስኤዎች ያሉ ሲሆን ከነሱ መካክል ዋነኞቹን እንመልከት።

1.ሄፐታይተስ ቫይረሶች (Hepatitis Viruses)

አምስት ዋና ዋና የሄፐታይተስ የቫይረስ አይነቶች አሉ። እነዚህም፦

• ሄፐታይተስ ኤ(A)፣

• ሄፐታይተስ ቢ(B)፣

• ሄፐታይተስ ሲ(C)፣

• ሄፐታይተስ ዲ(D) እና

• ሄፐታይተስ ኢ(E) ናቸው።

በአለም ጤና ድርጅት መረጃ መሰረት በዓለም ዙሪያ ወደ 354 ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎች ከሄፐታይተስ ቢ(B) ወይም ሲ(C) ጋር ይኖራሉ። በሃገራችን ኢትዮጵያም ለጉበት በሽታ መከሰት እነዚህ ቫይረሶች ዋነኞቹ መንስዔዎች ናቸው::

2.ራስ-ሰር ሄፐታይተስ :(autoimmune hepatitis)

የሰውነታችን በሽታ ተከላካይ ስርዓት የጉበት ህዋሳትን (ሴሎችን) በሚያጠቃ ጊዜ የሚከሰት ሲሆን፤ ይህም ጉበት እንዲቆጣ ያደርገዋል::

3. በአልኮል ምክንያት የሚከሰት ሄፐታይተስ (alcoholic hepatitis)

ይሄኛው የጉበት ላይ ጉዳት (ሄፐታይተስ አይነት) የሚከሰተው ከመጠን በላይ አልኮል በመጠጣት ነው። ከላይ እንዳየነው አንዱ የጉበት ተግባር አልኮልን ከሰውነት ማስወገድ ስለሆነ ከመጠን በላይ አልኮል መጠጣት በጊዜ ሂደት ጉበት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል።

4. ምክንያትነቱ ከአልኮል ውጭ በሆነ በጉበት ውስጥ በተከማቸ ስብ ምክንያት የሚከሰት ሄፐታይተስ (Non Alcoholic Steatohepatitis/Metabolic Dysfunction Associated Steatohepatitis)

 

ሰዎችን ለዚህ በሽታ ከሚያጋልጡ ነገሮች ውስጥ የሚከተሉት ይካትታሉ:-

ከመጠን ያለፈ ውፍረት(obesity)

ሁለተኛው አይነት የስኳር በሽታ (Type 2 Diabetes)

ከፍተኛ የሆነ የኮሌስትሮል (cholestrol) እና ትራይግሊሰራይድ(triglyceride) መጠን

 

ሄፐታይተስ እንዴት ይተላለፋል?

ሄፐታይተስ ኤ እና ኢ ቫይረሶች የተበከለ ምግብ ወይም ውሃ በመጠቀም ይከሰታሉ።

ሄፐታይተስ ቢ፣ ሄፐታይተስ ሲ እና ሄፐታይተስ ዲ የሚተላለፉት በሽታው ካለበት ሰው ደም ጋር በመገናኘት ነው። ሄፐታይተስ ቢ እና ዲ ከሌሎች የሰውነት ፈሳሾች ጋር በመገናኘት ሊተላለፉ ይችላሉ። ይህ በብዙ መንገዶች ሊከሰት ይችላል። ለምሳሌ የመድኃኒት መርፌዎችን መጋራት ወይም ጥንቃቄ የጎደለው የግብረ ሥጋ ግንኙነት በማድረግ። በተጨማሪም በእርግዝና ወይም በወሊድ ጊዜ ከእናት ወደ ልጅ ሊተላለፉ ይችላሉ::

 

የሄፐታይተስ ምልክቶች ምንድን ናቸው?

አጣዳፊ ሄፐታይተስ ምንም አይነት ምልክት ላይኖረው ይችላል።

ከ6 ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ በሄፐታይተስ የተያዘ ሰው ምልክት ካሳየ

• የጉንፋን አይነት ምልክቶች(ከፍተኛ ያልሆነ ትኩሳት፣ የድካም ስሜት፣ የሰውነት መቆረጣጠም)

• የሆድ ህመም(በተለምዶ ልብ (ጨጓራ) አካባቢ የሚባለው ቦታ ወይም ከዚህ አካባቢ በስተቀኝ ላይ ህመም መሰማት)

• የምግብ ፍላጎት ማጣት፣ ማቅለሽለሽ፣ ማስታወክ

• ዓይን እና ቆዳ ቢጫ መሆን ሊታዩበት ይችላል።

በአብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ምልክቶች ቀለል ያሉና በራሳቸው የሚጠፉ ናቸው። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ በሽታው በጣም ከባድ ሆኖ እስከ ሞት ያደርሳል።

ስር የሰደደ ሄፐታይተስም ምንም ምልክት ሳያሳይ በሽታው የተወሳሰበ ደረጃ ላይ ሲደርስ ብቻ ምልክቶቹ መታየት ሲጀምሩ ሊታወቅ ይችላል። ይህም የሚከሰተው በጉበት ላይ ቀስ በቀስ በጊዜ ሂደት ጠባሳ ስለሚፈጠር ነው። ከላይ ከተጠቀሱት በአጣዳፊ ሄፐታይተስ ጊዜ ከሚታዩ ምልክቶች በተጨማሪ

• የሆድ እና የሰውነት ማበጥ

• ደም ማስመለስ

• ምክንያቱ ያልታወቀ ክብደት መቀነስ

• ደም ያለመርጋት ችግር

• የእንቅልፍ መዛባት፣ የባህሪ መቀያየር፣ ንቃት መቀነስ ወይም አለመንቃት (coma) በስር የሰደደ ሄፐታይተስ ጊዜ ይታያሉ።

 

ለሄፐታይተስ ምን ምን ምርመራዎች ይደረጋሉ?

• የጤና ባለሙያው የሚያደርገው አካል ምርመራ

• የሄፐታይተስ ቫይረስ የደም ምርመራዎች

• የጉበት ተግባር ምርመራዎች:- የደም ናሙና በመውሰድ ጉበት ምን ያህል በብቃት እንደሚሰራ ለማወቅ ይጠቅማል።

• የጉበት ኢንዛይም መጠን ምርመራዎች- የጉበት ኢንዛይም ማለት የጉበት ጉዳትን የሚያመለክቱ በደም ውስጥ የሚገኙ ንጥረ ነገሮች ሲሆኑ መጠናቸው ከፍ ሲል የጉበት መጎዳት እንዳለ ያሳያሉ።

• የጉበት በሽታ በአካላዊ ምርመራ ላይ ምንም አይነት ምልክት ላይኖረው ይችላል። ነገር ግን በደም ምርመራ ከፍ ያለ የጉበት ኢንዛይም መጠን መገኘት የጉበትን መጎዳት ያመለክታሉ።

• እንደ አልትራሳውንድ፣ ሲቲ ስካን ወይም ኤምአርአይ (MRI) ያሉ የምስል ምርመራዎች

• እጅግ በጣም አንዳንድ ጊዜ የጉበት ጉዳት መኖሩን ለማረጋገጥ የጉበት ናሙና (ባዮፕሲ) ማድረግ ሊያስፈልግ ይችላል።

 

በሄፐታይተስ ምክንያት የሚመጡ መዘዞች ምንድን ናቸው?

ምንም እንኳን ምልክቶቻቸው በራሳቸው ጊዜ ቢጠፉም ሄፕታይተስ ቢ እና ሲ በሰውነት ውስጥ በመቆየት ስር የሰደደ ኢንፌክሽን የመፍጠር ባህርይ አላቸው:: የሚፈጥሩትም መዘዝ የጉበት ጠባሳ ወይም ሲርሆሲስ (cirrhosis) እና የጉበት ካንሰር (liver cancer) ናቸው።

የጉበት ጠባሳ ወይም ሲርሆሲስ (cirrhosis): የጉበት መጎዳት ስር ከሰደደ እና ረዘም ላለ ጊዜ ከቆየ በጉበት ላይ ከባድ የሆነ ጠባሳ ይፈጠራል። ጉበት ላይ ከፍተኛ ጠባሳ መፈጠር የጉበት ተግባርን ያስተጓጉላል።

 

የሄፐታይተስ ሕክምናዎች ምንድን ናቸው?

ለሄፐታይተስ የሚሰጠው ሕክምና በሽታውን ባስከሰተው መንስኤ ይወሰናል::

አጣዳፊ የቫይረስ ሄፐታይተስ ምልክቶች ብዙውን ጊዜ በራሳቸው ይጠፋሉ። ጥሩ ስሜት ለመሰማት እረፍት ማድረግ እና በቂ ፈሳሽ ማግኘት ብቻ ያስፈልግዎታል። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ምልክቶቹ እጅግ ከባድ ሊሆኑ ይችላሉ። በዚህ ጊዜ ሆስፒታል ውስጥ ህክምና ያስፈልጋል::

ሥር የሰደደ የሄፐታይተስ በሽታ ያለባቸው ሰዎች የፀረ-ቫይረስ መድሃኒት እንዲወስዱ ሊታዘዝ ይችላል:: ስለዚህ ቋሚ የሆነ ክትትል ማድረግ አለባቸው።

ሥር የሰደደ የሄፐታይተስ በሽታ ያለባቸው ሰዎች አልኮል ፣ ጉበትን ሊጎዱ የሚችሉ ባህላዊም ሆነ ከሀኪም ትእዛዝ ውጭ መድሀኒት መውሰድ የለባቸውም!

የባህላዊ መድሀኒቶች በውስጣቸው ምን አይነት ኬሚካል በምን ያህል መጠን አንደያዙ በተጨባጭ ስለማይታወቅ እነዚህ መድሀኒቶች ጉበት በሽታ ላለበት ሰው ብቻ ሳይሆን ለተቀረው ህብረተሰብም እንዲወሰዱ አይመከርም!

የክብደት መቀነስ እና የአመጋገብ ለውጦች ምክንያትነቱ ከአልኮል ውጭ በሆነ በጉበት ውስጥ በተከማቸ ስብ ምክንያት የሚከሰት ሄፐታይተስ (Nonalcoholic steatohepatitis) ቀዳሚ ሕክምናዎች ናቸው።

 

ሄፐታይተስን መከላከል ይቻላል?

እንደ ሄፐታይተስ አይነቱ በመወሰን የሄፐታይተስ በሽታን ለመከላከል ወይም ለመቀነስ የተለያዩ መንገዶች አሉ። ለምሳሌ፦

• ከመጠን በላይ አልኮል ባለመጠጣት የአልኮል ሄፐታይተስን (የጉበት ጉዳትን) መከላከል ይቻላል።

• የሄፐታይተስ ቢ ቫይረስን ለመከላከል አስተማማኝ እና ውጤታማ ክትባቶች አሉ። ይህ ክትባት የሄፐታይተስ ቢ ቫይረስ እድገትን ይከላከላል እና ህፃን ልጅ ሲወለድ የሚሰጠው ክትባት ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ እድልን በእጅጉ ይቀንሳል።

• የምግብ እና የመጠጥ ንጽህናን በአግባቡ በመጠበቅ በሄፐታይተስ ኤ እና ኢ እንዳንጠቃ መከላከል ይቻላል።

እንቅስቃሴ ማድርግ፣ የተመጣጠነ ምግብ መመገብ፣ ውፍረት መቀነስ

በሄፐታይተስ ቫይረስ የተያዘን ሰው በምንከባከብበት ወቅት በሽታው እንዳይዘን መጠንቀቅ። ለምሳሌ፦ የእጅ ጓንት መጠቀም ከሰውነት ከሚወጡ ፈሳሾች እና ደም ንክኪ ይከላከላል።

 

ሄፐታይተስ ቫይረስ ቢ የተጋለጡ ሰዎች ምን ማድረግ ይችላሉ?

ሄፐታይተስ ቢ ቫይረስ ክትባት ሳይወስዱ ወይም ክትባቱን በሙሉ ወስደው ሳይጨርሱ ለቫይረሱ ከተጋለጡ በሽታውን ለመከላከል ከ24-48 ሰዓት ውስጥ ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ ክትባት መውሰድ ይችላሉ።

 

ስለዚህ የጉበት ህመም የሚከሰተው በሌሊት ወፍ ሽንት ነው?

ሄፐታይተስ በአብዛኛው የሚከሰተው ከላይ ባየናቸው ምክንያት እንጂ በቀጥታ ከሌሊት ወፍ ሽንት ጋር አይገናኝም!

 

Sources

Mehta P, Reddivari AKR. Hepatitis. [Updated 2022 Oct 24]. In: StatPearls [Internet]. Treasure Island (FL): StatPearls Publishing; 2023 Jan-. Available from: https://www.ncbi.nlm.nih.gov/books/NBK554549/

NASH Causes | Stanford Health Care

Medscape

 

 

የጤና ወግ

ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።

የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።

https://linktr.ee/Yetena_Weg