በ ዶ/ር ትንሳኤ አለማየሁ

በሀገራችን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከገባ 6ኛ ወራችንን ይዘናል፡፡ ከወረርሽኙ ለየት ያሉ ባህርያት አንዱ እስካሁን ከምናውቃቸው ካብዛኞቹ ተላላፊ ህመሞች አንፃር በቀላሉ ከሰው ሰው የመሻገር አቅሙ ነው፡፡ 

በሽታው ከሰው ሰው የሚተላልፍበት መጠን ከቦታ ቦታ እና በሁኔታዎች ይለያይል።

በአንዳንድ ወቅቶች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመተላለፍ በሰርግ፣ በሀዘን፣ በአምልኮ ወ.ዘ.ተ. የተሰበሰቡ ሰዎች በጅምላ በኮቪድ-19 ህመም ሲያዙ (በዱከም፣ በአዲስ አበባ አብነት እና 24 ሰፈሮች እንዲሁም በቅርቡ በቨርጂንያ ነዋሪ በሆኑ ኢትዮ-አሜሪካውያን) 

በሌሎች ጊዜያት ደግሞ ብዙ ሰዎች በትራንስፖርት፣ በስብሰባ በመሳሰለው ተገኝተው አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ህሙማን እናያለን፡፡ በተለይ የሁለተኛው አይነት አጋጣሚዎች ለብዙ ሰው መዘናጋት መንስኤ ይሆናሉ፡፡

እውነታው አሁንም ቢሆን ማህበረሰባዊ መራራቅ ከሌለ፣ አፍና አፍንጫ ካልተሸፈነ እና የግል እና የቁሳቁስ ንጽህና ካልተጠበቀ ለኮቪድ-19 ህመም ተጋላጭ አንደሆንን ያሳያል፡፡ 

በጣም ልብ ልንለው የሚገባው ነገር በጣም ጥቂት ሰዎች ለብዙ ሰዎች በበሽታ መያዝ ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉ ነው። 

የሚከተለው ጽሁፍ፣ ታድያ ይህ ከሆነ “ይኸው እዚህ ቦታ ተሰልፌ ምንም አልሆንኩም ወይም ይህ ለቅሶ ቦታ ሄጄ አላመመኝም” ብለው እንደ መከራከርያ ለሚነሱ ጥያቄዎች የተወሰነ ማብራርያ ይሰጣል፡፡

ለ ኮሮና ቫይረስ ከፍተኛ አጋላጭነት  ያላቸው ሁኔታዎች (Super spreading events ) ምንድናቸው ?

 በሚያዝያ ወር የተሰራ ጥናት እንደሚያሳየው እስከ 80 ፐርሰንት የሚደርሰው የኮሮና ቫይረስ  ኢንፌክሽን በጣም በጥቂት ሰዎች (እስከ 10 ፐርሰንት በሚደርሱ ብቻ)  ሊተላለፍ  እንደሚችል ያሳያል። 

ሌላ በአሜሪካ ጆርጂያ የተሰራ ጥናት ከተከሰቱ የኮሮና ቫይረስ ኢንፌክሽኖች 20 ፐርሰንት የሚደርሰው በጣም በጥቂት ሰዎች ( 2 % በሆኑ ሰዎች) ባሉ ሰዎች ብቻ ምክንያት የመጣ ነው።

 እነዚህ በጣም ጥቂት ሰዎች እንዴት ብዙ ሰዎችን በበሽታ ሊያስዙ ቻሉ? 

ከ ጥናቶቹም መረዳት እንደሚቻለው ሰው በብዛት የሚገኝባቸው እና ብዙም የአየር ዝውውር የሌለባቸው ቤቶች ውስጥ ለምሳሌ ቡና ቤት፣  ሰዎች የተሰበሰቡበት ለቅሶ ቤት፣ ሰው  በብዛት የሚገኝበት በቤተክርስቲያን ወይም የሃይማኖት ተቋም እንደነዚህ አይነት ከፍተኛ የመስፋፋት ምንጮች ሆኑ ይችላሉ። እነዚህ ሁኔታዎች ከፍተኛ አጋላጭነትን ይፈጥራሉ። አንድ የታመም ሰውበነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ ከሌሎች ሰዎች ጋር ከተገኘ ለብዙዎች መታመም ምክንያት ሊሆን ይችላል።

ይሄ super spreading  event እንዴት ይፈጠራል?

ይሄ እንደታማሚው -የህመም ጊዜ  ፣ ባህሪ ( ማስክ  የማድረግ ልምድ ) የተገኙበት ቦታ ፣ እና ጊዜ ይወሰናል ። በዝርዝርለመግለፅ

1. የኮቪድ-19 ህመም በከፍተኛ ሁኔታ የሚተላለፈው ታማሚው በቫይረሱ ከተጠቃ በኋላ ባሉት የመጀመርያዎቹ 5 ቀናት ነው፡፡ ስለዚህም ቫይረሱ በሰውነትዎ ከገባ በ 3ኛዉ ቀን ላይ ያለዎት የቫይረስ መጠን እና ህመሙን በዙርያዎ የማስተላለፍ አቅም በ 12ኛው ቀን ህሙም ሊያስተላልፉባቸው ከሚችሉት የሰዎች ቁጥር ጋር አይወዳደርም፡፡

ቀጥሎ የሚነሳው ጥያቄ የህመም ስሜት ከሌለብኝ ስንተኛው ቀን ላይ እንደሆንኩኝ እንዲሁም የማስተላለፍ አቅሜ ከፍተኛ ነው ወይስ ዝቅተኛ የሚለውን እንዴት አውቃለሁ ነው፡፡ 

የህመም ስሜት ከሌለ ወይም በጣም ቀላል ምልክቶች ብቻ ካሉ ያን ማወቅ አይቻልም፡፡ ለዛም ነው ሁል ጊዜ የስብሰባዎቻችንን መጠን መቀነስ እና ርቀታችንን መጠበቅ አስፈላጊ የሚሆነው፡፡ 

የህመሙን የማስተላለፍ አቅሙ ከፍተኛ የሆነ ሰው የተገኘበት ለቅሶ ላይ ተገኝተው እርስዎም ሌሎችም

በመቶዎች የሚቆጠሩ ታዳሚዎች ሊታመሙ ይችላሉ፡፡ 

ወይም ምንም ታማሚ የሌለበት ወይም ህመሙ እየተገባደደ ያለ ሰው የተሳፈረበት አውቶቡስ ላይ ተጉዘው ምንም ሳያጋጥም ሊወጡ ይችላሉ፡፡ መፍትሄው ሁሌ የመከላከል ህጎችን ማክበር ነው፡፡

2. ሌላው አንድ ታማሚ ለምን ያህል ሰው ሊያስተላልፍ ይችላል የሚለውን የሚወስነው ምን ያህል ቫይረስ በውስጡ አለ የሚለው ነው፡፡

ለምሳሌ ብዙ የበሽታ የመከላከል አቅምን የሚፈታተኑ ተጓዳኝ ህመሞች ካለዎት ከፍተኛ መጠን ለው የ SARS CoV-2 ቫይረስ ሊኖርዎት እና ለበርካታ ቤተሰብ አባላት ወይም ጓደኞች ሊያስተላልፉ ይችላሉ፡፡ በተቃራኒው ጠንካራ የህመም የመከላከል አቅም ያለዎት ከሆነ በመተንፈሻ አካሉ ገብተው የሚዘዋወሩትን የ SARS CoV-2 ቫይረሶች መጠን ሊገደቡ ብሎም ለትንሽ ሰው ብቻ የኮቪድ-19 ህመም ሊያስተላልፉ ይችላሉ፡፡

3. አሁንም ሌላ መታሰብ ያለበት ሰርጉን፣ ለቅሶውን፣ የሃይማኖት ቦታውን ወይም ሰልፉን ሊሳተፍ የመጣው ሰው ስራው ምንድነው የሚለው ነው፡፡ 

ለምሳሌ የትራንስፖርት (ታክሲ፣ አውቶቡስ፣ ባቡር፣ አውሮፕላን)) አሽከርካሪዎች ተከታታይ ተጋላጭነት አላቸው፡፡ በስራዎ ፀባይ ምክንያት በ SARS CoV-2 ቫይረስ ቢጠቁ እና ርቀትዎን ሳይጠብቁ ለአምልኮ ወይም ለሌላ ጉዳይ ለረዥም ሰአት ከብዙ ሰው ጋር ቢገናኙ ከላይ የጠቀስነው ከፍተኛ አስተላላፊ ጊዜ ላይ የመሆን እድልዎ ከሌሎች ከፍ ይላል፡፡ በዛኑ ልክ የግላቸውን ጤና እየተንከባከቡ የሌላውን ደህንነት የሚጠብቁ እና እንቅስቃሴያቸውን የሚገድቡ ሰዎች ደግሞ ለህብረተሰብ ጤና መጠበቅ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡

4. ሌላው የመሰብሰቢያ አዳራሾች አሰራር እና የአየሩ ሁኔታ (ፀባይ) ነው፡፡  በቂ የሆነ አየር የማያገኝ የተጣበበ ክፍል ለበሽታው በከፍተኛ ሁኔታ መስፋፋት ምክንያቶች ናቸው 

5. የተሰብሳቢዎች እድሜ ሌላው ወሳኝ ነገር ነው፡

በበርካታ ጥናቶች እንደታየው በስብሰባዎች የኮቪድ-19 ህመም የመተላለፍ እድል እድሜቸው 60 አመት እና ከዛ በላይ በሆኑት ላይ ይብሳል፡፡ በአንደዚህ ያሉ ቦታዎች የአዛውንቶች ተጋላጭነት እድሜያቸው 18 አመት እና በታች ከሆኑ ልጆች አንፃር ከ 3 እስከ 4 እጥፍ ይጨምራል፡፡ ስለዚህም በተለይ የአምልኮ ቦታዎችን የመጎብኘት ልምዳቸው፣ ሀዘንተኛን የማጽናናት ልምዳቸው ከፍተኛ በሆኑት እናት እና አባቶችችን ርቀት የማይጠበቅበት ቦታዎች መገኘታቸው የበለጠ ተጋላጭነትን ይፈጥርባቸዋል፡፡ በአንድ ጊዜም ብዙ ቁጥር ያላቸው አዛውንቶች ሊታመሙ ይችላሉ፡፡

ከላይ የተቀስኳቸውን ጨምሮ የኮቪድ-19 ስርጭትን አቅጣጫ ሊቀይሩ የሚችሉን አጋጣሚዎች ማን ሁሉንም አሰላስሎ ስለተጋላጭነቱ እርግጠኛ መሆን ይችላል? በቁጥጥርዎ ያለው ማህበረሰባዊ መራራቅን ማክበር፣ አፍና አፍንጫዎን መሸፈን እና የግል እና የቁሳቁስ ንጽህናዎን መጠበቅ ነው፡፡

የጤና ወግ

በመረጃ የተመሰረተ ሕክምና ብቻ ።  

………………………………………………………………………………………………………………………..

ይህ የጤና ወግ ድረ ገፅ ነው።
ስለ ጤንነታችሁ ማወቅ የምትፈልጉትን መረጃ የምታገኙበት ፣ በህክምና ባለሙያዎች የሚዘጋጅ የመረጃ ምንጭ ነው።
ሁልግዜም ከሀኪማችሁ ተማከሩ፣ ተጨማሪ መረጃ ከፈለጋችሁ የኛን ድረ ገፅ ጎብኙ።

በጥናት የተደገፈ መረጃ ብቻ እናቀርባለን።

የህክምና ባለሙያዎች ለህሙማኖቻችሁ የሚሆን የሚነበብ መረጃ ከፈለጋችሁ ይህን ግፅ ጠቁሟቸው። ህሙማኖቻችሁ እንዲያውቁት የምትፈልጉትን ነገር መረጃ ጠቅሳችሁ ፃፉልን፣ ስምችሁን ጠቅሰን እናወጣለን። የህክምና ተማሪዎች እንዲጽፉ እናበረታታለን።

በተጨማሪም በጤና ወግ ፖድካስት፣  በ ዩትዩብ ፣በ ትዊተር ፣ በ ፌስቡክ ፣ በቴሌግራም የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ገፆቻችን ታገኙናላችሁ