በዶ/ር ሔለን ብርሃኔ (ጠቅላላ ሀኪም, ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የወሊድ እና ስነ-ተዋልዶ ህክምና ማዕከል)

አርትኦት እና እርማት – በ ዶ/ር ምስክር አንበርብር (Gynecologist/Obstetrician)

 

መካንነት ምንድንነው? 

በህክምና አለም መካን መሆን የሚገለጸው፤ለመዉለድ ያቀዱ አንድ ወንድ እና ከ35 ዓመት በታች ያለች ሴት ከአንድ ዓመት በላይ ለሆነ ጊዜ ያለምንም የወሊድ መከላከያ  በቂ የሆነ የግብረ ስጋ ግንኙነት በማድረግ ለማርገዝ ሳይችሉ መቅረት ሲሆን፣ ከ35 ዓመት በላይ ለሆነች ሴት ግን የጊዜ ገደቡ 6ወር ይሆናል።

በአለማችን  ትንሽ የማይባል ቁጥር ያላቸው ሰዎች በመካንነት ይጠቃሉ። የአለም ጤና ድርጅት  ከስድስት ሰዎች አንዱ በመካንነት ሊቸገር ይችላል ይላል። በሃገራችን በተሰራ ጥናት ደግሞ ከአምስት ሰዎች አንዱ በመካንነት እንደሚጠቃ ያሳየናል። 

በማህበረሰባችን ውስጥ ከምናስተውላቸው ትክክል ያልሆኑ እሳቤዎች አንዱ የመካንነት ተጠቂዎች ሴቶች ብቻ ናቸው የሚለው ነው።ሴቶችም ሆኑ ወንዶች ለመካንነት መከሰት አስተዋጾ ያረጋሉ፣ 30-40% የሚሆነውን ጊዜ ሴቶች 30% ወንዶች እንዲሁም 10-15% የሚሆነውን ሁለቱም ለመካንነት መከሰት ምክንያት ይሆናሉ። 

ቁጥሩ ከሚያሳየን በተለየ መልኩ ሴቶችን ለችግሩ እንደ ብቸኛ መንስኤ አድርጎ በመውሰድ ማግለል እና መውቀስ ይታያል። ይህ መስተካከል ያለበት ተገቢ ያልሆነ አስተሳሰብ ነው።

ሌላኛው ስለመካንነት የተሳሳት የሆነው አስተሳሰብ ደግሞ የማይፈታ እና ሊታከም የማይችል ህመም ነው ብሎ ማሰብ ነው። ምርመራ በማድረግ እና ለተገኘው የመካንነት መንስኤ ተገቢውን ህክምና በማግኘት ከ85-90% የሚሆን ጊዜ መፍትሄ ማግኘት ይቻላል። ስለዚህ መካንነት በሚገጥምበት ጊዜ ተስፋ ቆርጦ ከመቀመጥ ይልቅ ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ መታከም የተሻለ አማራጭ ነው።

 

የመካንነት መንስኤዎች

በሴቶች ላይ የሚታዩ መንስኤዎች

እርግዝና እንዲፈጠር የሴቶች እንቁላል በትክክል እና በበቂ መጠን መመረት(የእንቁልጢ ስራ)፣ እንቁላል የሚያሳልፈው ትቦ በቂ ስፋት መኖር እና 

በማህጸን ግድግዳ ላይ ጽንስ ተመቻችቶ መቀመጥ መቻል አለበት። 

ከነዚህ ውስጥ አንዱ እንኳን ሲረበሽ ለማርገዝ መቸገርን ያስከትላል።

ከተለመዱት መንስኤዎች መካከል ቀጣዮቹ ይገኙበታል።

  • የእንቁላል ምርት መቀነስ ፡ ይህ የሚከሰተው ከሆርሞን መዛባት፣ የእንቁላል መጠን ማነስ እንዲሁም የእንቁልጢ የአለጊዜው  ስራ ማቋረጥ ሲኖር ነው።
  • የእንቁላል መተላለፊያ ቱቦ መጥበብ ወይም መደፈን
  • የማህጸን እጢ መኖር

በወንዶች ላይ የሚታዩ መንስኤዎች

  • የዘር ፍሬ ቁጥር አነስተኛ መሆን 
  •  የዘር ፍሬ እንቅስቃሴ በቂ ያለመሆን
  • አልኮል በከፍተኛ መጠን መጠቀም ፣ ትንባሆ ማጨስ እና ጫት መቃም
  • የሆርሞን መዛባት አብዛኛውን ጊዜ የሚታዩት መንስኤዎች ናቸው።

 

የመካንነት ምርመራ

ለሴት

የመካነት ምርመራ ለማድረግ ሁለቱም ጥንዶች ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ በሃኪም መታየት አለባቸው።

የሆርሞን ምርመራ፣ የእንቁላል ብዛትን ማጣራት፣ እንቁልጢን እና ማህጸንን በአልትራሳውንድ መመልከት እንዲሁም የቱቦውን ክፍት መሆን እና ጥበት ያለመኖሩን ለማጣራት በካሜራ መመልከት ለሴቶች ከሚደረጉ ምርመራዎች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

ለወንድ

ለወንዶች የሚደረጉ ምርመራዎች ፡ የዘር ፈሳሽ ምርመራ(የዘር ፍሬውን መጠን ፣ እንቅስቃሴ ፣ የአፈጣጠር ሁኔታ የሚያጣራ ምርመራ ነው)፣ የሆርሞን ምርመራ፣ የዘር ፍሬ አልትራሳውንድ ምርመራ ይገኙበታል።

 

የመካንነት ህክምና

ለመካንነት የሚሰጠው ህክምና በመንስኤው ላይ የተመሰረተ ነው። ከዚህ በተጨማሪ የጥንዶቹ እድሜ፣ ለማርገዝ የሞከሩበት ጊዜ እርዝመት እንዲሁም ከበቂ የምክር አገልግሎት በኋላ የሚመርጡት መንገድ ላይ ተመስርቶ ሃኪሙ የሚሰጣቸውን ምርመራ ይወስናል።

በአብዛኛው ጊዜ የሚሰጡት ህክምናዎች የሚከተሉት ናቸው።

  • የእንቁላል ምርትን የሚጨምሩ መድሃኒቶችን ለሴቷ መስጠት: እነዚህ ሆርሞንን የሚያካትቱ መድሃኒቶች በተለይም ከእንቁላል ምርት መቀነስ ጋር ተያይዞ የሚኖር መካንነትን ለማስተካከል ይረዳል
  • አይዩአይ (IUI) –  ይህ የወንዱን ዘር(ስፐርም) በመውሰድ ቀጥታ የሴቷ ማህጸን ውስጥ በመክተት የሚደረግ ህክምና ነው። አብዛኛውን ጊዜ በወንዱ ምክንያት የሚከሰት መካንነት ላይ ይጠቅማል።
  • ኤአርቲ (ART)-  አርቴፊሻል የሆነ የመካንነት ህክምና መንገድ ሲሆን በጣም የተለመደው አይቪኤፍ (IVF)የተሰኘውን መንገድ ያመላክታል። ይህ እንቁላል ከሰውነት ወጥቶ በላቦራቶሪ ውስጥ ከስፐርም ጋር በማገናኘት ጽንስን ፈጥሮ ከ3-5 ባሉት  ቀናት ውስጥ  ተመልሶ ወደ ሴቷ ማህጸን በመክተት የሚከናወን የህክምና  መንገድ ነው።