በዶክተር ቤተልሄም ተስፋስላሴ(ጠቅላላ ሀኪም)
By Dr.Bethlehem Tesfaselassie General Practitioner
Reviewed and Approved by Dr.Misikr Anberbir (Gynecologist/Obstetrician)
ማረጥ (Menopause) ምንድን ነው?
- ማረጥ ከእድሜ መጨመር ጋር ተያይዞ የሚመጣ ተፈጥሯዊ ሂደት ሲሆን ፤ ሴቶች የወር አበባ ማየት የሚያቆሙበት ጊዜ ነው።
- አንዲት ሴት አረጠች የሚባለው ለ 12 ወራት ወይም ለአንድ አመት እና ከዚያ በላይ የወር አበባ ሳታይ ስትቆይ ነው። ይህም የመውለጃ ግዜ ማብቃቱን ያመላክታል።
- አብዛኛዎቹ ሴቶች ከ 45 እስከ 55 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ማረጥ ያጋጥማቸዋል። ሆኖም ግን በአንዳንድ ሴቶች ላይ ማረጥ ከ40 አመት በፊት ሊከሰት ይችላል። ለዚህም የተለያዩ የጤና እክሎች መንስኤ ይሆናሉ።
- ማረጥ የሚከሰተው ኦቫሪ የሚባለው እንቁላል አምራች አካል ኢስትሮጅን (Estrogen )ማምረት ሲያቆም ነው። ኢስትሮጅን የወር አበባ ዑደትን ለመቆጣጠር የሚረዳ ሆርሞን (ንጥረነገር) ሲሆን ፤ የዚህ ንጥረ ነገር ማነስ በዚህ ወቅት ለሚታዩ የሰውነት ላይ ለውጦች መከሰት ዋነኛ ምክንያት ነው።
- የማረጥ ሽግግር ቀስ በቀስ ሆኖ አመታት ሊወስድ ይችላል። ይህ ሽግግር ብዙውን ጊዜ በወር አበባ ላይ ለውጦችን በማየት ይጀምራል። ለምሳሌ፦ የወር አበባ ከተለመደው በተለየ መልኩ ቶሎ ቶሎ መምጣት ወይም መዘግየት፣ በመጠን መብዛት ወይም ማነስ። ምንም እንኳን እነዚህ ምልክቶች ከማረጥ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ሊሆኑ ቢችሉም፤ የተለያዩ አሳሳቢ የጤና ችግሮች ተመሳሳይ ምልክት አላቸው። ስለዚህ አንዲት ሴት እነዚህን ምልክቶች ካየች ችላ ሳትል የጤና ባለሙያ ማማከር አለባት!
የወር አበባ ዑደት ከመቀየያር በተጨማሪ የማረጥ ሌሎች ምልክቶች ምንድን ናቸው?
- በፊት እና ላይኛው የሰውነት አካል ላይ የሚሰማ ድንገተኛ የሙቀት ስሜት እና ላብ ፦ይህ ስሜት ከጥቂት ሴኮንዶች እስከ ብዙ ደቂቃዎች ወይም ከዚያ በላይ ሊቆይ ይችላል። አንዳንድ ሴቶች በወር ውስጥ ጥቂት ጊዜ ሲያጋጥማቸው ሌሎች ደግሞ በቀን ውስጥ ብዙ ጊዜ።
- የእንቅልፍ ችግሮች፦ እንቅልፍ ማጣት (መተኛት መቸገግር) ወይም ከተለመደው ጊዜዎ በፊት መንቃት። የሌሊት ላብ እንቅልፍንም ሊረብሽ ይችላል።
- የብልት መድረቅ ፣ከዚህ ጋር ተያይዞ ኢንፌክሽኖች መጋለጥ እና በወሲብ ወቅት ህመም መሰማት
- የሽንት ቱቦ መቆጣት ፣ ቶሎ ቶሎ ሽንት መምጣት፣ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን መጋለጥ
- የአጥንት መሳሳት (ኦስቲዮፖሮሲስ)፦ከ 35 አመት በኋላ ትንሽ መጠን ያለው አጥንት መሳሳት በወንዶችም በሴቶችም ላይ የተለመደ ነው። ነገር ግን ከማረጥ በኋላ ባሉት የመጀመሪያዎቹ 4-8 ዓመታት ውስጥ በሴቶች ላይ የአጥንት መሳሳት ፍጥነት ይጨምራል። ይህ የሚከሰተው የኢስትሮጅን መጠን በመቀነሱ ሲሆን ለአጥንት ስብራት ያጋልጣል። አብዛኛውን ጊዜ የጭን ፣ የእጅ አንጓ እና የአከርካሪ አጥንቶች ይጎዳሉ።
- የመንፈስ ጭንቀት፣ ድባቴ መሰማት
- ኤስትሮጅን የልብ በሽታ (heart attack) እና በአንጎል ውሰጥ የደም መፍሰስን (stroke) ይከላከላል። ከማረጥ በኋላ የዚህ ንጥረነገር ማነስ የእነዚህ በሽታዎች ተጋላጭነትን ይጨምራል። ከዚህ ምክንያት በተጨማሪ ይህ የእድሜ ክልል ሌሎች ለልብ በሽታ የሚያጋልጡ ምክንያቶች (እንደ የአካል ብቃት መቀነስ ፣ ስኳር በሽታ፣ ከፍተኛ የኮሌስትሮል መጠን እና የደም ግፊት) የበዙበት ጊዜ ነው። እነዚህ ሁሉ ተጣምረው በማረጥ ላይ ባሉ ሴቶች ላይ የልብ በሽታ (heart attack) እና በአንጎል ውሰጥ ደም መፍሰስ (stroke) መከሰት እድልን ይጨምራሉ።
በማረጥ ጊዜ አንዳንድ ሴቶች የወር አበባ ማየት ከመቆም ውጭ ምንም ምልክት አይታይባቸውም ወይም ጥቂት ቀላል ምልክቶች ብቻ ይኖራቸዋል። ሌሎች ደግሞ ከባድ ሊሆኑ የሚችሉ ብዙ ምልክቶች አሏቸው። እነዚህ ምልክቶች ከሚፈጥሩት አካላዊ እና ስነ-ልቦናዊ ተፅእኖ የተነሳ ህክምና ሊያስፈልጋቸው ይችላል።
ማረጥ ተፈጥሯዊ ሂደት ስለሆነ ምንም ዓይነት ሕክምና አይጠይቅም ። ከዚህ ይልቅ ሕክምናዎች የሚያተኩሩት ምልክቶችን በማስታገስ እንዲሁም ከእድሜ መጨመር ጋር ተያይዘው ሊከሰቱ የሚችሉ ሥር የሰደዱ ሁኔታዎችን በመከላከል ወይም በማከም ላይ ነው።
የማረጥ ምልክቶችን እንዴት በራሳችን መቆጣጠር እንችላለን?
- በፊት እና ላይኛው የሰውነት አካል የሰውነት ላይ ድንገተኛ የሙቀት ስሜት ሲሰማ ቀዝቃዛ ውኃ መጠጣት ወይም ወደ ቀዝቃዛ ቦታ መሄድ እና ይህን ስሜት የሚቀሰቅሰው ምን እንደሆነ ለማወቅ መሞክር ያስፈልጋል። ለብዙ ሴቶች ትኩስ መጠጦች፣ ቡና (ካፌይን)፣ ቅመም ያላቸው ምግቦች፣ የአልኮል መጠጥ፣ ውጥረት(stress)፣ ሞቃታማ የአየር ጠባይ እና ሞቅ ያለ ክፍል ምልክቶቹን ያባብሳሉ።
- በቂ እንቅልፍ መተኛት ፣ ቡና ከመውሰድ መቆጠብ( እንቅልፍን ስለሚያደናቅፍ)
- የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፦ አዘውትሮ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የልብ ሕመምን፣ የስኳር በሽታን፣ የአጥንት መሳሳት እና እድሜ መግፋት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ሌሎች በሽታዎችን ለመከላከል ያስችላል።
- የተመጣጠነ ምግብን መመገብ፦ እነዚህም የተለያዩ ፍራፍሬዎችን፣ አትክልቶችንና ጥራጥሬዎች፣ የእንሰሳት ተዋፅኦዎች (ወተት እና የ መሳሰሉት) ያካትታል። ቅባት፣ ዘይትና ስኳር ገደብ ማበጀት። ጠንካራ አጥንትን ለመጠበቅ የሚረዳ በቂ ካልሲየም እና ቫይታሚን ዲ በአመጋገብ ውስጥ ማካተት።ካልሲየም ወይም ቫይታሚን ዲ የሚያስፈልግ ከሆነ መውሰድ።
- አለማጨስ፦ ማጨስ በልብ በሽታ፣ በአንጎል ውስጥ ደም በመፍሰስ፣ የአጥንት መሳሳት፣ በካንሰርና በሌሎችም የተለያዩ የጤና ችግሮች የመያዝ አጋጣሚያን ከፍ ያደርጋል።
- አልኮል መጠጥን መቀነስ
ከላይ ያየናቸውን ዘዴዎች ምልክቶቹን ካላስታገሱና የማረጥ ምልክቶች በአንዲት ሴት ላይ ተፅእኖ ካሳደሩ የሆርሞን ቴራፒ (ህክምና) ይደረጋል።
የሆርሞን ህክምና (Hormonal therapy) ምንድን ነው?
- ሆርሞን ህክምና ማለት ኤስትሮጅን የተባለውን ንጥረነገር በመድሀኒት መልክ ለብቻው ወይም ከሌላ ሆርሞን (ኘሮጀስትሮን) ጋር አጣምሮ የሚሰጥ ህክምና ነው።
- የሆርሞን ቴራፒ ማረጥ ምልክቶችን ለማስታገስ ይረዳል።
- ኤስትሮጅን በተለያዩ መልክ ሊሰጥ ይችላል። (እንክብሎችን፣ የቆዳ ላይ በሚለጠፉ ንጣፎችን ወዘተ)
- የብልት መድረቅ ብቻ ያጋጠማቸው ሴቶች ይህ መድሀኒት እዛው አካባቢ ላይ እንዲቀቡ ተደርጎ በክሬም መልክ ሊታዘዝ ይችላል።
የሆርሞን ህክምና ጥቅሞች ምንድ ናቸው?
- ድንገተኛ የሙቀት ስሜትን ለማስታገስ
- የብልትን መድረቅ እና በወሲብ ወቅት ህመም መሰማትን ለማስወገድ
- የአጥንት መሳሳት ለመከላከላል
- የተቀናጀ ኤስትሮጅንና ፕሮጄስቲን ሕክምና የአንጀት ካንሰርን አደጋ ሊቀንስ ይችላል። ሆኖም ግን የሆርሞን ቴራፒ የተወሰኑ የካንሰር ዓይነቶችን እና ሌሎች ሁኔታዎችን አደጋ ይጨምራል።
ከላይ ካየናቸው ህክምናዎች በተጨማሪ በአእምሮ ጤንነት ላይ ስለሚታዩ ለውጦች ከሐኪም ጋር መወያየት ተገቢ ነው። የቤተሰብ አካላዊ እና ሰነ-ልቦናዊ ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑንም መዘንጋት አይገባም።
በመጨረሻም በዚህ የእድሜ ክልል ውሰጥ ያለች ሴት ወደ ጤና ተቋም በመሄድ የተለያዩ የጤና ምርመራዎች እንድታደርግ ይመከራል። አነዚህም የደም ግፊት ፣ የስኳር መጠን መለካት፣ የተለያዩ የካንሰር ቅድመ ምርመራዎች ማድረግ (የጡት፣ የአንጀት፣ የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር…ወዘተ) ናቸው።
ምንጮች፦
The Menopause Years | ACOG
Menopause (who.int)
Menopause – Diagnosis and treatment – Mayo Clinic
የጤና ወግ
ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።
የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።
https://linktr.ee/Yetena_Weg