ዶ/ር ብሩክ አለማየሁ (የውስጥ ደዌ ስፔሻሊሰት)
መግቢያ
የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ19) ወረርሽ ከተነሳበት ጊዜ ጀምሮ በአለም ዙርያ በቫይረሱ ምክንያት ከ ስድሳ ሺ (60,000) በላይ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ እስካሁን ባለን መረጃ በቫይረሱ ምክንያት የሞተ ሰው በሀገራችን ባይኖርም በአህጉራችን አፍሪካ ከ280 በላይ ሰዎች ሞተዋል፡፡
ከዚህም የተነሳ በጤና ባለሙያዎችም ዘንድ ሆነ በማህበረሰቡ ውስጥ በኮቪድ ምክንያት የሚከሰትን ሞት በተመለከተና ከዚህም ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን እንዴት ማስተናገድ እንዳለብን ስጋቶችና ግርታዎች ተፈጥረዋል፡፡ በሀገራችን ኢትየጵያ ደግሞ አንድ ሰው ከሞተ በኋላ የሚከናወኑ በባህላችንና ወጋችን ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ሂደቶችና ክንውኖች አሉ፡፡ ስለዚህም ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያይዘው የሚነሱና ሊነሱ የሚችሉ ጥያቄዎችን ለመመለስ እንሞክራለን፡፡
በኮቪድ19 የሞተ ሰው ሬሳ ቫይረሱን/በሽታውን ሲያስተላልፍ ይችላል? ከሟቹ አካል አጠገብ መሆን አደጋ አለው?
- ስለኮቪደ19 ብዙ የማናውቃቸው እና ገና እየተማርናቸው ያሉ ነገሮች ቢኖሩም እስካሁን እንደሚታወቀው ኮቪድ19 የሚተላለፈው አንድ ሰው ሲያስል ወይም ሲያስነጥስ ከመተንፈሻ አካል በሚወጡና ቫይረሱን በያዙ የአየር ድሮፕሌቶች ወይም ቫይረሱ ያለበትን ግዑዝ አካል በእጅ ነክተን በእጃችን ደግሞ አፍ፣ አፍንጫ ወይም አይናችንን ስንነካ ነው፡፡
- ይህ ሁኔታ ደግሞ አንድ ሰው ከሞተ በኃላ አይከሰትም፡፡
- ሬሳው ባለበት ክፍል ውስጥ መሆን በቫይረሱ ለመያዝ ያጋልጣል ተብሎ አይጠበቅም፡፡
- ነገር ግን እንደ እጅን መታጠብ ያሉ መሰረታዊ ጥንቃቄዎችን መተግበር እና ሬሳው ከተወሰደ በኋላ ደግሞ እንደ የበር እጀታ፣ ጠረጴዛ እና ሌሎች ክፍሉ ውስጥ የነበሩ ቁሶችንም ማፅዳት ያስፈልጋል፡፡
ሬሳውን መንካት አይቻልም? ሬሳውን ማጠብ ፣ መገነዝ ፣ መቅበርስ?
- ሰዎች የሟቹን ሬሳ ላለመንካት መሞከር አለባቸው (በተለይ እድሜያቸው ከፍ ያለና ተደራራቢ በሽታዎች ያሉባቸው ሰዎች)፡፡
- በተለይ ሬሳው ሳይዘጋጅ (ሳይፀዳ)በፊት የሟቹን አካል መሳም፣ ማቀፍ ወይም እጁን መያዝ አይመከርም፡፡
- ከመገነዙ በፊት አካሉ መዘጋጀት/መፀዳት [መታጠብና ከተዋሃሲያን ነፃ (disinfect) መደረግ] አለበት፡፡
- ሬሳው የሚፀዳውና የሚገንዙ ሰዎች ቢያንስ የእጅ ጓንትና ማስክ እንዲያደርጉ ይመከራል፡፡
- ከሰውነት የሚወጣ/የሚፈናጠር ፈሳሽ እንደሚኖር የሚጠበቅ ከሆነ ደግሞ ሌሎች ራስን መጠበቅያ ቁሶች ሊያስፈልጉ ይችላሉ (የአይን መሸፈኛ መነፅር፣ የፊት መሸፈኛ እና ሌሎችም)፡፡
- አንዳንድ ሀገራት አካሉ በሬሳ ላስቲክ (leak-proof plastic body bag) ውስጥ እንዲከተትና የላስቲኩ ውጫዊ ክፍል እንደ በረኪና ባሉ ኬሚካሎች እንዲፀዳ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡
- ይህንን የሚያከናውን ሰው ከጨረሰ በኋላ እጁን በሳሙናና ውሃ ቢያንስ ለ20 ሰከንድ መታጠብ ወይም 60 በመቶና ከዚያ በላይ አልኮል ባለው ሳኒታይዘር እጅን ማፅዳት ያስፈልጋል፡፡
ሬሳውን ከአንድ ቦታ ወደሌላ ሲወሰድ ምን ጥንቃቄ ይደረግ?
- ሬሳው ትራንስፖረት በሚደረግበት ጊዜ የሚወስዱት ሰዎች ማስክና ጓንት ቢያደርጉ ይመከራል፡፡
- አድርሰው ከጨረሱ በኋላ ደግሞ የተጓጓዘበትን መኪና በአግባቡ በበረኪና ማፅዳት ይገባል፡፡
የቀብር ስነስርዓት ምን መምሰል አለበት ምን ጥንቃቄ ቢደረግስ ይመረጣል?
- ከተቻለ በቦታው የጤና ባለሙያ(ዎች) ቢኖር ጥሩ ነው፡፡
- በቀብር ስርዓት ወቅት ቫይረሱ ከሟቹ የመተላለፍ እድል ባይኖረውም የሟቹ ቤተሰቦች፣ የቅርብ ሰዎች እና ሌሎች ተሳታፊዎች በቫይረሱ ተይዘው ከሆነ ከአንዱ ወደ ሌላው ሊተላለፍ ይችላል፡፡
- የአሜሪካው CDC በመጀመሪያ (መጋቢት 19/2012) ቀብር ላይ ከ50 በላይ ሰዎች ባይገኙ ብሎ የነበረ ቢሆንም ከዚያ በኋላ ግን ከ10 ሰው እንዳይበልጥ መክሯል፡፡
- የሟች ቤተሰብ የሚመጡ ሰዎችን ቁጥር ከመቀነስ ባለፈም በስነ ስርዓቱ ላይ የ 2ሜትር አካላዊ መራራቅና የእጅ ንፅህና መጠበቅ ላይ ጥንቃቄ እንዲያደረጉ መክሯል፡፡
- ሟቹ የሞተው በሌላ ህመም ቢሆንም እንኳን እነዚህን ጥንቃቄዎች መተግበር አስፈላጊ ነው፡፡
- ቀበር አስፈፃሚዎች ከቀብሩ በኋላ እጃቸውን በደንብ መታጠብ አለባቸው፡፡
ለቅሶ ቤት እና ሌሎች ስነ ስርዓቶችስ?
- በሀገራችን አንድ ሰው ከሞተ በኋላ የተለያዩ ስነ ስርዓቶች እንደሚካሄዱ ይታወቃል፡፡
- እነዚህም ቀብር፣ እስከ ሰልስት ድረስ የሚደረግ የሀዘን ጊዜ፣ ከዚያም በኋላ ለሳምንታት ጎረቤት፣ ዘመድ፣ አዝማድ እየመጣ የሚጠይቅበትና የሚያስተዛዝንበት ባህል፣ የ40 ወይም የ80 ቀን መታሰብያ ፕሮግራሞች፣ የሀውልት ምረቃ እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡
- እነዚህ ስርዓቶች በባህሪያቸው ሰዎች የሚሰበሰቡባቸው እንደሆኑ ይታወቃል፡፡
- የተለያዩ ሀገራት በቀብር ሰዓት ላይ እንኳን የሰዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን እንዲቀነስና ሰዎች በማናቸውም ሁኔታ እንዳይሰበሰቡ ከልክለዋል፡፡
- በሀገራችንም ምንም እንኳ ከዚህ ቁጥር በላይ/በታች ተብሎ የተቀመጠ ግልፅ ገደብ ባይኖርም ስብሰባዎችን ማድረግ በመንግስት ተከልክሏል፡፡
- ከዚህ አንፃር እነዚህ ከላይ የተጠቀሱትን ስርዓቶች ማድረግ ምንም እንኳ የሟች ቤተሰብ እንዲፅናና እና እንዲበረታ ከማድረግ አንፃር በጣም ጠቀሜታ ያላቸው ዕሴቶች ቢሆኑም ከቫይረሱ ባህሪ እና በሽታው ተስፋፍቶ እንዳይሰራጭ ሲባል በዚህ ወቅት መደረጋቸው የሚመከር አይደለም፡፡
እነዚሀ ክልከላዎች ቢኖሩም የሟችን ክብር ለመጠበቅ፣ የቤተሰብንም ስሜት ለመረዳትና በተቻለ መጠን ለማስተናገድ እና ሀይማኖታዊ/መንፈሳዊ ፍላጎቶቻቸውን ሙሉ በሙሉ ላለመጋፋት በመንግስት፣ በባለሙያዎች እና በህግ አስከባሪዎች በኩል ጥንቃቄ ሊደረግና ከማህበረሰቡና ከሀይማኖት መሪዎች/አባቶች ጋር በቅንጅት መስራት ይገባል፡፡ ከእስልምናም ሀይማኖት አንፃርም ሆነ ከክርስትና የሀይማኖት መሪዎች በቂ የሆነ ምክርና አቅጣጫ ቢሰጡ መልካም ነው፡፡
የጤና ወግ
በመረጃ የተመሰረተ ሕክምና ብቻ ።
………………………………………………………………………………………………………………………..
ይህ የጤና ወግ ድረ ገፅ ነው።
ስለ ጤንነታችሁ ማወቅ የምትፈልጉትን መረጃ የምታገኙበት ፣ በህክምና ባለሙያዎች የሚዘጋጅ የመረጃ ምንጭ ነው።
ሁልግዜም ከሀኪማችሁ ተማከሩ፣ ተጨማሪ መረጃ ከፈለጋችሁ የኛን ድረ ገፅ ጎብኙ።
በጥናት የተደገፈ መረጃ ብቻ እናቀርባለን።
የህክምና ባለሙያዎች ለህሙማኖቻችሁ የሚሆን የሚነበብ መረጃ ከፈለጋችሁ ይህን ግፅ ጠቁሟቸው። ህሙማኖቻችሁ እንዲያውቁት የምትፈልጉትን ነገር መረጃ ጠቅሳችሁ ፃፉልን፣ ስምችሁን ጠቅሰን እናወጣለን። የህክምና ተማሪዎች እንዲጽፉ እናበረታታለን።
በተጨማሪም በጤና ወግ ፖድካስት፣ በ ዩትዩብ ፣በ ትዊተር ፣ በ ፌስቡክ ፣ በቴሌግራም የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ገፆቻችን ታገኙናላችሁ