By Yafet Abebe, 5th year medical student at myungsung medical collegeC2 

ያፌት አበበ (ሚዩንግሱንግ ህክምና ኮሌጅ የ5ኛ አመት ተማሪ)

Reviewed/Approved  by: Dr. Fitsum Tilahun (Editor at Yetena Weg/ Nephrologist)

 

ሥር የሰደደ የኩላሊት በሽታ ማለት ኩላሊቶች ሲጎዱ እና ደምን በሚፈለገው መጠን ማጣራት የማይችሉበት ሁኔታ ሲፈጠር ነው።

ሥር የሰደደ የኩላሊት በሽታ በማንኛውም ሰው ላይ ሊከሰት ይችላል። የበሽታው ሁኔታ ​​​​ከፍተኛ ደረጃ እስኪደርስ ድረስ ምልክት ሳያሳይ ብዙ ጊዜ ሳይታወቅ ሊቆይ ይችላል። ይህ የሚከሰተው የኩላሊት ተግባር በእጅጉ ሲቀንስ እና ጤናን አልፎ ተርፎም ህይወትን ለመጠበቅ የኩላሊት እጥበት ወይም የኩላሊት ንቅለ ተከላ በሚያስፈልግበት ጊዜ ነው።

ይህም የኩላሊት ተግባር ከመደበኛ የኩላሊት ተግባር 10 በመቶ ወይም ከዚያ በታች በሚሆንበት ጊዜ ነው። የህመሙ ደረጃ መለስተኛ ፣ መካከለኛ ወይም ከባድ ተብሎ ሊከፈል ይችላል። በሽንት ውስጥ አልቡሚን መኖሩ የኩላሊት ጉዳት መከሰቱን ያሳያል። ህመሙ መጀመሪያ ደረጃ ላይ ሲሆን የተወሰነ የኩላሊት ተግባር ይኖራል። የኩላሊት ውድቀት የሚከሰተው ህመሙ መጨረሻ ደረጃ ላይ ሲደርስ ብቻ ነው። የተለመዱት የCKD መንስኤዎች የስኳር በሽታ እና የደም ግፊት ናቸው። የሥር የሰደደ የኩላሊት በሽታ ህክምና ዋና ዐላማ የመጨረሻ ደረጃ የኩላሊት ህመምን ቀድሞ ለመከላከል ነው።

መደበኛ የኩላሊት ተግባር

ኩላሊቶቻችን ሁለት ወሳኝ ተግባራትን በሰዉነታችን ዉስጥ ያከናዉናሉ። እነዚህም፡-

1. ጎጂ እና መርዛማ ምርቶችን ማስወገድ

2. የውሃ ፣ ፈሳሾች ፣ ማዕድናት እና ኬሚካሎች ማለትም እንደ ሶዲየም ፣ ወዘተ ያሉ ኤሌክትሮላይቶችን ሚዛን ለመጠበቅ ያገለግላሉ።

ኩላሊት መርዛማ የሆኑ የቆሻሻ ምርቶችን እና ከመጠን በላይ ውሃን ከሰውነት በማስወገድ ሽንትን ያመርታል። በእያንዳንዱ ኩላሊት ውስጥ የተሠራው ሽንት በፊኛ ኩልት ቱቦ ውስጥ ያልፋል፤ ከዛም ወደ ፊኛ ይፈሳል። በመጨረሻም በሽንት ቧንቧ አማካኝነት ከሰውነት ይወገዳል።ይህ የመንጻት ሂደት “ኔፍሮን” ተብለው በሚታወቁት አነስተኛ የማጣሪያ ክፍሎች ውስጥ የሚከናወን ነዉ። እያንዳንዱ ኔፍሮን “በግሎሜሩልስ” እና “ትዩብዩልስ” የተሰራ ነው። እያንዳንዱ ኔፍሮን የመንጻት ሂደቱን በአግባቡ ለማከናወን ጤነኛ መሆን አለበት። በኩላሊቶች አማካኝነት የተሠራው ሽንት፤ በሽንት ቱቦዎች በኩል ወደ ሽንት ፊኛ ይወርዳል። በእያንዳንዱ ኩላሊት ውስጥ ከ 700,000 እስከ 1,000,000 ኔፍሮኖች ይገኛሉ። ብዙ የሰውነት ተግባራት በኩላሊት ትክክለኛ አሠራር ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ይህ የማጣራት ሂደት በትክክል እንዲከናወን የደም ግፊት እና ወደ ኩላሊት የሚሄደው ደም በቂ መሆን አለበት። የኔፍሮኖችን ቁጥር የሚቀንስ እንዲሁም አገልግሎታቸውን የሚያዛባ በሽታ ከጊዜ በሁላ ሥር ለሰደደ የኩላሊት በሽታ ይዳርጋል።

ሥር ለሰደደ የኩላሊት በሽታ አጋላጭ ሁኔታዎች 

የስኳር በሽታ

የደም ግፊት በሽታ

በኩላሊት በሽታ የተጠቃ የቤተሰብ አባል መኖር

ከመጠን ያለፈ ውፍረት

ሲጋራ ማጨስ

ዕድሜ መግፋት

በአፍሪካውያን እና በአፍሪካን አሜሪካውያን ላይ አንዳንድ ከዘር ጋር የተያያዙ (ጄነቲክ) ምክንያቶች

በሽንትዎ ውስጥ ፕሮቲን መኖር

ሥር የሰደደ የኩላሊት በሽታ ለምን ይዳርጋል?

ብዙ ሰው ላይ ሥር የሰደደ የኩላሊት በሽታ የሚገኘው በሌሎች ምክንያቶች የደም ወይም የሽንት ምርመራዎች ሲደረግ ነው። በደም ውስጥ የክሬቲንና ዩሪያ መጠን የኩላሊትን ጤንነት ደረጃ ያንፀባርቃሉ። ክሬቲኒን እና ዩሪያ በተለምዶ በኩላሊት በኩል ከደም የሚወገዱ ሁለት ተረፈ ምርቶች ናቸው። የኩላሊት ሥራ በሚቀዘቅዝበት ጊዜ የክሬቲን እና የዩሪያ የደም መጠን በአንጻሩ ይጨምራል። የፊት ፣ የሆድ እና የእግር እብጠት ብዙ ጊዜ የኩላሊት ህመም ማሳያ ነው። በኩላሊት ህመም ምክንያት የሚከሰት እብጠት አንድ ባህሪይ በመጀመሪያ ከዐይን ሽፋኖቹ በታች የሚስተዋል መሆኑ እና በማለዳ በጣም ጎልቶ መታየቱ ነው። ብዙ ጊዜ ህመምተኞች የሚያሳዩት የመጀመሪያ ምልክት የእግር እብጠት ነው።

በተጨማሪም ሥር የሰደደ የኩላሊት በሽታ ለማቅለሽለሽ እና ማስመለስ፣ ለምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ ለእግር እና የቁርጭምጭሚት እብጠት፣ ለከፍተኛ የደም ግፊት ፣ለትንፋሽ እጥረት እና ለደረት ህመም ይዳርጋል።

ሥር ለሰደደ የኩላሊት ህመም ምርመራዎች

የተለያዩ የኩላሊት ችግሮችን ለመመርመር ሐኪሙ ዝርዝር ታሪክ ይወስዳል። ሰውን በጥልቀት ይመረምራል ፣ የደም ግፊቱን ይፈትሻል። ከዚያም ተገቢ የኩላሊት ህመም ምርመራዎች እንዲደረጉ የሚያዝ ይሆናል።

የሽንት ምርመራ 

የተለያዩ ዓይነት የሽንት ምርመራዎች ፤ የተለያዩ የኩላሊት በሽታ ዓይነቶችን ለይቶ በዝርዝር ለማወቅ ጠቃሚ ፍንጮችን ይሰጣሉ።

መደበኛ የሽንት ምርመራ 

መደበኛ የሽንት ምርመራ ውጤት በኩላሊት ላይ ችግር እንዳለ ፍንጭ ሊሰጠን ይችላል ነገር ግን ውጤቱ ችግር ባያሳይም አንድ ሰው የኩላሊት ህመም የለበትም ለማለት አያስችለንም። በሽንት ውስጥ የፕሮቲን መኖር በተለያዩ የኩላሊት ህመም ላይ ይሥተዋላል፤ በመሆኑም በፍጹም ቸል ሊባል አይገባውም። በሽንት ውስጥ የፕሮቲን መኖር የመጀመሪያ እና ብቸኛው ሥር የሰደደ የኩላሊት ህመም (የልብ ህመምም ሊሆን ይችላል) የማስጠንቀቂያ ምልክት ሊሆን ይችላል።

•በሽንት ውስጥ ነጭ የደም ሴሎች መኖር የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን (UTI) መኖርን ሊያመለክት ይችላል።

• የፕሮቲን እና የቀይ የደም ሴሎች (አር.ቢ.ሲ) መኖር የኩላሊት ብግነት በሽታ መኖሩን አመላካች ነዉ።

ሌሎች የሽንት ምርመራዎች 

• የ24 ሰዓት የሽንት ምርመራ፦ የኩላሊት ህመም ላለባቸው ህሙማን፤ በሽንት በኩል የጠፋውን ፕሮቲን ትክክለኛ መጠን ለማወቅ ይህ ዓይነቱ ምርመራ አስፈላጊ ነው። ይህ ምርመራ የህመሙን ክብደት እንዲሁም በፕሮቲን መጥፋት ምክንያት የሕክምና ተጽዕኖ ደረጃን ለመገምገም ጠቃሚ ነው።

• የባክቴርያ እድገት ምርመራ ፦ ይህ ምርመራ ዩ.ቲ.አ.ይ የተባለውን የሽንት ቧንቧ የፈጠረውን ባክቴሪያ ዓይነት በተጨማሪም ለሕክምናው የአንቲባዮቲክስ ምርጫን በተመለከተ ጠቃሚ መረጃ ይሰጣል።

• አሲድ ፋስት ባሲላት የሽንት ምርመራ፡- ይህ ምርመራ የሽንት ቧንቧዎችን ነቀርሳ ለመመርመር ጠቃሚና አስፈላጊ ነው።

የደም ናሙና ምርመራዎች 

የተለያዩ የኩላሊት ህመሞችን በተገቢ ሁኔታ ለመለየት የተለያዩ የደም ናሙና ምርመራ ሂደቶች እጅጉን ወሳኝ ናቸው። በኩላሊት ህመምተኞች ላይ በተደጋጋሚ የሚከናወኑ የተለያዩ የደም ናሙና ምርመራዎች የሚከተሉት ናቸዉ። የደም ስኳር ፣ የደም ፕሮቲን ፣ ኮሌስትሮል ፣ ንጥረ ነገሮች (ሶድየም ፣ ፖታሲየም እና ክሎራይድ) ፣ ካልሲየም ፣ ፎስፈረስ ፣ ባይካርቦኔት ፣ ኤስኦ ታይተር ወዘተ።

የራዲዮሎጂ ምርመራዎች 

የኩላሊት አልትራሳውንድ  

ቀላል ፣ ጠቃሚ ፣ ፈጣን እና ደህንነቱ የተጠበቀ (የጨረር ተጋላጭነት የሌለው) ምርመራ ነው። ስለ ኩላሊት መጠን በተጨማሪም ዕጢዎች እና ጠጠሮች መኖር አለመኖራቸውን እና የመሳሰሉ ጠቃሚ መረጃዎችን ይሰጣል። አልትራሳውንድ ከዚህ በተጨማሪም፤ በሽንት ቧንቧው ውስጥ ያለው የሽንት ፍሰት መዘጋት እና አለመዘጋቱን መለየት ይችላል። በሥር ሰደድ የኩላሊት ህመም ወይም ኩላሊት ድክመት ደረጃ ላይ ሁለቱም ኩላሊት መጠናቸው አነስተኛ ሆኖ ሊገኝ ይችላል።

የሆድ ራጅ 

ይህ የምርመራ ዓይነት በሽንት ቧንቧ ስርዓት ውስጥ ጠጠሮች ከተከሰቱ ለመመርመር ጥቅም ላይ ይውላል።

የውስጥ የደም ቧንቧ ዩሮግራፊ 

የውስጥ የደም ቧንቧ ዩሮግራፊ ልዩ የራጅ ምርመራ ነው። በዚህ ምርመራ ውስጥ ቀለም (በራጅ ውጤቶች ላይ ሊታይ የሚችል ፈሳሽ) የያዘ የሬዲዮ አዮዲን በክንድ በኩል ወደ አንድ የደም ሥር ውስጥ ይገባል። ይህ ቀለም ከዚያ በኋላ በኩላሊቱ ውስጥ በማለፍ በሽንት በኩል ይወጣል። ይህ መላውን የሽንት ክፍል በዓይነ ሕሊናዎ እንዲታይ ያስችላል። እንደ ጠጠር ፣ አንዳች እክል ፣ ዕጢ ፤ ያልተለመዱ እና በኩላሊት መዋቅር እና ተግባር ውስጥ ያሉ ሌሎች ችግሮችን ጭምር ሊገልጽ ይችላል።

ቮይዲንግ ሲስቶዩሬትሮግራም 

ይህ ምርመራ በልጆች ላይ የሚመጣን የሽንት ቧንቧ ችግር የሚያሳይ ምርመራ ነው። በዚህ ምርመራ ውስጥ ቀለም (በራጅ ዉጤቶች ላይ ሊታይ የሚችል ፈሳሽ) የያዘ የሬዲዮ አዮዲን ይገባ እና ሽንት እንዲሸና ይደረጋል ፤ ከዚያ ራጅ ይነሳል። ይህ የሽንት ወደኋላ የመመለስ ህመምን ያሳያል።

ሌሎች ምርመራዎች

ሲቲ ስካን ፣የኩላሊት ደም ሥር አልትራሳውንድ፣ሬድዮ ኒኩለር ጥናት፣አንጂዮግራፊ እና የመሳሰሉት

የኩላሊት ባዮፕሲ

በኩላሊት ባዮፕሲ ወቅት አንድ ትንሽ የኩላሊት ቁራጭ በመርፌ ተወስዶ በአጉሊ መነጽር ምርመራ ይደረጋል። የኩላሊት ባዮፕሲ የአንዳንድ የኩላሊት ህመሞችን ትክክለኛ መንስኤ ይመረምራል። የኩላሊት ባዮፕሲ የተወሰኑ ያልታወቁ የኩላሊት በሽታዎች ልዩ መንስዔ ያወጣል። የኩላሊት ህመም ባለሙያው በዚህ መረጃ ውጤታማ የሕክምና ስትራቴጂ ማቀድ እና ህመምተኞችን እና ቤተሰቦቻቸውን በማሳተፍ ስለህመሙ ክብደት እና ሂደት በመከተል መምራት ይችላል።

ስር የሰደደ የኩላሊት ህመም ሕክምና

ስር የሰደደ የኩላሊት ህመም ፈውስ የለውም። ከፍተኛ የሆነው ስር የሰደደ የኩላሊት ህመም ደግሞ ሕይወትን ለማስቀጠል የኩላሊት እጥበት ወይም ንቅለተከላ ያስፈልገዋል። ስለዚህም ቀደም ብሎ ህመሙን ማግኘት እና ጥንቁቅ የሆነ የመድኃኒት ሕክምና ማድረግ ብቸኛ አዋጪ እና ውድ ያልሆነ የበሽታው መፍትሔ ሲሆን የኩላሊት እጥበትንና ንቅለ ተከላን አስፈላጊነትም ያዘገያል።

በስር የሰደደ የኩላሊት ህመም ውስጥ የደም ግፊት ቁጥጥር ዓላማ

አልፎ አልፎ የሚደረግ የሀኪም ክትትል የደም ግፊትን ሁኔታ ለማወቅ ያስችላል። ነገር ግን፤ በስር የሰደደ የኩላሊት በሽታ ውስጥ የደም ግፊት መለኪያን ገዝቶ በመደበኛነት ቤት ውስጥ መለካት የደም ግፊትን ለመከታተል እና ለመቆጣጠር የበለጠ ይረዳል። አንጅዮቴንሲን ኮንቨርቲንግ ኢንዛይም ኢንሂቢተርስ እና አንጅዮቴንሲን ሪሰፕተር ብሎከርስ በቅድሚያ የሚመረጡ ደም ግፊትን ለመቀነስ የሚረዱ እንዲሁም የኩላሊትን የጉዳት ሂደት በመቀነስ ኩላሊትን የሚጠብቁ መድኃኒቶች ናቸው። ሆኖም ግን ማንኛውንም መድሀኒት ከመውሰድ በፊት ሀኪምን ማናገር ያስፈልጋል። ይህም አንዳንድ የኩላሊት በሽታን ሊያባብሱ የሚችሉ መድሀኒቶችን ከመውሰድ ይታደገናል።

በስር የሰደደ የኩላሊት ህመም ውስጥ ለምን ደም ማነስ ይከሰታል እና ህክምናውስ እንዴት ነው?

ኩላሊቶች በተገቢው ሁኔታ በሚሰሩ ጊዜ የአጥንት መቅኔ ቀይ የደም ሴሎች እንዲያመርት የሚረዳ ኢሪትሮፖይቲን የሚባል ሆርሞን ያመነጫሉ። በስር የሰደደ የኩላሊት ህመም ጊዜ የኩላሊት የመስራት አቅም ሲቀንስ የኢሪትሮፖይቲንም ምርት ይቀንሳል ፤ ይኼም ለደም ማነስ ይዳርጋል። የአይረን ኪንኖች ፣ ቫይታሚኖች አንዳንዴም በደም ስር የሚሰጥ አይረን በመጀመሪያ ደረጃ በስር የሰደደ የኩላሊት ሕመም ምክንያት ለሚመጣ ደም ማነስ ይሰጣሉ።

ከባድ ለሆነ ወይም በመድኃኒት ለማይመለስ ደም ማነስ ኦክስጅን የሚሸከሙ ቀይ ደም ሴሎች እንዲሰሩ የሚረዳ ሰው ሰራሽ ኢሪትሮፖይቲን በኢንጀክሽን መልክ መስጠት ያስፈልጋል።

 

ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።

የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።

https://linktr.ee/Yetena_Weg