በ ዶ/ር አቤል ተዘራ አበበ (ጠቅላላ ሐኪም)

By: Dr. Abel Tezera Abebe ( General Practitioner)

Reviewed By Dr Hermon Amare, Psychiatrist

📌 የሚከተለው ፅሁፍ የአንዳንድ አንባቢዎችን ስሜት ሊረብሽ የሚችል ይዘት ስለሚኖረው ህፃናት እና የስነ ልቦና ውጥረት ያለባቸው ግለሰቦች እንዲያነቡት አይመከርም።

 

በህክምና ት/ቤት ውስጥ ራሴን ባጠፋ ይሻለኛል የሚሉ ዛቻዎች ከፍ ሲልም ራስን ለማጥፋት የሚደረጉ ሙከራዎችን ማየት የተለመደ ነው። አሁን አሁን  ደግሞ ከተለያዩ የህብረተሰብ  ክፍሎች ራስን የማጥፋት ሙከራ የሚያደርጉ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ ይገኛል። ከነዚህም ውስጥ እስከወዲያኛው የሚያሸልቡም ጥቂት አይደሉም።

ለመሆኑ ራስን ማጥፋት ምን ያህል አሳሳቢ ጉዳይ ነው? ምክንያቶቹ እና መከላከያ መንገዶቹስ ምን ምንድን ናቸው?

እንደ የዓለም አቀፍ  የጤና ድርጅት መረጃ መሰረት በየአመቱ ከ 800 ሺህ በላይ ሰዎች ራሳቸውን ሲያጠፉ ቁጥራቸው ከዚህም በላይ የሆኑ ሰዎች ደግሞ የራስ ማጥፋት ሙከራን ያደርጋሉ።

መረጃው አያይዞም ከ 15 እስከ 29 አመት የእድሜ ክልል ከሚገኙ ሕብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ራስን ማጥፋት አራተኛው የሞት መንስኤ እንደሆነ ያስቀምጣል። በተጨማሪም በአለም ላይ ራሳቸውን ከሚያጠፉ ሰዎች መካከል ከሶስት አራተኛ በላይ የሚገኙት በዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ውስጥ ነው።

የኢትዮጲያ ህክምና ማህበር ባወጣው ጥናት መሰረት በምስራቅ አፍሪካ ራስን የማጥፋት አሀዝ በአመት ከ100 ሺህ ህዝብ ከ 5 እስከ 15  ሲሆን በኢትዮጵያ ደግሞ ከ 100 ሺህ ህዝብ ውስጥ 9 ያህሉ ራሳቸውን እንሚያጠፉ ያስነብባል። ይህም ማለት በየቀኑ 30 የሚሆኑ ሰዎች ራሳቸውን ሲያጠፉ ቢያንስ 150 ሰዎች ደግሞ የሚወዷቸውን ማጣት በሚያስከትለው መዘዝ ቀሪ ህይወታቸውን ይገፋሉ።

 

ራስን የማጥፋት ምክንያቶች

በአብዛኛው የሚጠቀሱት ራስን የማጥፋት ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፣

  • ከዚህ በፊት የነበረ ራስን የማጥፋት ሙከራ
  • ድባቴ (depression) ፣ ጭንቀት እና የመሳሰሉ የአእምሮ የጤና እክሎች
  • የሲጋራ ፣ አልኮል እንዲሁም የተለያዩ እጾች ሱስ
  • አካላዊ ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ውጥረቶች ለምሳሌ :- የእድሜ ልክ ህመሞች ፣ ፍቺ ፣ ስራ አጥነት ፣ጾታዊ ትንኮሳ እንዲሁም ድንገተኛ የሆኑ አሳዛኝ እና አስደንጋጭ ክስተቶች
  • ለጦር መሳሪያ ቅርበት ያላቸው ግለሰቦች

 

ተጎጂ የህብረተሰብ ክፍሎች

ራስን ማጥፋት የትኛውንም ማህበረሰብ እንዲሁም የትኛውንም ግለሰብ ሊያጠቃ የሚችል ቢሆንም በአብዛኛው ግን በአስራዎች ውስጥ የሚገኙ ታዳጊዎች እና በሃያዎቹ ውስጥ ያሉ ወጣቶችን የበለጠ ሲጎዳ ይታያል።  ይህም የሆነው በተለያዩ ሱሶች ከመጠመድ ፣ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን ከመጋፈጥ አንፃር ወጣቶች ግንባር ቀደም ሚና ስለሚጫወቱ ነው።  ከዚህ ጋር ተያይዞም በአፍላነት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚታዩት ስሜታዊነት ፣ ቶሎ ተስፋ የመቁረጥ እና ግራ የመጋባት ባህርያት ጉዳቱን የበለጠ ያባብሱታል።

ማግለል እና መድሎ የሚደርስባቸው የህብረተሰብ ክፍሎችም እንዲሁ ራስን ለማጥፋት ተጋላጭ የሆኑ ናቸው። በተለይ የአእምሮ ህመም ያለባቸው ሰዎች ከሚደርስባቸው መገለል አንፃር ራሳቸውን ሲደብቁ እና ከማህበረሰቡ ሲለዩ ይስተዋላል። ይህም በተዘዋዋሪ የበለጠ ህመሙን በማባባስ ለራስ ማጥፋት ሙከራ እና ህልፈት ይደረጋል።

ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ ጊዜያዊ ማቆያዎች ውስጥ ያሉ ስደተኞች እና ተፈናቃዮች እንዲሁም በማረሚያ ቤት ውስጥ ያሉ ግለሰቦች የበለጠ ተጋላጭ እንደሆኑ ይገለፃል።

 

ባህል እና ቴክኖሎጂ ራስን ለማጥፋት ምክንያት ወይስ መፍትሄ?

 እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ጠንካራ ሀይማኖታዊ እና ማህበራዊ ኑሮ በሚስተዋልባቸው ሀገሮች ውስጥ ራስን የማጥፋት አሃዝ ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲነፃፀር አናሳ ነው። ነገር ግን ከከተማ መስፋፋት እና ዘመናዊነት ጋር በተያያዘ አብሮ መኖር ፣ መደጋገፍ እና መጠያየቅ የምንላቸው እሴቶች እየተሸረሸሩ በተቃራኒው ደግሞ ብቸኝነት ፣ ጭንቀት እና ውጥረት ለተለያዩ የአእምሮ ቀውሶች ሲበረታም ራስን ለማጥፋት ምክንያት ሲሆኑ ይታያል።

በቀን ከአምስት ሰአታት በላይ በተንቀሳቃሽ ስልኮች ስክሪን ላይ ማሳለፍ ለጭንቀት እና ሌሎች ተያያዥ የአእምሮ እክሎች እንደሚያጋልጥ ጥናቶች ያሳያሉ። ከዚሁም ጋር በተያያዘ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚቀርቡት አሉታዊ ይዘት ያላቸው መልእክቶች ጉዳዩን የበለጠ ያባብሱታል።  በተቃራኒው ደግሞ ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ በመጠቀም ማህበረሰቡን ከብቸኝነት ፣ ጭንቀት እና አላስፈላጊ የአእምሮ መበከል ለመታደግ የሚጥሩ ፤ ተጎጂዎችንም ተገቢውን የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያበረታቱ የሚዲያ አካላት ፣ የጤና ባለሙያዎች እና በጎፈቃድ ግለሰቦች በርካታ ናቸው።

 

መከላከያ መንገዶች

– ከዚህ ቀደም ራስን የማጥፋት ሙከራ ያደረጉ ሰዎችን ወይም ሌሎች ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከ ጦር መሳርያዎች ፣ ፀረ-ተባይ መድሀኒቶች እና ሌሎች ራስ ላይ ጉዳት ከሚያደርሱ ነገሮች ማራቅ

–  የራስ ማጥፋት ሙከራ ያደረጉ ሰዎችን አስፈላጊ የሆነ የህክምና እርዳታ እንዲያገኙ መድረግ

– በተለያዩ ሱሶች ውስጥ የተዘፈቁ እንዲሁም ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ውጥረት ውስጥ ያሉ የማህበረሰብ ክፍሎችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የህክምና ፣ የፋይናንስ እና ሌሎች ዘለቄታዊ መፍትሄዎችን መፈለግ

– የመገናኛ ብዙሀንን በመጠቀም በተለይ ወጣቶች እና ተጋላጭ ግለሰቦች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎችን መመስራት

 

በአጠቃላይ ራስን ማጥፋት በአመት ለመቶ ሺዎች ህልፈት ምክንያት ከመሆኑም በላይ አምራች የሆነውን ወጣቱን የህብረተሰብ ክፍል በመጉዳት የሚያሳድረው ማህበራዊ እና ሀገራዊ ጫና አጅግ አስከፌ ነው። ለዚህም እያንዳንዱ የማህበረሰብ ክፍል ከሚዲያ ተቋማት ፣ ከመንግስት አካላት እና ከጤና ባለሙያዎች ጋር በመሆን በጋራ ልንከላከለው የሚገባ ጉዳይ ነው።

 

ቸር ቆዩኝ

 

ዋቢ

  1. World Health Organization. (2021). Suicide. Retrieved from https://www.who.int/news-room/fact-sheets/detail/suicide
  1. Centers for Disease Control and Prevention. (2020). Suicide Prevention. Retrieved from https://www.cdc.gov/suicide/index.html

3. Suicide: What can doctors do?- Ethiopian Medical Association https://www.ethiopianmedicalass.org/suicide-what-can-doctors-do/#

  1. Bifftu BB, Tiruneh BT, Dachew BA, Guracho YD. Prevalence of suicidal ideation and attempted suicide in the general population of Ethiopia: a systematic review and meta-analysis. Int J Ment Health Syst. 2021 Mar 24;15(1):27. doi: 10.1186/s13033-021-00449-z. PMID: 33761982; PMCID: PMC7992356.
  2. Yohannes K, Gezahegn M, Birhanie M, Simachew Y, Moges A, Ayano G, Toitole KK, Mokona H, Abebe L. Suicidality and homelessness: prevalence and associated factors of suicidal behaviour among homeless young adults in Southern Ethiopia. BMC Psychol. 2023 Apr 18;11(1):121. doi: 10.1186/s40359-023-01162-x. PMID: 37072864; PMCID: PMC10111304.
  3. Habtamu E, Desalegn D. Suicidal behavior and associated factors among prisoners in Dilla town, Dilla, Ethiopia 2020: An institutional based cross-sectional study. PLoS One. 2022 May 11;17(5):e0267721. doi: 10.1371/journal.pone.0267721. PMID: 35544553; PMCID: PMC9094534.
  4. Youth Suicide Research Consortium https://www.youthsuicideresearch.org/blog/youth-and-digital-technology-useblog/youthresearchorg