Written by : ኤፍራታ አንበርብር-የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የ5ተኛ ዓመት የሕክምና ተማሪ )

Approved by: ዶ/ር የፍሬዘር ገዛኸኝ (ሳይካትሪ ሬዚደንት)

 

ሱስ ምንድነው?

  ሱስ ማለት በተደጋጋሚ እና ቋሚ ሊባል በሚቻል መልኩ ለረጅም ጊዜ የሚደረግ እና በአንድ ነገር ላይ አካላዊ፣ ባህርያዊ እና ስነልቦናዊ ጥገኝነትን የሚያሳይ የአዕምሮ ሕመም ነው። ሰዎች ከተለያዩ ነገሮች ሱስ ሊይዛቸው ይችላል። በዋነኝነት የሚጠቀሱት የንጥረ ነገር (Substance) ሱሶች ለምሳሌ:- እንደ አልኮል፣ ጫት፣ ሲጋራ፣ የተለያዩ አደንዛዥ እና አነቃቂ እፅዋት እንዲሁም መድሃኒቶች ሲሆኑ ከእነዚህ ባልተናነሰ መልኩ ሰዎች እንደቁማር፣ ቴክኖሎጂ እና የመሳሰሉ የባህርይ ሱሶችም ውስጥ ሊወድቁ ይችላሉ። በዚህ ጽሑፍ ላይ በስፋት የምናየው ስለንጥረ ነገር ሱስ (Substance use disorder) ይሆናል። 

 

ሰዎች ለምን ወደሱስ ይገባሉ?

  በአገራችን ብሎም በአለማችን የተስፋፋው የሱስ ችግር በአብዛኛው በወጣቶች ላይ ይስተዋላል። ከእድሜያቸው ጋር ተያይዞ የሚመጣው ነገሮችን የማወቅና የመሞከር ጉጉት እንዲሁም የአካባቢያዊ እና የአቻ ተፅእኖ በዋነኝነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ምክንያቶች ናቸው። ለመነቃቃት፣ ከድብርትና ከጭንቀት ስሜት ለመላቀቅ፣ የደስታና የመዝናናት ስሜትን ለመፍጠር፣ ሕመምን ለማስታገስ እና ጊዜ ለማሳለፍ የሚሉት ምክንያቶች ሰዎች በአብዛኛው ሱስ ውስጥ ለመግባታቸው የሚያስቀምጧቸው ናቸው። 

  ከዚህም በተጨማሪ ሱሰኝነት ከስብዕና እና ከሌሎች የተለያዩ የአዕምሮ ችግሮች ጋር በእጅጉ የተሳሰረ ነው። ይህም ማለት የተለያዩ የአዕምሮ ሕመም ያለባቸው ሰዎች ሱስ ውስጥ ለመግባት በከፍተኛ ሁኔታ የተጋለጡ ናቸው። በተመሳሳይ ሁኔታ ደግሞ በሱስ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ለተለያዩ ተጓዳኝ የአዕምሮ ሕመሞች የመጋለጥ እድላቸው ሰፊ ነው። 

 

የሱስ ምልክቶች ምንድናቸው?

  ከላይ እንደተጠቀሰው አንድ ሰው አንድን ንጥረ ነገር (Substance) ለረጅም ጊዜ በተደጋጋሚ ሲጠቀም እና በዛ ንጥረ ነገር ላይ በአካል፣ በባህርይ እና በስነልቦና ጥገኛ ሲሆን ሱሰኛ ይባላል። እሱ ራሱ ድርጊቱንና ውሳኔውን ከሚቆጣጠረው በላይ ሱሱ አዕምሮውን ስለሚቆጣጠረው ለማቆም ቢፈልግ እንኳን እጅግ ከባድ ይሆንበታል። ሱስ ያለበት ሰው የሚያሳያቸው ምልክቶች እንደሚጠቀመው ነገር ሊለያዩ ቢችሉም ጠቅለል አድርገን ስናያቸው ግን የሚከተሉትን ይመስላሉ። 

  • ሱሱን ለመጠቀም (ለማስታገስ) ከፍተኛ ጊዜ ማጥፋት

  • ለማቆም ወይም ለመቀነስ መቸገር

  • አምጣ አምጣ የማለት ስሜት

  • ለማቆም ወይም ለመቀነስ በሚሞክርበት ጊዜ የተለያዩ አካላዊ የሆኑ የሕመም ምልክቶችን ማሳየት

  • የንጥረ ነገሩን መጠን በየጊዜው መጨመር

  • የአካል እና የአዕምሮ ጤና መቃወስ እንደሚያስከትል እያወቁ መጠቀም

  • የስራ እና የትምህርት መስተጓጎል

  • ሃላፊነቶችን አለመወጣትና ማህበራዊ ቀውስ ውስጥ መግባት

  • ከቤተሰብ፣ ከጓደኛ እና ከስራ ባልደረባ ጋር ጤናማ ያልሆነ ግንኙነት ውስጥ መግባት

  • ንጥረ ነገሮቹን ተጠቅሞ ሕይወትን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ድርጊቶችን ማከናወን። ለምሳሌ:- መኪና መንዳት

 

ከሱስ መላቀቅ  ይቻላል?

  አዎ ይቻላል! ማንኛውም አይነት ሱስ ያለበት ሰው ተገቢው የስነአዕምሮ ሕክምና ክትትል ከተደረገለት ሙሉ በሙሉ ማገገም እና መላቀቅ ይችላል። ሆኖም ግን ከሚያደርገው የሕክምና ክትትል በላይ የራሱ ዝግጁነት እና ቁርጠኝነት እጅግ አስፈላጊ ነው። 

  ከሱስ ለመላቀቅ ከሚደረገው የስነአዕምሮ ሕክምና በዋነኝነት የሚሰጠው የንግግር ሕክምና (Psychotherapy) ነው። ይህም አንድ ሱሰኛ ሰው ከሱሱ ለማገገም በሚያደርገው ጉዞ በእጅጉ ያግዘዋል። ከዚህ በተጨማሪም አንድ ሰው የአንድ ንጥረ ነገር ሱሰኛ (ጥገኛ)ሲሆን ሰውነቱ በከፍተኛ ሁኔታ ይህን ንጥረ ነገር ስለሚላመደው ለማቆም ወይም ለመቀነስ በሚሞክርበት ጊዜ የተለያዩ የሕመም ምልክቶች (Withdrawal Symptoms) ሊያሳይ ይችላል። ለምሳሌ አንድ የአልኮል ሱስ ያለበት ሰው ሰውነቱ የለመደውን መጠን ያህል አልኮል ካላገኘ የመንቀጥቀጥ፣ የመቃዠት፣ ለሌሎች የማይታዩ/ የማይሰሙ ነገሮችን ማየት/መስማት እና የመሳሰሉ ምልክቶችን ሊያሳይ ይችላል። ስለዚህም ከንግግር ሕክምናው (Psychotherapy) በተጨማሪ እነዚህን ምልክቶች በመድሃኒት ማከም አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። ከነዚህም በተጨማሪ ለሱስ የሚጋብዙ ሁኔታዎችን ለይቶ ማወቅ እና ከእነሱም መራቅ የማገገም ሒደቱን ሊያግዝ ብሎም ከሱሱ ከወጡ በኋላ እንዳያገረሽ ሊከላል ይችላል። 

 

የጤና ወግ 

ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።

የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።

https://linktr.ee/Yetena_Weg