በ ዶ/ር ኤልሮኢ አሹሮ (ሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅ እጩ ሀኪም /intern)
ይህ ችግር ሊያሳስበን የሚገባ ነው??
በእኔ የስራ ልምድ internship ከጀመርኩ ሶስት ወር ባይሞላኝም ከሶስት የሚበልጡ የስኳር ታካሚዎች በእግር ላይ ስጋ የሚሞትበት ቁስል (gangrene) መጥተው እጣፈንታቸው መቆረጥ ሆኖ ታዝቤያለሁ።
የስኳር በሽታ ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ውስጥ የሚመደብ በሰውነታችን ውስጥ ያለው የስኳር(glucose) መጠን ከሚፈለገው በላይ ሲጨምር የሚፈጠር በሽታ ነው።
ሀገራችን ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሀራ በታች ባሉ ሀገራት በስኳር ምክንያት የሚመጡ የጎንዮሽ ጉዳቶች በዋናነት ቶሎ ችግሩን ካለማወቅና መፍትሄ ካለመውሰድ የሚመጡ ናቸው።አብዛኛው ታካሚ ወደ ህክምና ተቋም የሚመጣው ከረፈደ በኋላ ነው።ይህም ከግንዛቤ እጥረት አልያም ችላ ከማለት የሚመጣ ነው።
የስኳር በሽታ ከሚያስከትላቸው ጉዳቶች ውስጥ አንዱ የእግር ቁስለት (diabetic foot ulcer) ነው። የእንድ የስኳር በሽተኛ ለዚህ ችግር የእድሜ ልክ ተጋላጭነት 25% ነው።
ይህ በሽታ ከአደጋ ውጪ ለሚፈጠር የእግር መቆረጥ ቀዳሚ ምክንያት ነው።እንዲሁም ለረጅም ግዜ በሆስፒታል መቆየትን ያስከትላል።
በስኳር ህመም ምክንያት የሚመጣ የእግር ቁስለት በሰውነታችን ያለው የስኳር መጠን ያለአግባብ በመብዛቱ ምክንያት በተለያዩ የሰውነታችን አካላት ላይ በሚያደርሰው ጉዳት የሚመጣ ለረጅም ግዜ የሚቆይ እግርን የሚያጠቃ ቁስለት ነው። እነዚህ አጋላጭ መንስኤዎችም፤
- የነርቭ መጎዳት(Diabetic Neuropathy) – ይህ የነርቭ መጎዳት ችግር እንደተፈጠረ የሚያመለክቱንን ስሜቶች ማጣት ሲሆን በእኩል ደረጃ ከታችኛው የእግር ጣቶች ተነስቶ ወደ ላይ የሚሄድ በጊዜ ሂደትም እጅን የሚያጠቃ ችግር ነው።
- ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ችግር መጠቃት ወይም የእግር መቆረጥ
- በእግር ላይ አደጋ ማጋጠም
- ወደ እግር የሚሄድ የደም ቱቦ መጥበብን ተከትሎ የሚመጣ በቂ ደም ያለመሄድ (Peripheral arterial disease)
- የእግር ትክክለኛውን ቅርፅ ማጣት (Foot deformity)
አንድ የስኳር በሽተኛ ለዚህ በሽታ ተጋላጭ መሆኑን እንዴት ሊያውቅ ይችላል?
- ለረጅም ግዜ ከቆየ ጫና ወይም ሀይል የሚመጣ የወፈረ ቆዳ ፤ ይህ ቦታ በመሰንጠቅ ምክንያት የተለያዩ ህዋሳት በመግባት የመበከል እድል አለው።
- የእግር ትልቁ ጣት መጋጠሚያ አጥንት ቦታውን ለቆ መገፋት እና ቅርፅ ማጣት (Bunion)
- ከውጫዊ ሀይል መብዛት የሚመጣ የጣት ቅርፅ መበላሸት (Hammer toe)
- የእግር ትልቁ ጣት ጥፍር ወደ ውስጥ ማደግ
Bunion Hammer toe
አንድ የስኳር በሽተኛ ምን አይነት ምልክቶች ሲያይ ወደ ህክምና ቦታ በአስቸኳይ መሄድ ይኖርበታል?
- እግሩ ላይ ትንሽም ሆነ ትልቅ አደጋ ሲደርስበት፦ የመቆረጥ፣ የመሰንጠቅ፣ የመመታት፣ የመጋጨት
- የህመም ስሜት ሲሰማው፦ የመጠዝጠዝ፣ የማቃጠል፣ የመደንዘዝ፣የመውጋት
በተጨማሪም ከታካሚው የሚጠበቁ እርምጃዎች
- መድሀኒትን በአግባቡ በመውሰድ የስኳር መጠንን መቆጣጠር እና የተመጣጠነ ምግብ መመገብ
- በየቀኑ የእግር ሁኔታን መከታተል፦ አለመድረቁን፣ ያልታወቀ ጉዳት አለመድረሱን
- ጠባብ ጫማዎችን ከማድረግ መቆጠብ
- በባዶ እግር አለመራመድ
- ካልሲን በንህፅና መጠቀም እና በየቀኑ መቀየር
- ሲጋራ አለማጨስ
- የእግር ጥፍሮችን በአግባቡ መቆረጥ
- ለብ ባለ ውሀ እግርን በየቀኑ መታጠብ ከዚያም በቅባት ማለስለስ
- አንዴ ከተፈጠረ ድጋሚ እንዳይፈጠር ቁስሉን በሚገባ መሸፈን ፣በየወሩ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ክትትል በማድረግ
በሀገራችን ኢትዮጵያ ያለው ስርጭት ቢለያይም ከ1.5% – 30% ይደርሳል። በስኳር በሽታ ምክንያት የሚመጣ የእግር ቁስለት አንዴ ከተፈጠረ ድጋሚ የመፈጠር እድሉ
በአንድ አመት ውስጥ 40%
በሶስት አመት 60%
በአምስት አመት 75% ነው።
ይህ አሃዝ ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለብን ያሳስበናል።
ወንዝ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው እንደሚባለው የስኳር በሽታም ሆነ በሱ ምክንያት የሚመጣው የእግር ቁስለት ያለ ሳይመስል ጉዳቱ ስር የሚሰድ ችግር ነውና ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
ዋቢ/ References
- Harrison’s principles of internal medicine(20th edition), 2018
- uptodate.com 3.40.5 accessed on November 2021
- Medscape – Diabetic foot ulcer
- Tolossa T, Mengist B, Mulisa D, Fetensa G, Turi E, Abajobir A. Prevalence and associated factors of foot ulcer among diabetic patients in Ethiopia : a systematic review and meta-analysis. 2020
ይህ ፅሁፍ በዶ/ር ቃልኪዳን አላቸው (የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት/ኢንዶክሪኖሎጂስት) እና የጤና ወግ ኤዲተሮች የተገመገመ ነው።