ኢትዮጵያ ውስጥ የተላላፊ በሽታዎች ህክምናን የሚፈታተኑ 10 ምልከታዎች
Tweet
10 things challenging treatment and prevention of infectious diseases in Ethiopia
- ያለ ሀኪም ትእዛዝ መድሀኒት ገዝቶ መጠቀም
ብዙ ባለሙያዎች ባደረጉት ጥናት መሰረት ህብረተሰባችን ያለ ሀኪም ትእዛዝ መድሀኒት የመጠቀም ልምዱ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህንን የሚመሰክር ጥናት ለማንበብ ይሄን ሊንክ ይጫኑ ፡፡ በተለይም ደግሞ የፀረ ተህዋስያን መድሀኒቶች (antibiotics) ተገቢውን ማዘዣ ለያዙ ታካሚዎች ብቻ መስጠት መድሀኒት የተላመዱ ተህዋስያን እንዳይበረክቱ ያግዛል፡፡
- በባለሙያዎች መሀል ያለ የግንዛቤ እጥረት
የፀረ ተህዋስያን ህክምና በህክምና ስልጠና ላይ በመጀመርያዎቹ አመታት ላይ የሚሰጥ ትምህርት ነው፡፡ ሀኪሞች በልምድም በእድሜም እየጨመሩ ሲሄዱ የሚያውቁት የሚመስላቸው ነገር ግን የሚረሱት ህክምና ነው፡፡ የተላላፊ በሽታዎች እና የፀረ ተህዋስያን መድሀኒቶች ህክምና ስልጠናም በህክምና ት/ቤቶች በሁለት እግሩ ያልቆመ እና ትኩረት የተነፈገው ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ 33 የህክምና ት/ቤቶች የተላላፊ በሽታዎች እና የፀረ ተህዋስያን መድሀኒቶች የድህረ-ምረቃ ስልጠናን ለሀኪሞች የሚሰጠው የጥቁር አንበሳ የህክምና ት/ቤት ብቻ ነው፡፡
- የመድሀኒት ዝውውር ቁጥጥር መላላት
የሀገራችን የመድሀኒት ዝውውር ቁጥጥር በቂ አይደለም፡፡ በህገወጥ መንገድ የሚዘዋወሩ የፀረ ተህዋስያን መድሀኒቶች ባብዛኛው በሚመከረው መንገድ (ሙቀታቸው ተጠብቆ፣ የአገልግሎት ዘመናቸው ሳያልፍ ወ.ዘ.ተ.) ከአምራቹ ወደ ተጠቃሚው አይደርሱም፡፡ ስለዚህም ውጤታማ አይሆኑም፡፡
- የሚድያው ለፀረ ተህዋስያን መድሀኒቶች መላመድ እና ውጤታማነት መቀነስ (antimicrobial resistance) ትኩረት አለመስጠት
የፀረ ተህዋስያን መድሀኒቶች መላመድ በአመት ውስጥ ከማንኛውም ህመም የበለጠ ታካሚዎች ይገድላሉ ፡፡ የሀገራችን ሚድያዎች ግን ትኩረት ነፍገውታል፡፡
ይህንን የሚመሰክር ጥናት ለማንበብ ይሄን ሊንክ ይጫኑ ፡፡
- ከፀረ ተህዋስያን ህክምና በፊት መሟላት ያለባቸው ምርመራዎች (Microbiology diagnostics) ትኩረት ሰጥቶ እንዲሟሉ አለማድረግ
እንደማንኛውም ህክምና የተላላፊ በሽታዎች ህክምና ከመሰጠቱ በፊት ህመሙን ስላስከተለው ተህዋስ ተገቢው መረጃ በምርመራ መደረግ አለበት፡፡ በኢትዮጵያ ያሉ ሆስፒታሎች ከአመታዊ ወጪያቸው ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው የፀረ ተህዋስያን መድሀኒቶች ግዢ ነው፡፡ በተቃራኒው ለምርመራ (laboratory) ከሚይዙት በጀት ዝቅተኛውን ድርሻ የሚይዘው ከፀረ ተህዋስያን ህክምና በፊት መሟላት ያለባቸው ምርመራዎች (Microbiology diagnostics) ግዢ ነው፡፡ ይህ ተቃርኖ ካልተፈታ የተላላፊ በሽታዎች ህክምናን መቆጣጠር ይከብደናል፡፡
- የውሀ አቅርቦት አለመኖር ወይም መቆራረጥ
የተላላፊ በሽታዎች ህክምና እና መከላከልን ዘወትር ከሚፈታተኑ ምክንቶች ዋነኛው የውሀ አቅርቦት አለመኖር ወይም መቆራረጥ ነው፡፡ “በሽታ ለመከላከል እጃችሁን በሳሙና እና በውሀ ታጠቡ” የዘወትር የህክምና ባለሙያዎች ምክር ቢሆንም ያን ለማሟላት በተለይ በተለይ በህክምና መስጫ ተቋማት መቼም የማይቆራረጥ ዉሀ መሟላት ግደታ ነው፡፡
- የጤና መድህን አገልግሎት አለመስፋፋት
በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደረው ህብረተሰባችን በሚታመምበት ሰአት ሁለት አማራጮችን ይጋፈጣል፡፡ የመጀመርያው ሆስፒታል በመሄድ ምርመራ አድርጎ መድሀኒት ገዝቶ መታከም ሲሆን ሁለተኛው ቀጥታ ፋርማሲዎችን በመጎብኘት ያለ ሀኪም ትእዛዝ መድሀኒት ገዝቶ መጠቀም ነው (ቢያድንም ባያድንም)፡፡ ከገቢ ውስንነት የተነሳ ድሀው ህዝባችን ተራ ቁጥር 3 ላይ የተጠቀሰውን ይፈጽማል፡፡ ምናልባት ለዚህ መፍትሄ የሚሆነው በህመም ሰአት ተገቢውን ቅድመ-ህክምና ምርመራ ለማድረግ መንግስት የጀመረውን የጤና መድህን አገልግሎት በስፋት ማዳረስ ነው፡፡ ከዛም ህመም በሚያጋጥምበት ሰአት ህክምናው የሚያዘውን ቅድመ-ምርመራ በማድረግ፣ ተህዋሱ ታውቆ የሚገባውን መድሀኒት መውሰድ ይችላል፡፡ በገቢ ማነስ ምክንያት መምረጥ ወዳልተገባ አማራጭ መግባት የለብንም፡፡
- የህክምና ባለሞያዎች እና የሚድያ መራራቅ
በብዙ ሙያ የተሰማሩ ሰዎች በተለያዩ የሚድያ መድረክ እየቀረቡ (በራሳቸው ተነሳሽነት) ህብረተሰቡን ያስተምራሉ፡፡ ይህ ግን በህክምና ባለሞያዎች አይታይም፡፡ የህክምና ባለሞያዎች ሀላፊነት ተሰምቷቸው እና ተነሳሽነትን ወስደው ትክክለኛ የህክምና መረጃን ለህብረተሰቡ ማድረስ አለባቸው፡፡ የተላላፊ በሽታዎች ህክምና በሀሰተኛ መረጃዎች ስህተተኛ ግንዛቤ ከሚወሰድባቸው ህክምናዎች ግንባር ቀደም ነው፡፡
- የህክምና መስጫ ተቋማት ቁጥራቸው በበዛ ታካሚዎች እና አስታማሚዎች መጣበብ
ባብዛኛው ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት እንደሚታየው በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ የህክምና መስጫ ተቋማት ብዙ ታካሚዎች ያስተናግዳሉ፡፡ በተጨማሪም ቁጥራቸው በበዛ አስታማሚዎች ይጣበባሉ፡፡ ለምሳሌ አንድ 6 ታካሚዎች የሚያስተናግድ የመንግስት ሆስፒታል ክፍል ለያንዳንዱ ታማሚ 2 አስታማሚ ቢይዝ እና እያንዳንዱ ታማሚ በትንሹ 2 ጠያቂ በቀን ቢያስተናግድ 1 ታማሚ በቀን (የሆስፒታሉን ሰራተኞች ሳይጨምር) ከ29 ሰዎች ጋር ግንኙነት ይኖረዋል፡፡ ይህ ከታማሚው የተላላፊ በሽታዎች እና ተህዋስያን ወዳልታመሙ ሰዎች እንዲሄድ እና ታማሚውም ለሌሎች ህመሞች እንዲጋለጥ ያደርጋል፡፡ ሆኖም በህክምና መስጫ ተቋማት የጎብኚዎችን እና አስታማሚዎችን ቁጥር የመመጠን ፖሊሲ ሊኖረን ያስፈልጋል፡፡
- ከሀገሪቱ ነባራዊ የፀረ ተህዋስያን ህክምና ጋር ተዛማጅ የሆኑ ምርምሮች እጥረት
ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ተዛማጅ የሆኑ የፀረ ተህዋስያን ህክምና ምርምሮች እጥረት አለ፡፡ ያሉትም ጥቂት ተመራማሪዎች በቂ ድጋፍ እና ማበረታቻ ያንሳቸዋል፡፡ የሀገሪቱ የተላላፊ በሽታዎች ህክምና ፖሊሲ መሰረት የሚሆኑትን ሀገር በቀል መረጃዎች ለማግኘት ተመረማሪዎችን ማሳሳት ያስፈልጋል፡፡