በ ቅርብ ግዜ የወጡ መረጃዎች ከዚህ ቀደም በኮቪድ 19 ታመው ያገገሙ ሰዎች በድጋሚ እንደ አዲስ  በበሽታው ሊያዙ እንደሚችሉ  አልፎም ለሞት ሊዳረጉ እንደሚችሉ ያሳያሉ ። በዚህ ዙሪያ የተሰሩ ጥናቶች ምን ያሳያሉ? 

ዶ/ር ትንሳኤ አለማየሁ

የመጀመርያ የኮቪድ19 ህመም ከተከሰተ በኋላ ድጋሚ ልንያዝ እንደምንችል በቂ ማስረጃዎችን እያገኘን ነው፡፡ የመጀመርያውን ህመም ያገገሙ ሰዎች ለምን ያህል ጊዜ የበሽታ መከላከያቸው (Immunity) ይጠብቃቸዋል የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ከ7 ያላነሱ ጥናቶች ተደርገዋል፡፡ እነዚህም ጥናቶች የመጀመርያውን ህመም ከዳንን በኋላ ከ 52 እስከ 120 ቀናት ለሚሆን ጊዜ ሰውነታችን ከኮቪድ ሊጠበቅ እንደሚችል መረጃ ያቀርባሉ ፡፡ ያ ማለት የተጠቀሰው ጊዜ ካለፈ እንደ አዲስ ተጋላጭነት ይኖረናል ማለት ነው፡፡ አጭር የ Immunity ጊዜ ያላቸው በመጀመርያ ህመማቸው ጊዜ ምንም ምልክት ወይም አነስተኛ የህመም ምልክት የነበራቸው ሲሆኑ እና በተነፃፃሪ ረዘም ያለ የመከላከያ ጊዜ ያላቸው ደግሞ በፀና ታመው የዳኑት እንደሆኑ እነዚህ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ በታማሚዎች ወጣት መሆን ወይም አዛውንት መሆን ምክንያት የተለያየ የበሽታ የመከላከያ ጊዜ አልተመዘበም፡፡ አጫሾች ከማያጨሱ ሰዎች ጋር ሲነፃፀር ያጠረ የበሽታ የመከላከያ ጊዜ እንዳላቸው በጥናት ተረጋግጧል ፡፡      

በላብራቶሪ ምርመራ የተረጋገጠ ድጋሚ ወይም ሁለተኛ የኮቪድ-19 ኢንፌክሽን እስካሁን በስምንት ሀገራት ተመዝግቧል፡፡ በድጋሚ የታመሙ ሰዎች በሁለቱም ጾታዎች እና በተለያ እድሜ ክልሎች (ከ20 እስከ 89 አመት ድረስ) ይገኛሉ :: በሆላንድ፣ በኢኳዶር፣ በአሜሪካ እና በስፔን በድጋሚ የታመሙ ሰዎች ከበፊቱ የከፋ ህመም ሲኖራቸው ታይቷል፡፡ ከበፊቱ ቀለል የለ የኮቪድ ህመም በሁለተኛው ጊዜ ያጋጠማቸው ታማሚዎች ደግሞ ከሆንግ ኮንግ፣ አሜሪካ እና ቤልጅየም ሪፖርት ተደርገዋል፡፡ ስለዚህ የኮቪድ19 ህመም ድጋሚ ቢከሰት ይበረታል ወይም ይቀላል ብሎ በአሁኑ ሰአት መናገር አይቻልም፡፡ እስካሁን የታዩት ለሁለተኛ ጊዜ የተከሰቱት ኢንፌክሽኖች የመጀመርያዎቹ ከዳኑ በአማካይ ከ72 ቀናት በኋላ የተረጋገጡ ናቸው፡፡ በተጨማሪም በዚህ ሳምንት የመጀመርያው በድጋሚ የኮቪድ ህመም ምክንያት የሞቱ ታማሚ በሆላንድ ተመዝግበዋል፡፡

አብዛኛው ቀላል እና መሀከለኛ የኮቪድ-19 ህመም ስሜቶች ኖሯቸው የሚድኑ ሰዎች የህመም ምልክቶቻቸው ከ 7 – 10 ቀናት የሚቆዩ ሲሆን ለሁለተኛ ጊዜ የተያዙ ሰዎች ላይ ይህ የህመም ጊዜ ከላይ ከተጠቀሰው ሲያጥር አይታይም፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ህመም ምክንያት ሊሆኑ ከሚችሉ ነገሮች ውስጥ መጀመርያ ህመም ካስከሰተው የ SARS CoV-2 ቫይረስ ዝርያ የተለየ አይነት ቫይረስ (strain)፣ ከሌሎች ኢንፌክሽኖች አንፃር የኮቪድ በሽታ የመከላከያ (Immunity) ጊዜው ማነስ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ሁኔታውን ለመረዳት ብዙ ጥናቶች ያስፈልጋሉ፡፡

ስለዚሀ ከኮቪድ መዳን ለረዥም ጊዜ መከላከያን አይሰጥም፡፡ በብዙ ሀገራት እየታየ እንዳለው ድጋሚ የኮቪድ 19 ህመሞች ይከሰታሉ፡፡ ሲከሰቱም የመጀመርያውን ካገገሙ በኋላ ፈጥኖ (3 ወር ባልሞላ ጊዜ) ሊሆን ይችላል፡፡ ድጋሚ የሚከሰቱ ህመሞች እድሜ እና ጾታ አይመርጡም፡፡ እንደመጀመርያው ጊዜ (episode) እስከ ሞት ድረስ የማድረስ እድል አላቸው፡፡ እስካሁን ስናደርግ የነበርነው የመከላከያ መንገዶች (ማስክ፣ የእጅ ንጽህና እና ማህበረሰባዊ መራራቅ) አጠናክረን መቀጠል አለብን፡፡  

የጤና ወግ

በመረጃ የተመሰረተ ሕክምና ብቻ ።  

………………………………………………………………………………………………………………………..

ይህ የጤና ወግ ድረ ገፅ ነው።
ስለ ጤንነታችሁ ማወቅ የምትፈልጉትን መረጃ የምታገኙበት ፣ በህክምና ባለሙያዎች የሚዘጋጅ የመረጃ ምንጭ ነው።
ሁልግዜም ከሀኪማችሁ ተማከሩ፣ ተጨማሪ መረጃ ከፈለጋችሁ የኛን ድረ ገፅ ጎብኙ።

በጥናት የተደገፈ መረጃ ብቻ እናቀርባለን።

የህክምና ባለሙያዎች ለህሙማኖቻችሁ የሚሆን የሚነበብ መረጃ ከፈለጋችሁ ይህን ግፅ ጠቁሟቸው። ህሙማኖቻችሁ እንዲያውቁት የምትፈልጉትን ነገር መረጃ ጠቅሳችሁ ፃፉልን፣ ስምችሁን ጠቅሰን እናወጣለን። የህክምና ተማሪዎች እንዲጽፉ እናበረታታለን።

በተጨማሪም በጤና ወግ ፖድካስት፣  በ ዩትዩብ ፣በ ትዊተር ፣ በ ፌስቡክ ፣ በቴሌግራም የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ገፆቻችን ታገኙናላችሁ