በ ዶ/ር  ትንሳኤ አለማየሁ 

የ ህፃናት አና ተላላፊ በሽታዎች ሕክምና ስፔሺያሊስት

የኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ አይቀርም፡፡ ስለዚህ አስቀድሞ ብዥታዎችን ማጥራት እና እውነታ ላይ የተመሰረተ እና የተቀናጀ መከላከያ መንገድ (በመደናበር እና ባሉባልታ ያልተመሰረተ) ያስፈልገናል፡፡ 

  1. የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ለበሽታው ምልክቶች መጠቆሚያ ያዘጋጀውን 8335 ቁጥር Save አርጉት (ግድየለም አርጉት)፡፡
  2. ካሁን በኋላ የህዝብ መጓጓዣዎች ላይ የመስኮት ክፈቱ አትክፈቱ ክርክር መኖር የለበትም፡፡ የህዝብ መጓጓዣዎች በበቂ ካልተናፈሱ የቫይረሱ ስርጭት ከፍተኛ ይሆናል፡፡
  3. ማስክን ከማጥለቅ እጅን ቶሎ ቶሎ በሳሙና እና በውሀ መታጠብ እንዲሁም በሚገኝበት ሰአት እጃችንን በአልኮሆል መጠራረግ በሽታውን ለመከላከል ውጤታማ ነው፡፡ ስለዚህም ቢያስፈልግም በማስክ እጥረት ሆድ አይባሰን፡፡ ዋናው መከላከያ መንገድ የእጅን ንጽህና መጠበቅ ስለሆነ፡፡ 
  4. የህክምና ባለሙያዎች፣ ስራቸው ከብዙ የሀገር ውስጥ እና የውጪ ዜጎች ጋር የሚያገናኛቸው ባለሙያዎች፣ የትራንስፖርት ዘርፍ ሰራተኞች ሞባይላቸውን፣ የመስሪያ ጠረጴዛቸውን እና የኮምፕዩተር ኪይቦርዳቸውን በአልኮሆል መጠራረግ አለባቸው፡፡
  5. በ COVID19 ከሚያዙ ህሙማን ከ 2 – 3% የሚሆኑት ብቻ ለሞት ይጋለጣሉ፡፡ በአንዳንድ ሚድያዎች ሪፖርት እንደሚደረገው የያዘውን ሁሉ የሚገል ህመም አይደለም፡፡ ህብረተሰቡ ይህንን ተገንዝቦ ወደ ህክምና ተቋማት በመምጣት ህክምና ማግኘት ብሎም ለበሽታው መከላከል አስተዋጽዎ ማድረግ አለበት፡፡ ያሉት ታማሚዎች ሁሉ በታወቁ ቁጥር በጊዜ ህመሙን መቆጣጠር ይቻላል፡፡ አትደበቁ፡፡
  6. ከኤርፖርት ተመርምረው እና ደህንነታቸው ተረጋግጦ ቢወጡም በሚመጡት ቀናት የህመም ስሜት ሊመጣ ይችላል፡፡ ለቫይረሱ ከተጋለጥን በሁላ እስከ 21 ቀን ቆይቶ ህመም ሊከተል ይችላል፡፡
  7. የኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ ከተረጋገጠ በኋላ ህዝባዊ ስብሰባዎች፣ የእግር ኳስ ጨዋታዎች፣ የሃይማኖት ፕሮግራሞች የመሳሰሉትን መሰረዝ ወይም ማስተላለፍ ያስፈልጋል፡፡ በሀገራችን ባለው የትራንስፖርት እጥረት የህዝብ መጓጓዣዎች ላይ እገዳ ማድረግ ቢከብድም አማራጭ ባለበት ሁኔታ ሁሉ የእግር እና የብስክሌትን ጉዞ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡
  8. እጃችን ከፊታችን ጋር ማነካካት የለብንም፡፡ በጣም ቀላል ግን ውጤታማ መከላከያ መንገድ ነው፡፡
  9. የመኖርያ እና የመስሪያ ቦታዎች መስኮት በመክፈት በቂ የአየር ዝውውር እንዲኖራቸው ያስፈልጋል፡፡
  10. የመድሀኒት አቅርቦት ኤጀንሲ ለአልኮሆል እና ለማስኮች አቅርቦት ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ያሰፈልገዋል፡፡ እንዲሁም በእርዳታ የምናገኘውን የመመርመርያ አቅርቦት እንዲጨምር ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከህዝባችን ብዛት አንፃር በቀን ብዙ ሰው መመርመር ሊያስፈልገው ይችላል፡፡