By Jochebed Kinfemichael Suga, 4th year medical student at Myungsung Medical College

ጆኬቤድ ክንፈሚካኤል ሱጋ (ሚዩንግሱንግ ህክምና ኮሌጅ የ፬ አመት ተማሪ)

Reviewed/Approved by: Dr.Lemma Zewde (Editor at Yetena Weg/ Internist)

 

ቅዝቃዜ ወቅቶች ላይ ወደውጪ መውጣትን ስናስብ ብርድ እንዳይመታህ/ሽ ልብስ ደርብ/ቢ ፣ ታክሲ ውስጥ የሚያስል ሰው ሲኖር ብርዱ ነው መስኮቱን ዝጉት ወይንም ደግሞ ብርድ መታኝ መሰለኝ ሰውነቴን ይቆረጣጥመኛል የሚሉ ነገሮችን ተብለን ወይም ብለን እናውቃለን፡፡

ለመሆኑ ብርድ የሚባል በሽታ በሀኪሞች ዘንድ ይታወቃል?

ብርድ እና ጉንፋን

በተለይ በዚህ ዘመን ራሱን በሳል በሚገልጠው የኮሮና በሽታ ከመታየቱ በፊት አብዛኛውን ጊዜ የሚያስል ሰው የሚያቀርበው ምክንያት ትላንት ብርድ መታኝ መሰለኝ የሚል ነው፡፡ በብዛትም የሳል ምልክት የሚስተዋለው የብርድ እና ቅዝቃዜ ወቅት እንደመሆኑ መጠን ብርድ እና ጉንፋንን አቆራኝቶ ማውራቱ ብዙም አይገርምም፡፡ ብርድ እና ጉንፋን በብዛት ተቆራኝተው ቢገኙም የአየር ሁኔታ ግን ሰዎችን ከማሳመም ጋር ቀጥተኛ የሆነ ዝምድና የለውም፡፡ ሆኖም ግን ጨርሶም ግንኙነት የላቸውም ማለት አይደለም፡፡

አየርን ወደ ሳንባችን በአፋችን እና በአፍንጫችን እንቀበላለን፡፡ ይህ የተቀበልነው አየር ወደ ሳንባ ከመድረሱ በፊት ግን ከአየር መቀበያ እስከ ሳንባ ድረስ ያለው መተላለፊያ መንገድ የተቀበለውን አየር የማሞቅ እና የተሻለ እርጥበት እንዲይዝ ይሰራል፡፡ በዚህም ሰውነታችን የተሻለ የመተንፈስ ስነስርአት እንዲኖረን ይረዳል፡፡

ቀዝቃዛ አየር በተለምዶ ደረቅ እና አነስተኛ እርጥበት አዘል በመሆኑ ይህንን አየር በምንተነፍስበት ጊዜ አየር ወደ ሳንባ የሚተላለፍበት መንገድ ላይ ድርቀትን ያስከትላል፡፡ ይህም የአየር መተላለፊያ መንገድ የተለምዶ አየር የማሞቅ እና እርጥበት አዘል የማድረግ ስራዉ ላይ ተግዳሮት ይፈጥርበታል፡፡ ይህም በአየር መንገዶች ላይ መጥበብ ያመጣል፡፡ ይሄ ደግሞ አየር በማስወጣት ሂደት ወቅት የሚሰማ ድምፅ (wheezing) እንዲኖር ያደርገዋል፡፡

ይህ የአየር እርጥበት ማነስ እና መድረቅ የአየር መተላለፍያ መንገድ ብቻ ሳይሆን የሳንባ መቆጣትንም ስለሚያስከትል በጉንፋን ጊዜ የምናስተውላቸውን ምልክቶች (እንደ ሳል፣ ከመተንፈስ ጋር የሚወጣ ድምፅ (wheezing) እና የትንፋሽ ማጠርን) እናስተውላለን፡፡ በተጨማሪም በሰውነታችን ድርቀት (dehydration) ስለሚያስከትል ሰውነታችን በተለይም በአየር መተላለፊያ ውስጥ በተለምዶ የሚኖር ወፍራም ዝልግልግማ ፈሳሽ መመረት (mucous production) ይቀንሳል፡፡ ይህ የዝልግልግማ ፈሳሽ(mucous) በአየር መተላለፊያ መንገዶች ውስጥ መኖር ወደሳንባችን በቀላሉ ሊገቡ ከሚችሉ ጀርሞች እና ረቂቅ ተዋስያንን በማጥመድ የጥበቃ አገልግሎትን ይሰጣል፡፡ የዝልግልግማ ፈሳሽ መመረት መቀነስ ይህን የጥበቃ አገልግሎት ስለሚያጠፋ ጀርሞች እና ረቂቅ ተዋሲያን በቀላሉ በሳንባችን ውስጥ እንዲሰራጩ ያደርጋል፡፡ ይህም ለጉንፋን፣ የሳንባ ምች እና ከነዚህ ለባሱ ውስብስብ የሳንባ በሽታዎች ያጋልጣሉ፡፡

ብርድ እና የሰውነት ቁርጥማት 

ብርድ እና የሰውነት ቁርጥማት አብዛኛውን ጊዜ ተቆራኝተው ሲነገሩ እንሰማለን፡፡ የሀገራችን ሰዎች ሀኪም ቤት መሄድ ሳይጠበቅባቸው እራሳቸውን በማሞቅ እና ትኩስ ነገሮችን በመውሰድ ሲያክሙ ይስተዋላል፡፡ የሆነው ሆኖ ብርድ እና የሰውነት ቁርጥማት በሳይንስ የተደገፈ ግንኙነት ይኖራቸው ይሆን ብለው ጠይቀዋል?

በርግጥ ይህን ግንኙነት ለማስረዳት ሙሉ በሙሉ በሣይንስ የተደገፈ መልስ ባይኖርም ሳይንቲስቶች የተለያዩ ፅንሰ ሀሳቦችን በማንሳት ተወያይተውበታል፡፡ በብዙ ሳይንቲስቶች ተቀባይነትን ያገኘው ፅንሰ ሀሳብ (theory) እንደሚያስረዳው በሰውነታችን ውስጥ የሚገኙ ጅማቶች፣ ጡንቻዎች እና ህዋሳት (tissues) በቀዝቃዛ አየር ዉስጥ የመለጠጥ እና የመኮማተር ባህሪን ያሳያሉ፡፡ ይህ የመለጠጥ እና የመኮማተር ሂደት የህመም ስሜትን ይፈጥራል፡፡ የመለጠጡም ሂደት በሰውነታቸን ውስጥ ያለውን ውስን ቦታ ስለሚያጨናንቅ የሰውነት ህመም ስሜት ይፈጥራል፡፡

 

በተደጋጋሚ የሚጠየቁ ጥያቄዎች 

ለብርድ ማድረግ ያለብን ጥንቃቄዎች ምንድናቸው?

ዋናው ለራሳችን ማድረግ ያለብን እንክብካቤ ለሰውነታችን በቂ ፈሳሽን መስጠት ነው፡፡ ይህንን በማድረግም በኢንፌክሽን የመያዝ እድልን መቀነስ ይቻላል፡፡ በተጨማሪም ለሰውነታችን ሙቀት የሚሰጡ ልብሶችን መደራረብ፣ ትኩስ ቀለል ያሉ ምግቦችን መውሰድ፣ በሰውነታችን ፈሳሽን ሊቀንሱ የሚችሉ የአነቃቂ(ካፊን) መጠጦችን ከመውሰድ መቆጠብ እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ የበረታ ሳል ወይም ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ የሰውነት ላብ መጨመር እና ክብደት መቀነስን ሲያስተውሉ ግን የኢንፌክሽን ምልክቶች እንደመሆናቸው መጠን የጤና ተቋማት በመሄድ አስፈላጊውን ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

የሰዎች ፍሰት በሚበዛበት ስፍራ ላይ መስኮቶች መከፈት አለባቸው?

ብዙውን ጊዜ በታክሲዎች እና ዝግ ቦታዎች ላይ የሚያስሉ ሰዎች ሲኖሩ መስኮት ይዘጋ እና አይዘጋ የሚሉ ዉዝግቦች ይነሳሉ፡፡ በቅዝቃዜ እና በኢንፌክሽን ምክንያት የሚታዩ ሳል መለየት አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለሆነም ጥሩ የአየር ዝውውር እንዲኖር መስኮቶች ቢከፈቱ ለታማሚው ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ያሉ ሰዎችም በኢንፌክሽን እንዳይያዙ ይከላከላል፡፡ ስለዚህም የሰዎች ፍሰት በሚበዛባቸው ቦታዎች የአየር ዝውውርን የሚያጠናክሩ እርምጃዎች (ሰፋ ያሉ ክፍሎች መጠቀም፣ መስኮቶችን መክፈት እና ሌሎችም) መወሰድ አለባቸው፡፡

ማጣቀሻዎች

-Centers for disease control and prevention (CDC)

-Web MD

-Mayo clinic

-John’s Hopkins medicine

 

የጤና ወግ 

ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።

የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።

https://linktr.ee/Yetena_Weg