By Jochebed Kinfemichael Suga, 4th year medical student at Myungsung Medical College
ጆኬቤድ ክንፈሚካኤል ሱጋ (ሚዩንግሱንግ ህክምና ኮሌጅ የ፬ አመት ተማሪ)
Reviewed/Approved by: Alemayehu Woldeyes,MD,MSc(Consultant ophthalmologist)
ትራኮማ በባክቴሪያ የሚመጣ ተላላፊ የሆነ የአይን በሽታ ነዉ፡፡ ይህ በሽታ በጊዜ ሂደት ወደ የአይን ግርዶሽ የሚያመራ ሲሆን በሀገራችን በስፋት ተሰራጭቶ ለአይን ግርዶሽ ከሚያጋልጡ በሽታዎች ዉስጥ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ በዚህ በሽታ ከተጠቁ ሰዎች ዉስጥ አብዛኞቹ ከ3-6 አመት ያሉ ህፃናት ናቸዉ፡፡
ትራኮማ እንዴት ይከሰታል?
ትራኮማ የሚከሰተዉ ክላሚዲያ ትራኮማተስ (chlamydia trachomatis) በሚባል ባክቴሪያ ነዉ፡፡ ይህም ባክቴሪያ ትራኮማ በተያዘ ሰዉ አይን እና አፍንጫ ዉስጥ ስለሚኖር ከነዚህ ክፍሎች በሚወጣ ፈሳሽ ምክንያት ከአንድ ሰዉ ወደ ሌላ ሰዉ ይተላለፋል፡፡ ንፁህ ያልሆኑ እጆች፣ ልብሶች፣ የፊት ማድረቂያ ፎጣዎች እና ትንኞች ለበሽታዉ መዛመት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ፡፡
የትራኮማ በሽታ ምልክቶች ምንድን ናቸዉ?
ከትራኮማ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ህመም እና ምልክቶች ከታችኛዉ የአይን ሽፋን በበለጠ በላይኛዉን የአይን ሽፋን ላይ ይታያሉ፡፡ አብዛኛዉ ጊዜ ትራኮማ ሁለቱንም አይኖች የሚያጠቃ ሲሆን ከታች የተዘረዘሩት ዋነኛ ምልክቶቹ ናቸዉ፡፡
የአይን መብላት እና መቆጣት
ከአይን የሚወጣ ፈሳሽ (ዉሀማ ወይም ነጭ መግል መሰል ፈሳሽ)
የአይን ሽፋን እብጠት
ብርሃንን አለመፈለግ (photophobia)
የአይን ህመም
የአይን መቅላት
እይታ መቀነስ ብሎም መጥፋት
ለትራኮማ በሽታ አስተዋፅኦ የሚያደርጉ ነገሮች ምንድን ናቸዉ?
ለትራኮማ በሽታ አስተዋፅኦ ከሚያደርጉ ምክንያቶች ዉስጥ ዋነኞቹ የሚከተሉት ናቸዉ፡፡
የተጨናነቀ/ የተጣበበ መኖሪያ ስፍራ
የንፅህና ጉድለት
የቤት ዉስጥ ትንኝ እና ዝንብ መብዛት
የትራኮማ በሽታ ደረጃዎች
የትራኮማ በሽታ በጊዜ ሂደት እየባሰ የሚሄድ እንጂ በአንድ ጊዜ የአይን ግርዶሽ/አይነ-ስዉርነትን አያስከትልም፡፡ የአለም የጤና ድርጅት ይህን በሽታ በተለያየ ደረጃ ያስቀመጠ ሲሆን ደረጃዉ እየጨመረ በመጣ ቁጥር የበሽታዉን ክብደት ያሳየናል፡፡
1. መቆጣት እና እባጭ/inflammation-follicle/፡ ይህ በሽታዉ እንደጀመረ ያለዉ የመጀመሪያዉ ደረጃ ሲሆን በላይኛዉ የአይን ሽፋን የዉስጠኛዉን ክፍል ላይ ትንንሽ እባጮችን በማጉያ መሳሪያ መመልከት ይቻላል፡፡
2. ከፍተኛ የአይን መቆጣት/inflammation-intense/፡ አይናችን በከፍተኛ ደረጃ በሽታን የማስተላለፍ አቅሙ የሚጨምርበት ደረጃ ነዉ፡፡ ከባድ የአይን መቆጣት እና የላይኛዉ የአይን ሽፋን ማበጥ ይታያል፡፡
3. የአይን ሽፋን ጠባሳ/eyelid scarring /፡ በተደጋጋሚ በትራኮማ በሽታ መያዝ የዉስጠኛዉ የአይን ሽፋን ላይ ጠባሳ እንዲኖር ያደርጋል፡፡ በማጉያ መሳሪያ በሚታይበት ጊዜ ይህ የጠባሳ ቦታ እንደነጭ መስመር ሆኖ ይታያል፡፡ በጊዜ ሂደት ጠባሳን የያዘዉ የአይን ሽፋን ቅርፅ መለዋወጥ እንዲሁም ወደዉስጥ መገልበጥ ሊያሳይ ይችላል፡፡
4. የአይን ሽፋሽፍት ወደዉስጥ መቀበር/trichiasis/፡ የአይን ሽፋን የዉስጥ ክፍል ጠባሳ መፈጠር የአይን ሽፋን የተለያየ ቅርፅ ለዉጥ እንዲኖረዉ ያደርጋል፡፡ ይህም የአይን ሽፋሽፍት ወደ ዉስጥ እንዲቀበር አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡ ይህም የአይን ብሌን ላይ ማሳከክ እና ቁስለትን ይፈጥራል፡፡
5. የአይን ብሌን ሽፋን /corneal clouding/፡ የአይን ብሌን ዋናዉ ጉዳት በላይኛዉ የአይን ሽፋን ምክንያት የሚፈጠር ሲሆን የአይን ሽፋሽፍት ወደ ዉስጥ መታጠፍ በተደጋጋሚ ለሚከሰት የአይን መቆጣት፣ መቁሰል፣ ዉሎ አድሮ የአይን ብሌን ላይ ጠባሳ ወይም ጭጋጋማ ሽፋን መፈጠር አስተዋፅኦ ያደርጋሉ፡፡
የትራኮማ በሽታ እንዴት ይመረመራል?
የትራኮማ በሽታ አብዛኛዉን ጊዜ የበሽታዉን ምልክቶች በማየት ብቻ የሚታወቅ ሲሆን የአይን ጤና ባለሙያዎች በሚያጎላ መሳሪያዎች የአይን ሽፋንን እና የአይን ብሌንን በመመልከት የበሽታዉን ደረጃ እና የአይንን ሁኔታ ይመረምራሉ፡፡ ከአይን ሽፋን ላይም ናሙና በመዉሰድ ለላብራቶሪ ምርመራ በመላክ የዚህ በሽታ አምጪ ባክቴሪያ መኖር እና አለመኖር ማረጋገጥ ይቻላል፡፡
የትራኮማ በሽታ ጋር ተያይዘዉ የሚመጡ የበሽታው መወሳሰቦች ምንድን ናቸዉ?
ትራኮማ ቀደም ብሎ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ሳይደርስ (ሳይወሳሰብ) የህክምና እርዳታ ከተደረገ በቀላሉ ይታከማል፡፡ በተደጋጋሚ በዚህ በሽታ መያዝ ግን ደረጃዉ ከፍ ላለ የትራኮማ በሽታ እና የህክምና መወሳሰብ ያጋልጣል፡፤ ከትራኮማ በሽታ ጋር ተያይዘዉ ከሚመጡ የበሽታው መወሳሰቦች መሀከል ዋነኞቹ የሚከተሉት ናቸዉ፡፡
የዉስጠኛዉ የአይን ሽፋን ላይ ጠባሳ
የአይን ሽፋን ጉዳቶች (eyelid deformities)
የአይን ብሌን ጠባሳ (ጭጋጋማ ሽፋን)
ከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ የአይን እይታ ማጣት
የትራኮማ በሽታ እንዴት ይታከማል?
የትራኮማ በሽታ ህክምና በበሽታዉ ደረጃ ይወሰናል፡፡ በመጀመሪያዉ የበሽታ ደረጃ ላይ ትራኮማን መድሃኒት (antibiotic) ብቻ በመጠቀም ማከም ይቻላል፡፡ ወደ ከፍተኛው የበሽታ ደረጃ በሄድን ቁጥር ግን ከመድሃኒት በተጨማሪ የቀዶ ጥገና የሚያስፈልግ ይሆናል፡፡ ይህም በአይን ብሌን ላይ የሚፈጠረዉን ጠባሳ ለመግታት የሚደረግ ነዉ፡፡ የአይን እይታ መቀነስ ወይም መጥፋት ደረጃ የደረሰ የአይን ብሌን መጎዳት በአይን ብሌን ንቅለተከላ ህክምና ይታከማል።
የአይን ብሌን ንቅለተከላ ህክምና በሀገራችን ውስጥ ይሰጣል!
የትራኮማ በሽታ እንዴት መከላከል ይቻላል?
በተደጋጋሚ በትራኮማ በሽታ ከመያዝ ጋር ተያይዘው የሚመጡ የበሽታ መወሳሰቦች ብሎም የአይን እይታን ሙሉ በሙሉ ማጣት መከላከል በጣም አስፈላጊ ነዉ፡፡ የትራኮማ በሽታን ለመከላከል ከምናደርጋቸዉ ነገሮች ዉስጥ ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸዉ፡፡
ፊትን እና እጅን መታጠብ
ዝንብ እና ትንኞችን መከላከል
ቆሻሻን በአግባቡ ማስወገድ
የአካባቢን ንፅህና መጠበቅ ናቸው።
የጤና ወግ
ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።
የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።
https://linktr.ee/Yetena_Weg