Written by: Dr. Hana Wondale (University of Gondar, medical Intern)
Reviewed by: Dr. Lydia Million (pediatrician)
አለምአቀፍ የመንተባተብ ግንዛቤ ቀን በ1998 እ.ኤ.አ በስዊድን የተጀመረ ሲሆን ፤ በየአመቱም የተለያዩ መሪ ቃላት በመያዝ ሲከበር ቆይቷል። የዚህም አመት መሪ ቃል “የማዳመጥ ሀይል” ነዉ። ይህ ሀሳብ በዚህ አመት አዘጋጆች ሲብራራ ፤ የሚንተባተቡ ሰዎች ሌሎች በትግስት ማድመጥን እንዲማሩ ለማድረግ እድሉ እንዳላቸው እና መደማመጥ ደግሞ ለመተማመንና የተሻለ መግባባትን ለመፍጠር መሰረት መሆኑን ይገልፃሉ።
ሁላችን በተለያየ ወቅት ላይ በንግግራችን መካከል መንተባተብ ያጋጥመናል ታዲያ እንደችግር የሚቆጠረው መቼ ነው?
መንተባተብ የንግግር ቅልጥፍናን የሚያዛባ እክል ሲሆን ፤ ምልክቶቹ ለተናጋሪው እድሜ እና የቋንቋ ችሎታ ተገቢ ያልሆኑ እና በጊዜ የማይጠፋ ናቸው። መገለጫዎቹ/ምልክቶቹ ፦
- ቃላትን/አረፍተነገር ለመጀመር መቸገር
- ድምፅ/ቃላትን አርዝሞ መናገር (ምሳሌ ፡ እኔ ለማለት እእእእኔ)
- ድምፅ/ቃላትን መደጋገም
- ድምፅ/ቃላትን ከመናገር በፊት ወይም መሃከል ላይ ረዘም ላለ ጊዜ ዝም ማለት
- ከንግግር በተጨማሪ ሰውነት ላይ የሚታዩ ምልክቶች (አይን በፍጥነት መርገብገብ ፣ የከንፈር መንቀጥቀጥ እና ጭንቅላትን ላይናታች በተደጋጋሚ ማወዛወዝ) ይጠቀሱበታል።
ከቁጥጥር ዉጪ የሆነ ቃላትን/ድምፅን መደጋገም ፣ ቃላትን መቆራረጥ እና ጊዜያዊ የሆነ ድምፅ/ቃላትን ለማዉጣት መቸገርን ያካትታል።
ከአለም ህዝብ 1% የሚሆኑት ሲያወሩ ይንተባተባሉ ተብሎ ይገመታል። እድሜያቸዉ ከ3-4 ካሉ ህፃናት ዉስጥ 5% የሚሆኑት የሚንተባተብ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ወደ 80% የሚጠጉት በ8 አመታቸዉ ያቆማሉ። እስከ 7 እና ከዛ በላይ ያለዉ እድሜያቸው ላይ መንተባተብ የሚቀጥል ከሆነ ግን በዛዉ የመቀጠል እድሉ ከፍተኛ ነው። ልጆች ላይ መንተባተብ በእድሜያቸው ከሚጠበቀው የከፋ ከሆነ ፣ በዚያዉ የሚቀጥል ከሆነ ፣ ልጆችን ለጭንቀት የሚያጋልጥ ከሆነ እና ወላጆች ካሳሰባቸዉ ወደ ህክምና መሄድ ይገባቸዋል
ከፆታ አንፃር ሲታይ የወንድ ተንተባታቢዎች ቁጥር ከሴቶች 4 እጥፍ ይበልጣል።
መንስዔዎች
በልጅነት የሚከሰት መንተባተብ የንግግርን ፍጥነት የሚቆጣጠር የአዕምሯችን ክፍል እድገት ውስንነት እንደ ምክንያት ይጠቀሳል። ጥናቶች መንተባትብ በዘር የመተላለፍ እድልም እንዳለው የሚያሳዩ ሲሆን ፤ ከቅርብ የቤተሰብ አባል ውስጥ የሚንተባተብ ዘመድ ያለው አንድ ግለሰብ ከሌሎች በሶስት እጥፍ የበለጠ ለመንተባተብ ተጋላጭ የመሆን እድል አለው።
በአዋቂዎች ላይ የሚከሰት መንተባተብ ከእድገት ጋር ተያይዞ ከሚመጣ መንተባተብ የተለየ ምክንያት ሲኖረው ከነዚህም መካከል ፦
- የተለያዩ ህመሞች (እንደ ስትሮክ እና የጭንቅላት ላይ አደጋ) ማጋጠም
- የስሜት ውጥረት ወይም ጭንቀት (ይህ መንተባተብ ያለባቸው ላይ ችግሩን ሊያባብስ ይችላል)
- ስነልቦናዊ መንተባተብ (Psychological stuttering) – ስነልቦናዊ ጉዳት ያጋጠማቸው ግለሰቦች ከዛ በኋላ መንተባተብ ሲያጋጥማቸው እና በዛው ሲቀጥል
መንተባተብ ንግግር ላይ ከሚያመጣው እክል በተጨማሪ ተያይዘው የሚመጡ መዘዞች የዕለት-ተዕለት ህይወት ላይ ችግር ያመጣሉ። ከነዚህ መካከል ፦ ከሌሎች ጋር ለመግባባት መቸገር ፣ ንግግር ማድረግ የሚጠበቅባቸውን አጋጣሚዎች አለመጠቀም ፣ ትምህርት ወይም ስራ ላይ በጋራ የሚሰሩ እና ንግግር የሚያስፈልጋቸውን ስራዎች መራቅ/አለመሳተፍ ፣ ከሌሎች የሚደርስ ሹፈት እና በራስ መተማመን መቀነስ ይካተታሉ።
ቃላትን መደጋገምው
የመንተባተብ ህክምናው ሙሉበሙሉ ችግሩን የሚያጠፋ አይደለም ነገርግን የንግግር ቅልጥፍናና ከሌሎች ጋር መግባባትን ማሻሻል እንዲሁም በትምህርትና ስራ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ መጨመር ላይ ያተኮረ ነው።
የንግግር ህክምና ፡ ንግግርን ቀስ በማድረግ እና መንተባተብ ሲኖር በማስተዋል ቀስበቀስ የንግግር ፍጥነትን ለማሻሻል የሚያግዝ ህክምና ነው። በዚህ ህክምና ወቅት ባለሞያዎች ለቤተሰቦች የተለያዩ ዘዴዎችን በማሳየት መንተባተብ ያለባቸው ልጆችን በቤት ውስጥም ማገዝ እና የህክምና ሂደት ማገዝ ይቻላል።
የስነልቦና ህክምና ፡ መንተባተብን የሚያባብሱ ስሜቶችን (እንደ ጭንቀትና በራስ መተማመን መቀነስ) ለማስወገድ የሚረዳ ህክምና ነው።
ስለመንተባተብ የተሳሳቱ አመለካከቶች
በአብዛኛው ማህበረሰብ ውስጥ ስለ መንተባተብ የተሳሳቱ አመለካከቶች አሉ ፦
- ሰዎች የሚንተባተቡት ስለሚፈሩ ነው
- የሚንተባተቡ ሰዎች አይን አፋር ናቸው
- የሚንተባተቡ ሰዎች የማሰብ ችሎታቸው ዝቅተኛ ነው
እነዚህ የተሳሳቱ አመለካከቶች ለመንተባተብ ምክንያት ከመሆን ይልቅ የሚንተባተቡ ሰዎች ከሚደርስባቸው ማህበረሰባዊ ተፅዕኖ የሚከሰቱ ናቸው።