ከናሽናል ኪድኒ ፋውንዴሽን/ብሔራዊ የኩላሊት ፋውንዴሽን
አልኮል እና ኩላሊትዎ
የአልኮል መጠጥ መውሰድ ኩላሊትዎን ጨምሮ ብዙ የውስጥ የሰውነት ክፍልዎ ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል፡፡ አነስተኛ የአልኮል መጠጥ- በተወሰነ ጊዜ ልዩነት የሚወሰድ አንድ ወይም ሁለት የአልኮል መጠጥ ሰውነታችን ላይ የከፋ ጉዳት ላያደርስ ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ከመጠን ያለፈ የአልኮል መጠጥ ጤናችንን ሊጎዳ ይችላል፡፡ በተለይም ደግሞ ኩላሊታችን ላይ የከፋ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል፡፡
አልኮል ኩላሊታችን ላይ ጉዳት ሊያደርስ የሚችለው በምን አይነት መልኩ ነው?
ኩላሊታችን በደማችን ውስጥ ሊኖሩ የሚችሉ ጎጂ ንጥረ ነገሮችን ያጣራል፡፡ ከእነዚህም ንጥረ ነገሮች ውስጥ አልኮል አንዱ ነው፡፡ አልኮል ኩላሊታችን በደማችን ውስጥ የሚገኙ ጎጂ ንጥረ ነገሮችን የማጣራት ስራ ሊያደናቅፍ ይችላል፡፡ ኩላሊታችን በደማችን ውስጥ ሊኖር የሚችለውን ጎጂ ንጥረ ነገር ከማጣራት በተጨማሪም ሌሎች ብዙ ጠቃሚ ተግባራት ያከናውናል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንደኛው በሰውነታችን ውስጥ ትክክለኛ የውሃ መጠን መኖሩን መቆጣጠር ነው፡፡ በመሆኑም አልኮል ኩላሊታችንን እነዚህን ጉልህ እና ጠቃሚ ተግባራት እንዳያከናውን ተግዳሮት ይሆናል፡፡ ሰውነታችን አልኮልን ሲያስወግድ ኩላሊታችንን ጨምሮ የተለያዩ የውስጥ የሰውነት ክፍላችን ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል፡፡
ከመጠን ያለፈ አልኮል የደም ግፊታችን ላይ ተጽእኖ ሊያስከትል ይችላል፡፡ አብዝተው የአልኮል መጠጥ የሚወስዱ ሰዎች በከፍተኛ የደም ግፊት የመጠቃት እድላቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ በሌላም በኩል አልኮል የደም ግፊትን ለመቆጣጠር የምንወስደው መድሃኒት ወይም የህክምና ክትትል ላይ ተጽእኖ ሊፈጥር ይችላል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ከፍተኛ የደም ግፊት ለኩላሊት ህመም መንስኤ ነው፡፡ በቀን ከ2 በላይ የአልኮል መጠጥ መውሰድ በከፍተኛ የደም ግፊት የመያዝ እድላችንን በይበልጥ ይጨምራል፡፡
በተጨማሪም ስር የሰደደ የአልኮል ሱስ እና ለረጅም ጊዜ የሚወሰድ የአልኮል መጠጥ ጉበታችን ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ለኩላሊታችን ተጨማሪ ስራ የሚፈጥር ይሆናል፡፡ ሰውነታችን እንዲጣራ ወደ ኩላሊታችን የሚልከው ደም የተመጠነ ሲሆን ይህም ኩላሊታችን በአንድ ጊዜ የሚያጣራው የደም መጠን ውስን ስለሆነ ነው፡፡ የጉበት ጤና መታወክ ደግሞ በዚህ የኩላሊት አሰራር ሂደት ላይ እክል የሚፈጥር ነው፡፡
ጥናቶች እንደሚያሳዩት በቀን ለሴቶች ከአንድ መለኪያ በላይ ለወንዶች ደግሞ በቀን ከ ሁለት መለኪያ በላይ መጠጣት የለባቸውም።
አንድ መለኪያ ሲባል (አንድ የቢራ ጠርሙስ ፣ ወይም አንድ ብርጭቆ ወይን እንደ ማለት ነው።)
እንደ አለብዎት የህመም ሁኔታ ሀኪምዎ ለእርሶ የሚሆን ምክር ይሰጥዎታል። ሁልግዜም የብሀኪምዎን ምክር ያዳምጡ።
Source : The National Kidney Foundation.
ይህን የጤና መረጃ ከአሜሪካን የኩላሊት ህክምና ማህበር ድረ ገፅ ላይ ምንጭ አድርገን ስናቀርብ ፅሁፉን በመተርጎም የተባበርንን አቶ ናትናኤል ተክሉን ( Twitter: @natnaelteklu) ከልብ እናመሰግናለን ።
If you want to read the original article in English please click here