የጤና ወግ ማንኛውም ሰው የፊት ማስክ እንዲለብስ ቢደረግ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብላ ታምናለች፡፡
ሁሉም ሰዎች ከቤታቸው ሲወጡ (በተለይም አካላዊ ርቀትን መጠበቅ በማይችሉበት ቦታ ላይ) የፊት ማስክ እንዲጠቀሙ ትመክራለች፡፡
እንደ ምሳሌ የተለያዩ ሀገራት ያላቸው መመሪያዎች
  • ይህ በእንዲህ እያለ የኮቪድ19 ወረርሽኝ ከተነሳ በኋላ የማስክ ጠቃሚነት/አስፈላጊነት ላይ አትኩሮት ያደረጉ ጥናቶችም ብቅ ብቅ ሲሉ ቆይተዋል።
  • ይህንንም ተከትሎ የአሜሪካው CDC  በመጋቢት 26/2012 ባወጣው መመሪያ ሰዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ቢጠቀሙ የተሻለ እንደሆነ አዲስ ምክረ ሃሳብ ሰጥቷል፡፡ ይህም እየተገኙ ያሉ መረጃዎችን ተንተርሶ በተለይም ከበሽታው የመተላለፍ ባህሪያት ጋር ተያይዞ ያሉና ሌሎች አዳዲስ የምርምር ውጤቶችን ከተመለከቱ በኋላ የተደረሰ ውሳኔ እንደሆነ ተጠቅሷል:: በተለይም ደግሞ አካላዊ መራራቅን ለመተግበር በሚያስቸግርባቸው ቦታዎች ላይ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ መጠቀሙ አስፈላጊ እንደሆነ አስምሮበታል፡፡
  • ለዚህ ለውጥ ምክንያት የሆኑት መረጃዎች ምንድን ናቸው?
    1. በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ገና ምልክቶች ማሳየት ከመጀመራቸው በፊት (Pre-symptomatic) በሽታውን ሊያስተላልፉ እንደሚችሉ የተገኙ መረጃዎች [ለምሳሌ 123]
    2. በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ምንም ምልክት (Asymptomatic) ሳያሳዩ ሊኖሩና ነገር ግን በሽታውን ሊያስተላልፉ እንደሚችሉ የተገኙ መረጃዎች [ለምሳሌ 123]
    3. ቫይረሱ በተለመዱና ባልታሰቡ መንገዶች (ለምሳሌ፡ በመተንፈስ ብቻ፣ በመናገር) ሊተላለፍ እንደሚችል መረጃዎች ስለተገኙ
  • ሆኖም ግን የአሜሪካው CDC ካለው የሰርጂካል እና የ N95 ማስክ እጥረት አንፃር ማህበረሰቡ እንዲጠቀም ያሳሰበው ከጨርቅ የተሰሩ ማስኮችን (Cloth Masks) እንደሆነ መጠቀስ አለበት፡፡
  • CDC ይህን ይበል እንጂ እስካሁን WHO የቀደመውን አቋሙንና ምክረ-ሀሳቡን አልቀየረም::
  • ከላይ ከተጠቀሱት መረጃዎች በተጨማሪ ማስክ የመልበስ ባህል በዳበረባቸውና ባልዳበረባቸው ሀገራት መሀከል ወረርሽኙን ከመቆጣጠር አንፃር የታዩት ልዩነቶች  እና ቫይረሱን ለመከላከል የፊት ማስክ ያለውን ጠቀሜታ ያሳዩ ቀደምትአዲስ ሌሎች ሳይንሳዊ ምርምሮች ግንዛቤ ውስጥ መከተት አለባቸው።
  • እንዚህንና ሌሎች መረጃዎችን በመመልከት የጤና ወግ ማንኛውም ሰው የፊት ማስክ እንዲለብስ ቢደረግ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብላ ታምናለች፡፡ ሁሉም ሰዎች ከቤታቸው ሲወጡ (በተለይም አካላዊ ርቀትን መጠበቅ በማይችሉበት ቦታ ላይ) የፊት ማስክ እንዲጠቀሙ ትመክራለች፡፡
  • ሆኖም ግን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት ሁሉም ሰው ማስክ እንዲለብስ ማድረግ በጣም አስቸጋሪ መሆኑ ግልፅ ነው። ነገር ግን ከሚኖረው ጠቀሜታ አንፃር የጨርቅ ማስኮች በብዛት የሚመረቱበትና የሚሰራጩበትን መንገድ መፍጠር ያሻል፡፡
  • ከዚህ መለስ ሰዎች በቀላሉ በቤታቸው ማስኮችን መስራት ቢችሉ ጫናውን የሚቀንስ ሲሆን አማራጭ ሲታጣ ደግሞ በቀላሉ ቤት ውስጥ የሚገኙ ልብሶችን (ለምሳሌ፡ ስካርፍ፣ ነጠላ፣ ቲሸርት እና ሌሎችን) ቢጠቀሙ መልካም ነው እንላለን፡፡

እዚህ ላይ ማስታወስ የምንፈልገው ነገር ቢኖር የጤና ባለሙያዎች ካላቸው የተጋላጭነት ደረጃ አንፃር የጨርቅ ማስኮችን እንዲጠቀሙ ፈፅሞ አይመከርም፡፡ በተቻለ መጠን እንዳስፈላጊነቱ ሰርጂካል ማስክ ወይም N-95 ማስክ መጠቀሙ የተሻለ ነው፡፡

የጨርቅ ማስክ አዘገጃጀትና ለመስራት የሚመረጡ የጨርቅ አይነቶች

ይህንን በተመለከተ ጥቂት ጥናቶች ቢኖሩም አንዱ ካንዱ እንደሚሻል በእርግጠኝነት መናገር ያስቸግራል፡፡

የጨርቁ ውፍረት በጨመረ ቁጥር የተሻለ የመከላከል አቅም አለው ተብሎ ይታሰባል፡፡ ጨርቁን በመያዝ በደንብ የሚያበራን  የመብራት ብርሀን ምን ያህል እንደሚያስተላለፍ በመመልከት (light test) የጨርቁን ውፍረት መመዘን ይቻላል፡፡ በቀላሉ ብርሃን የማያስተላልፉ ጨርቆች የተሻለ ይመረጣሉ ማለት ነው፡፡

በአገራችን ሁኔታ ቀላሉና ለመተግበር የሚመቸው የጥጥ (cotton) ጨርቆችን መጠቀም ሲሆን በቂ ውፍረት እንዲኖረው ሁለት ተመሳሳይ ልኬት ያላቸውን ጨርቆች መደረብ የተሻለ ነው፡፡

የጨርቅ ማሰክ አስተጣጠብ

የጨርቅ ማስክ እንዴት መታጠብ አለበት ከሚለው አንፃር ጥናቶች ባይኖሩም እንደተለመደው በሳሙናና የሞቀ (ትኩስ) ውሃ ማጠብ ቫይረሱን እንደሚገድለው ይጠበቃል፡፡

መረሳት የሌለባቸው ጉዳዮች

ማስክ ማድረግ ብቻውን ከኮቪድ19ም ይከላከላል ብሎ ማሰብ ስህተት ነው፡፡ ማስክ መልበስ ከመሰረታዊ ጥንቃቄዎች ጋር ሲቀናጅ የተሻለ ውጤታማ ያደርጋል፡፡ እነዚህም

  • አካላዊ መራራቅን መተግበር
  • አካላዊ ንክኪዎች ማስቀረት
  • በተደጋጋሚና በአግባቡ እጅን መታጠብ/በአልኮል ማፅዳት
  • ሰዎች በሚበዙባቸው/በሚሰበሰቡባቸውን ቦታዎች አለመገኘት

በቀላሉ የፊት ማሰክ ቤት ውስጥ የሚሰራበትን መንገድ እንዲጠቁማችሁ ይህንን ምስል እና ቪዲዮ መመልከት ይችላሉ፡፡

የጤና ወግ

በመረጃ የተመሰረተ ሕክምና ብቻ ።  

………………………………………………………………………………………………………………………..

ይህ የጤና ወግ ድረ ገፅ ነው።
ስለ ጤንነታችሁ ማወቅ የምትፈልጉትን መረጃ የምታገኙበት ፣ በህክምና ባለሙያዎች የሚዘጋጅ የመረጃ ምንጭ ነው።
ሁልግዜም ከሀኪማችሁ ተማከሩ፣ ተጨማሪ መረጃ ከፈለጋችሁ የኛን ድረ ገፅ ጎብኙ።

በጥናት የተደገፈ መረጃ ብቻ እናቀርባለን።

የህክምና ባለሙያዎች ለህሙማኖቻችሁ የሚሆን የሚነበብ መረጃ ከፈለጋችሁ ይህን ግፅ ጠቁሟቸው። ህሙማኖቻችሁ እንዲያውቁት የምትፈልጉትን ነገር መረጃ ጠቅሳችሁ ፃፉልን፣ ስምችሁን ጠቅሰን እናወጣለን። የህክምና ተማሪዎች እንዲጽፉ እናበረታታለን።

በተጨማሪም በጤና ወግ ፖድካስት፣  በ ዩትዩብ ፣በ ትዊተር ፣ በ ፌስቡክ ፣ በቴሌግራም የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ገፆቻችን ታገኙናላችሁ