ዶ/ር ማህሌት አለማየሁ (MD)

በእርግዝናሽ ወቅት በሃገራችን ውስጥ ኮቪድ 19 መገኘቱ አሳስቦሽ ይሆናል። አዎን ያለንበት ወቅት ቀላል አይደለም ነገር ግን  እባክሽ ከተገቢው በላይ እራስሽን አታስጨንቂ ፥ ዋናው ነገር  ጥንቃቄዎችን ሁሉ ማድረግ ነው ። ብዙ ጥያቄዎችም ሊኖሩሽ ይችላሉ ። እኔ እርጉዝ ሰለሆንኩ ለኮቪድ  19 የበለጠ ተጋላጭ እሆን ወይ ?  ኮቪድ  19 ቢይዘኝ ወደ ጽንስ ይተላለፍ ይሆን ወይ ?   ወዘተ 

  1. እርጉዝ ስለሆንኩ ለኮቪድ  19 የበለጠ ተጋላጭ ነኝ ? 

ኮቪድ 19  በእርጉዝ ሴቶች ላይ ያለው ተፅንዖ በጥናት ላይ ነው። በ አሁን ሰዓት ያለው መረጃ ውስን ቢሆንም እርጉዝ ሴቶች ከሌላው ማህበረሰብ  በበለጠ ለከፋ የኮቪድ 19 ህመም የተጋለጡ ስለመሆናቸው ማስረጃ የለም። ቻይና ውስጥ የኮቪድ 19 የሳምባ ምች  ባለባቸው ዘጠኝ እርጉዝ ሴቶች በተደረገ ውስን ጥናት ፣ ነፍሰ ጡር ህመምተኞች እርጉዝ ካልሆኑ ህመምተኞች ተመሳሳይ ምልክቶች ነበሯቸው። ነገር ግን  እርጉዝ ሴቶች በእርግዝና ጊዜ በሰውነት ውስጥ ባሉ ለውጦች የተነሳ ለተለያዩ የመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽኖች ሊጋለጡ እንደሚችሉ ይታወቃል። ስለዚህ ራስሽን ከኮቪድ19 ለመጠበቅ ጥንቃቄዎችን ማድረግሽ በጣም አስፈላጊ ነው። 

ከኮቪድ ጋር የተያያዙ ምልክቶች ካየሽ ( ለምሳሌ ፥ ትኩሳት፣ ሳል፣ ትንፋሽ ማጠር ) ለሃኪምሽ አማክሪ። ወደጤና  ተቋማት ከመሄድሽ አስቀድመሽ ግን ደውዪ። 

  1. እራሴን ከኮቪድ 19 እንዴት መጠበቅ አችላለሁ ?

ከሌላው ማህበረሰብ ጋር በተመሳሳይ ጥንቃቄዎች አድርጊ

  • እጆችሽን አዘውትረሽ ቢያንስ ለአርባ ሰከንድ በሳሙና እና በውሃ በደንብ ታጠቢ ማለትም ሁሉንም ጣቶችሽን ( በጣቶችሽ መሃል እና የጣቶችሽን ጫፍ ጨምሮ )፣ የጥፍሮችሽን ውስጥ፣ የእጆችሽን መዳፍ እና የውጪኛው ክፍል መታጠብ ፥ ከቻልሽ ደግሞ ስለእጅ አስተጣጠብ ቪድዮዎችን ተመልከቺ።
  • አካላዊ ርቀትን ጠብቂ
  • ፊትሽን (አይንሽን፣ አግንጫሽን፣ አፍሽን ) ባልታጠበ እጅ አትንኪ
  • ካሳለሽ ውይም ካስነጠሰሽ አፍሽን እና አፍንጫሽን ክንድሽን አጥፈሽ ወይንም በሶፍት ሸፍኚ ፣ ሶፍት የተጠቀምሽ እንደሆነ ሶፍቱን ክዳን ባለው የቆሻሻ እቃ ውስጥ መጣልሽን እርግጠኛ ሁኚ።
  1. ኮቪድ 19 ከእናት ወደ ፅንስ ወይም አዲስ የተወለደ/ች ልጅ ሊተላለፍ ይችላል?

ኮቪድ 19 ካለባት ነፍሰ ጡር ሴት  በእርግዝና ወይም በወሊድ ጊዜ ቫይረሱ ወደ ፅንስ ወይም ሕፃን ማለፍ መቻሉ እስካሁን አይታወቅም፡፡ እስካሁን ድረስ ቫይረሱ በአሞኒቲክ ፈሳሽ ወይም በጡት ወተት ናሙናዎች ውስጥ አልተገኘም ፡፡

  1. ኮቪድ 19  ቢይዘኝ  በወሊድ ወቅት ተገቢውን አገልግሎት አገኛለሁ ?

ሁሉም እርጉዝ ሴቶች ፥ የተረጋገጠ ወይም የተጠረጠረ የኮቪድ 19  ኢንፌክሽን ያለባቸውን ጨምሮ በእርግዝና ፣በወሊድ እንዲሁም በድህረ ወሊድ ወቅት ጥራት ያለው ህክምና የማግኘት መብት አላቸው ፡፡

  1. ኮቪድ19 ቢይዘኝ ማጥባት እችላለሁ ? 

ሃኪምሽን አማክሪ!!

ይህ የሚወሰነው ከሃኪምሽ ጋር በመማከር ነው።

ልጅሽ እና አንቺ ለጊዜው ልትለያዩ ትችላላችሁ። 

ቤተሰብ ካለ የታለበ ወተት ሊያጠባልሽ ወይም ልታጠባልሽ ትችላለች።

እንድታጠቢ ከተወሰነ ግን በምታጠቢበት ጊዜ ፤

  • የፊት ማስክ (ጭንብል ) አድርጊ ፣
  • ህፃኗ/ኑን ከመንካትሽ በፊት እና በኋላ እጅሽን ታጠቢ
  • የነካሻቸውን ወለሎች በመደበኛነት  አፅጂ ፡፡
  1. ኮቪድ 19 ካለብኝ ልጄን መንካት እችላለሁ ?

     ሃኪምሽን አማክሪ!!

     ይህ የሚወሰነው ከሃኪምሽ ጋር በመማከር ነው።

  ልጅሽ እና አንቺ ለጊዜው ልትለያዩ ትችላላችሁ። አንቺ እና ልጅሽ አንድ ላይ እንድትቆዩ ከተወሰነ አለም የጤና ድርጅት እንደሚለው ልጅሽን ከመንካትሽ በፊት እና በኋላ  እጅሽን በሳሙና ታጠቢ እንዲሁም ሁሉንም ወለሎች ንጹህ አድርጊ ።

ሌሎችንም የሃኪምሽን ምክሮች ተግብሪ ። የአለም ጤና ድርጅት መረጃዎችን ተከታተይ ። ኮቪድ19 አዲስ እንደመሆኑ ምክሮች በየጊዜው ሊቀያየሩ ይችላሉ።

Sources :

  1. https://www.who.int/news-room/q-a-detail/q-a-on-covid-19-pregnancy-childbirth-and-breastfeeding

2. https://www.sciencedirect.com/science/article/pii/S0140673620303603

3. https://www.cdc.gov/coronavirus/2019-ncov/hcp/inpatient-obstetric-healthcare-guidance.html

የጤና ወግ

በመረጃ የተመሰረተ ሕክምና ብቻ ።  

………………………………………………………………………………………………………………………..

ይህ የጤና ወግ ድረ ገፅ ነው።
ስለ ጤንነታችሁ ማወቅ የምትፈልጉትን መረጃ የምታገኙበት ፣ በህክምና ባለሙያዎች የሚዘጋጅ የመረጃ ምንጭ ነው።
ሁልግዜም ከሀኪማችሁ ተማከሩ፣ ተጨማሪ መረጃ ከፈለጋችሁ የኛን ድረ ገፅ ጎብኙ።

በጥናት የተደገፈ መረጃ ብቻ እናቀርባለን።

የህክምና ባለሙያዎች ለህሙማኖቻችሁ የሚሆን የሚነበብ መረጃ ከፈለጋችሁ ይህን ግፅ ጠቁሟቸው። ህሙማኖቻችሁ እንዲያውቁት የምትፈልጉትን ነገር መረጃ ጠቅሳችሁ ፃፉልን፣ ስምችሁን ጠቅሰን እናወጣለን። የህክምና ተማሪዎች እንዲጽፉ እናበረታታለን።

በተጨማሪም በጤና ወግ ፖድካስት፣  በ ዩትዩብ ፣በ ትዊተር ፣ በ ፌስቡክ ፣ በቴሌግራም የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ገፆቻችን ታገኙናላችሁ ።

Share this: