By Jochebed Kinfemichael Suga, 4th year medical student at Myungsung Medical College
ጆኬቤድ ክንፈሚካኤል ሱጋ (ሚዩንግሱንግ ህክምና ኮሌጅ የ፬ አመት ተማሪ)
Reviewed/Approved by: Dr. Messay Tesfaye(Dermatovenereologist, Pediatric dermatology subspecialist)
በሰውነታችን ቆዳ ላይ በጥገኛ ተውሳክ ምክንያት ከሚፈጠሩ በሽታዎች ውስጥ አንዱ የእከክ በሽታ ነው፡፡ ይህም በሽታ በአይናችን ልናየው በማንችለው ሳርኮፕተስ ስኬቢ (sarcoptes scabiei) በሚባል ጥቃቅን ተዋስያን የሚመጣ ሲሆን ከፍተኛ የማሳከክ ባህሪ ያለው በሽታ ነው፡፡
የእከክ በሽታ እንዴት ይከሰታል?
የእከክ በሽታን የሚያመጣው ተውሳክ በቆዳ ላይ በሚያርፍበት ጊዜ ትንንሽ የሰረጎዱ ቦታዎች (burrows) በቆዳ ላይ ይፈጥራሉ፡፡ ይህ ቦታም እነዚህ ተዋስያን እንቁላሎቻቸውን የሚጥሉበት ቦታ ሲሆን ከእንቁላል ዑደተ ህይወት ሲወጡ ወደላይኛው የቆዳ ክፍል ጋር በመሆን ራሳቸውን በቆዳ ላይ ያሰራጫሉ፡፡ በቆዳ ላይ የእነዚህ ተዋሲያን መኖር በቆዳ ላይ የሚለቋቸው ፕሮቲኖች እና ቆሻሻዎች የሰውነት ቆዳን ስለሚያስቆጣ ከፍተኛ የማሳከክ ስሜት ይፈጠራል፡፡ ይህ ተዋስያን ሁሉም የሰውነታችን የቆዳ ክፍል ላይ ቢገኝም በሰውነት እጥፋት እና በአንዳንድ ቦታዎች ላይ በይበልጥ ይስተዋላል፡፡ በይበልጥ ከሚገኙባቸው ቦታዎች መሀከል በእጅ እና እግር ጣቶች መሀከል ባለ እጥፋት፣ በእምብርት አካባቢ፣ በብልት አካባቢ፣ በብብት ስፍራ፣ በጉልበት እጥፋት ቦታ፣ ከጥፍር ስር፣ ቀለበት እና የእጅ ሰአት ማሰሪያዎች አካባቢ ይገኙበታል፡፡ ይህ የእከክ በሽታ በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ ሲሆን በጠባብ ቦታዎች ላይ ተጠጋግተው በሚኖሩ ሰዎች መሀከል በቀላሉ ይዛመታል፡፡
የእከክ በሽታ ምልክቶች ምንድን ናቸው?
የእከክ በሽታ ከዚህ ቀደም ሳይያዝ የእከክ በሽታ አምጪ ተውሳክ በቆዳ ላይ ኖሮ የእከክ ምልክቶችን ከማየታችን በፊት ከ4-6 ሳምንታት ልንቆይ እንችላለን፡፡ ከዚህ ቀደም የእከክ በሽታ ለተያዘ ሰዉ ደግሞ ከ3-4 ሳምንታት ድረስ ምልክቶችን ሳያሳይ ሊቆይ ይችላል፡፡
የእከክ ቀዳሚ የሚባለው ምልክት ከአካባቢው ቀላ ብሎ የሚገኙ ትንንሽ እብጠቶች እና የቆዳ መቀየሮች ናቸው፡፡ ይህም ቀስ በቀስ በመዛመት ሰፋ ያለ የቆዳ ክፍልን ይይዛል፡፡
ለእከክ በሽታ ዋነኛ እና መሰረታዊ ምልክት ማሳከክ ሲሆን በይበልጥ ማታ ማታ ላይ ብሶ ይገኛል፡፡ ይህም ከህፃናት እንቅልፍ መረበሽ ጋር ይያያዛል፡፡
በተደጋጋሚ ከፍተኛ የሆነ ማከክ ለቆዳ መላጥ እና ለተደራቢ ኢንፌክሽን ያጋልጣል፡፡
የእከክ አይነቶች ምንድን ናቸዉ?
ሁሉም የእከክ አይነቶች የማሳከክ ባህሪ ቢኖራቸውም በሰውነት ቆዳ ላይ በሚያሳዩት ምልክቶች በተወሰነ መልኩ ልንለያያቸዉ እንችላለን፡፡
ክላሲክ እከክ(classic scabies): በብዛት የእጅ ጣቶች መካከል፣ ብብት አካባቢ፣ እምብርት እና ብልት አካባቢ ብሎም መቀመጫ መካከል እና ከጥፍር ስር አነስ አነስ ያሉ ሽፍታዎች ሆኖ ይታያል፡፡
ኖዱላር እከክ(nodular scabies)፡ ከአካባቢው ቀላ ያሉ ትንንሽ እባጮች በብብት እና ብልት አካባቢ በመሆን ይታያሉ።
ክረስትድ እከክ(crusted scabies)፡ በብዛት በሽታን የመከላከል አቅማቸው የደከመ እንደ እድሜያቸዉ የገፉ ፣ ኤችአይቪና የስኳር በሽታ ተጠቂዎች ላይ የሚታይ ሲሆን አጠቃላይ የሰውነት ክፍልን በማዳረስ እና በተለምዶ እከክ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ላይ ደግሞ የተከማቸ ቅርፊት በመስራት ይገለጣል። የእከክ አምጪ ተዋህሲያኑም በቁጥር ከፍ ብለዉ ይገኛሉ፡፡
የእከክ በሽታ እንዴት ይመረመራል?
የእከክ በሽታ በሽተኛ በሚናገረው እና ቆዳ ላይ በሚታየው ምልክቶች ብቻ በጤና ባለሙያዎች መለየት ይቻላል፡፡ የበሽተኛው እከክ በሽታ ካለበት ሰው ጋር ንክኪ መኖሩ ደግሞ የእከክ በሽታ የመሆኑ ሚዛን በይበልጥ እንዲያጋድል ያደርገዋል፡፡ ይህን የእከክ በሽታ ለማረጋገጥ የተለያዩ አጋዥ ምርመራዎችን እናደርጋለን፡፡ እነዚህም የእከክ በሽታን የሚያመጣውን ተውሳክ አጉልቶ ለማየት ይረዳናል፡፡
ማይክሮስኮፕ፡ የቆዳ ሽፍታዎች ከወጡባቸዉ ቦታዎች ላይ በመፈቅፈቅና ናሙና በመውሰድ አጉልቶ በሚያሳይ መሳሪያ የእከክ አምጪ ተውሳክን ለማይት መሞከር ነው፡፡
ደርሞስኮፒ፡ ይህ የመመርመርያ አይነት ተንቀሳቃሽ እና ነገሮች አጉልቶ የሚያሳይ መሳሪያ ነው፡፡ የጤና ባለሙያው የታካሚው ቆዳ ላይ ቅባት ወይም ጄልን በመቀባት መሳሪያውን ወደ ተቀባበት ቦታ በማስጠጋት የእከክ አምጪ ተውሳክ መኖር እና አለመኖሩን ለማየት እንዲሁም በዚህ ተውሳክ በቆዳ ላይ የተፈጠሩ ለውጦች (burrows) ለይቶ ለማወቅ ይጠቅመናል፡፡ ይህ መሳሪያ ነገሮችን በ10 እጅ ከፍ አድርጎ ስለሚያሳየን ያሉትን ተዋስያን በቀላሉ ለይቶ ለማወቅ ይጠቅመናል፡፡
የእከክ በሽታ ህክምና ምንድነው?
ለእከክ የሚታዘዘዉ መድሀኒት በቆዳ ላይ የሚቀባ ክሬም ሲሆን ለአዋቂዎች ከአንገት በታች እስከ እግር ድረስ ነው፡፡ ይህን መድሃኒት ብዙን ጊዜ ማታ ላይ የሚወሰድ ሲሆን መድሃኒቱ ከተወሰደ ከአንድ ሳምንት በኋላ በድጋሚ መወሰድ ይኖርበታል፡፡ ከጤና ባለሙያ ትዕዛዝ ውጪ በተደጋጋሚ ለእከክ የሚሰጡ መድሃኒቶችን መጠቀም በቆዳ ላይ ያለውን ቁስል እና ማሳከክ ሊያባብስ ይችላል፡፡ የክረስትድ እከክ አይነት በተለየ ጠንከር ባለ መድሃኒት ይታከማል፡፡
የእከክ በሽታ እንዳለበት የተረጋገጠ እና ካለበት ሰው ጋር በቅርበት አብረው የሚኖሩ ሰዎች እንዳለ የእከክ መድሃኒቶች መጠቀም ይኖርባቸዋል፡፡ በቅርበት የሚኖሩ ሰዎች ምልክት ባይኖራቸው እንኳን መታከም አለባቸው፡፡ ይህንንም በማድረግ የእከክ ወረርሽኝን መከላከል ይቻላል፡፡
የእከክ በሽታ እንዴት መከላከል ይቻላል?
የእከክ በሽታ ሲታከም ለቆዳ የሚሰጥ መድሃኒት ብቻ በቂ አይደለም፡፡ የእከክ በሽታ የሚያመጣውን ተውሳክን በማጥፋት ዳግመኛ እንዳይመለስ መቆጣጠር ይገባል፡፡ ተመልሶ እንዳይመጣ ለመከላከል ከምንወስዳቸው እርምጃዎች ውስጥ
- ሁሉንም ልብሶች በፈላ(በሞቀ) ውሀ ማጠብ
- በቀላሉ መታጠብ የማይቻሉ እንደአልጋልብስ ያሉ ልብሶችን በላስቲክ በማሸግ ማቆየት
እነዚህን በማድረግ የእከክ በሽታ የሚያመጣውን ተውሳክ ማጥፋት ይቻላል፡፡
የጤና ወግ
ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።
የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።
https://linktr.ee/Yetena_Weg