Written by በእምነት የሻው ሳልህ (በቅ/ጳ/ሚ/ሜ/ኮ የ5ኛ አመት ተማሪ)
Bemnet Yeshaw Saleh, 5th year medical student at St Paul hospital millennium medical college.
Reviewed/Approved by: Dr.Lemma Zewde (Editor at Yetena Weg/ Internist)
ኮሮና የሚባለው አንድ የቫይረስ ዓይነት ሲሆን ከራይኖ ቫይረስ በመቀጠል እጅግ የተለመደ የጉንፋን አምጪ ተህዋስ ነው፡፡ ብዙ የኮሮና ቫይረስ ዓይነቶች ሲኖሩ በቅርቡ ተከስቶ ሁላችንን ቤት ያዘጋን ኮቪድ 19 ከእነዚህ አንዱ አይነት ነው፡፡ እንደሚታወቀው የኮቪድ 19 ምልክቶች ከሰው ሰው ቢለያዩም ብዙ ጊዜ ትኩሳት፣ ሳል፣ የትንፋሽ ማጠር፣ ተቅማጥ የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡
ኮቪድ ምን ያህል ጎጂ እንደሆነ ያልተረዳ ይኖራል ማለት ይከብዳል፡፡ እስካሁን ድረስ በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ6 ሚሊዮን በላይ ደርሷል፤ እንዲሁም አሁን ላይ ብቻ ከስድስት መቶ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በበሽታው ተይዘዋል፡፡ይህን ሁሉ በመመልከት ታዲያ መጠንቀቅ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ መረዳት አይከብድም፡፡ ለኮቪድ 19 ማድረግ ከምንችላቸው ጥንቃቄዎች መካከል ደግሞ ክትባት መከተብ አንዱ ነው፡፡
ክትባት ማለት አንድን በሽታ ለመዋጋት ያለንን አቅም የሚያዳብርልን ንጥረነገር ነው፡፡
ይህንንም ለማድረግ ክትባት የበሽታ አምጪውን ተህዋስ ከሚመስል ነገር ይዘጋጃል፤ ከዚያም ወደ ሰውነታችን ሲገባ አካላችን ተዋግቶ ያሸንፈውና ያሸነፈበትን መንገድ መዝግቦ ይይዘዋል ፤ ከዚያ በኋላ ትክክለኛው በሽታ አምጪ ተህዋስ ወደ አካላችን ቢገባ እንኳን በፊት ክትባቱን የተዋጋበትን ልምድ በመጠቀም ማሸነፍ እንዲችል ይረዳዋል ማለት ነው፡፡ የመጀመሪያው ክትባት ከ200 ዓመት በፊት ጀምሮ ከተሰራ በኋላ ብዙ ክትባቶች ለተለያዩ በሽታዎች በመመረት ጥቅም ላይ ውለዋል፤ እየዋሉም ይገኛሉ፡፡
ስለኮቪድ 19 ክትባት የሚነገሩ የተሳሳቱ ትርክቶች
አንድ ጊዜ በሽታው ከያዘኝ መከተብ አያስፈልገኝም
ጥናቶች እንደሚያሳዩት መከተብ ከሁሉም የተሻለ ከበሽታው መጠበቂያ ዘዴ ነው፡፡ ይህ በሽታው ይዟቸው ለሚያውቁም ለማያውቁም ሰዎች ይሰራል፡፡ በሽታው ከያዘም በኋላ ክትባት ያልተከተቡ ሰዎች ክትባቱን ከወሰዱ ሰዎች ይልቅ በ2 እጥፍ የበለጠ በበሽታው የመጠቃት እድል እንዳላቸው አንድ ጥናት አመልክቷል፡፡ ስለዚህ በሽታው ይዞን ቢያውቅም መከተብ አስፈላጊ ነው፡፡
ክትባቱን ከወሰድን በኋላ ለበሽታው ጥንቃቄ ማድረግ አይጠበቅብንም
ይህ አባባል ስህተት ነው፤ ክትባቱን መውሰድ ሙሉ በሙሉ ከበሽታው ይከላከላል ማለት ስላልሆነ የሁል ጊዜውን ጥንቃቄ መቀጠል ይጠበቅብናል፡፡ መከላከያ መንገዶቹም ብዙ ጊዜ ስንሰማቸው የነበሩት ፣ ትኩሳት ወይም ሳል ካለበት ሰው 2 እርምጃ ያህል መራቅ፣ እጅን በንጹህ ውሃና ሳሙና መታጠብን አለመዘንጋት፣ በደንብ ሳንታጠብም አፍና አፍንጫን አለመንካት፣ በተለይ የህመም ስሜት ካለብን ሰዎች ወደ ሚሰበሰቡበት ቦታ አለመሄድ፣ በምናስልበት ጊዜ አፍና አፍንጫን በሶፍት ወይም በእጅ ክርን እጥፋት መሸፈን፣ በስራ ቦታ ወይም መኖሪያ መስኮት በመክፈት በቂ አየር እንዲኖር ማስቻል ይገኙበታል፡፡
ክትባቱ በራሱ የኮቪድ ኢንፌክሽንን ሊያስይዝ ይችላል
ይህ ፈጽሞ ከእውነት የራቅ አባባል ነው። የኮቪድ 19 ክትባት ተግባር በአካላችን ውስጥ ከቫይረሱ ጋር የሚመሳሰል ፕሮቲን እንዲመረት በማድረግ ሰውነታችን ለቫይረሱ ሳይጋለጥ ስለቫይረሱ እውቀት እንዲኖረው የሚያስችል አቋራጭ ጎዳናን መፍጠር ነው፡፡ ይህ ፕሮቲን ምንም አይነት ኢንፌክሽን አያመጣም፡፡
ክትባቱ አደገኛ የሆኑ የጎንዮሽ ጉዳቶች አሉት
እርግጥ ነው ክትባቶቹ የጎንዮሽ ጉዳቶች ሊኖሯቸው ይችላሉ፤ አብዛኞቹ ግን ጊዜያዊ እና ብዙም የማያሰጉ ናቸው፡፡ ከምልክቶቹ መካከል የተወጉበት ቦታ ላይ የህመም ስሜት መሰማት፣ ለአንድ እና ሁለት ቀን የሚቆይ የራስ ምታት ወይም ትኩሳት፣ የድካም ስሜት፣ ማቅለሽለሽ፣ የጡንቻና መገጣጠሚያ ህመም፣ እንዲሁም ህጻናት ላይ እንቅልፍና ለቅሶ መብዛት ይጠቀሱበታል፡፡ እነዚህ ምልክቶች እስካልቆዩ ድረስ የሚያሳስቡ አይደሉምና መፍራት አያስፈልግም፡፡
ልክ እንደ ማንኛውም መድሃኒት ክትባቱ እጅግ አልፎአልፎ የሚፈጠሩ የጎንዮሽ ጉዳቶች ሊኖሩት ስለሚችሉ ክትባቱን ከወሰድን በኋላ ማንኛውም ዓይነት የተለየ ምልክት ካየን ወደ ጤና ተቋም መሄድ ያስፈልጋል፡፡
ክትባቱ ምዕራባውያኑ እኛን የሚቆጣጠሩበት ዘዴ ነው
ይህን አባባል ብዙ ሰዎች በዕለት ዕለት እንቅስቃሴያችን ጊዜ ያነሱታል፤ ክትባቱን ምዕራባውያኑ እኛን ሊቆጣጠሩን፣ አለፍ ሲልም የሰይጣን ተገዢ ሊያደርጉን ፈልገው ነው የሚሰጡን የሚሉ አስተያየቶችም ሲሰጡ ይደመጣል፡፡ መታወቅ ያለበት ነገር ክትባቱ ምንም ዓይነት መቆጣጠሪያ እንክብል እንደሌለው ነው፡፡ ስለዚህ ይህም መሰረት የሌለው ሀሳብ እንደሆነ ልንረዳ ያስፈልጋል፡፡
ክትባቱ መሃንነትን ያመጣል
ይህ ሌላ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ክትባቱ የሚሰራበት መንገድ ከልጅ መውለድ ችሎታ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡
እንግዲህ በተለያዩ አጋጣሚዎች ከምንሰማቸው የተሳሳቱ መረጃዎች ራስን መቆጠብ(በተለይ የማይታመኑ ምንጮች ካሏቸው ማህበራዊ ሚዲያዎች) እና ከጤና ባለሙያ፣ እንዲሁም በሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ ተአማኒ ሊሆኑ የሚችሉትን መረጃዎች በመስማት ራስንና ቤተሰብን መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ ኮቪድ ገና አልጠፋም፤ እስከ አሁንም በሀገራችን እንደ ዓለም የጤና ድርጅት ዘገባ በትንሹ ከ500 ሺህ ጊዜ በላይ በላብራቶሪ ምርመራ የተረጋገጡ የኮቪድ ኬዞች አጋጥመዋል፡፡ አሁንም ብዙ ሰዎች በበሽታው ተይዘው ይገኛሉና መዘናጋት ዋጋ ያስከፍላል፡፡
ክትባት መከተብ አንተን/ አንቺን ብቻ ሳይሆን ማህበረሰቡንም ከበሽታ ይጠብቃል፡፡ እንከተብ!!
References
Reduced risk of reinfection with SARS-CoV-2 After COVID-19 Vaccination- Kentucky, May-June 2021. http://pubmed.ncbh.nlm.nih.gov
When good messages go wrong: perspectives on COVID-19 vaccines and vaccine communication from generally vaccine accepting individuals in Canada. https://pubmed.ncbi.nlm.nih.gov
Myths Vs Facts, making sense of COVID-19 vaccine misinformation. http://www.bu.edu
Ministry of health official website. http://www.moh.gov.et
Possible side effects after getting a COVID 19 vaccine
CDC. http://www.cdc.gov
የጤና ወግ
ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።
የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።
https://linktr.ee/Yetena_Weg