Written by – ረድኤት ወልደሩፋኤል (በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊንየም ህክምና ኮሌጅ ኢንተርን)

Reviewed by  – ዶ/ር  ቅድስት ገ/ፃዲቅ  (የፅንስና ማህፀን ስፔሻሊት ሀኪም)

 

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ምንድነው?

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን  የሴቶችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊና ፖለቲካዊ ስኬቶች የሚያከብር ቀን ነው።  ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በዓለም ዙሪያ በሚገኙ በርካታ አገሮች ይከበራል። ይህ ቀን ሴቶች በብሔር፣ በጎሳ፣ በቋንቋ፣ በባህላዊ፣ በኢኮኖሚም ይሁን በፖለቲካ ልዩነት ሳይገለሉ በስኬታቸው እውቅና ያገኙበት ቀን ነው። በተጨማሪም ቀኑ የፆታ እኩልነትን ለማፋጠን እርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ የሚያሰማ ቀን ነው።

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ታሪክ

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በይፋ ዕውቅና ተሰጥቶት መከበር የጀመረው እ.ኤ.አ በ1977 በሰሜን አሜሪካና በመላው አውሮፓ የነበሩ እንቅስቃሴዎችን ተክትሎ ነው፡፡ ዕውቅና ያገኘው በተጠቀሰው አመት ቢሆንም የመጀመሪያው  የሴቶች ቀን የተከበረው በ1909 ዓ.ም. ነው።  ይህም በአሜሪካ ሶሻሊስት ፓርቲ  በብሔራዊ ክብረ ባህል ደረጃ የተከበረ ሲሆን፡ በ በመጋቢት 8 ቀን 1857እ.ኤ.አ በኒው ዮርክ ከተማ የሴቶች የልብስ ሰራተኞች ያካሄዱትን ተቃውሞን ለመዘከር ነበር፡፡ የመጀመሪያው የሴቶች ቀን በአሜሪካ መከበርን ተከትሎ በቀጣይ አመታት በተልያዩ የአለም ክፍሎች መከበር ቀጥሏል፡፡

በመጋቢት 19 ቀን 1911እ.ኤ.አ የሴቶች ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ በኦስትሪያ ፣ በዴንማርክ ፣ በጀርመንና በስዊዘርላንድ ከአንድ ሚልዮን በሚበልጡ ሰዎች ተከበረ ። ክብረበአሉም የሴቶች ድምፅ የመስጠት (የመምረጥ) መብት እና የሕዝብ ሥልጣን የመያዝ መብት እንዲሰጣቸው ጥሪ ያስተላለፈ ነበር።

በቀጣይ አመታትም የዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን መሰራጨቱን ቀጠለ፡ እ.ኤ.አ. በ1922 ቻይና ደረሰ። በቻይና 1949 እ.ኤ.አ, ማርች 8 (1941አም፣ የካቲት 29) ቀን ለሴቶች “ግማሽ የሥራ ቀን” ተብሎ ታወጀ፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በማርች 8 (የካቲት 29) መከበሩን ቀጥሏል።

ይህንን ዓለም አቀፍ ዕውቅና ተከትሎም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እ.ኤ.አ በ1975 የሴቶች ቀን ማክበር ጀመረ፡ ከ2 አመት በኋላም በድርጅቱ አባል ሀገራት ጸድቆ ማርች 8፣ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን (IWD) ተብሎ ተሰየመ፡፡

አሁንም የሴቶችን ቀን ማክበር አለብን? ለምን?

አዎ!!

ከላይ እንደተጠቀሰው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን (IWD) የሴቶችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊና ፖለቲካዊ ስኬቶች የሚያከብር በተጨማሪም የፆታ እኩልነትን ለማፋጠን እርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ የሚያሰማ ክብረ ባእል ነው፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ መሻሻል ቢታይም የሥርዓተ-ፆታ አለመመጣጠን በብዙ የዓለም ክፍሎች ተስፋፍቶ የሚታይ ጉዳይ ነው። ሴቶች በትምህርት፣ ሥራ፣ የጤና አጠባበቅ እና የፖለቲካ ዘርፎች እኩል እድሎችን እንዳያገኙ አድልዎ እና እንቅፋት ይደርስባቸዋል፡፡

የአለም ኢኮኖሚክ ፎረም የአለም አቀፍ የስርዓተ-ፆታ ልዩነት ሪፖርት እንደሚናገረው አሁን ባለው ፍጥነት የተሟላ ዓለም አቀፍ የሥርዓተ-ፆታ እኩልነትን ማግኘት እስከ 2158 እ.ኤ.አ  ድረስ ወይም 134 ዓመታት ይወስዳል:። ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ማክበር የሥርዓተ-ፆታ እኩልነትን ለማስፈን አሁንም መሠራት ያለበትን ሥራ ለማስታወስ ያገለግላል። ሴቶች ስለሚገጥሟቸው ተግዳሮቶች ግንዛቤን በማሳደግ ሁሉንም አሳታፊ እና ፍትሃዊ ማህበረሰብ ለመፍጠር መሰረት ይሆናል።

በተጨማሪም ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ብዙ መሰናክሎችን ያልፉ እና ስለሴቶች ያለውን አሉታዊ አመለካከቶችን ያፈረሱ ሴቶች ያስመዘገቡት ውጤት የሚከበርበት ወቅት ነው። ከሳይንቲስቶች እና አክቲቪስቶች ጀምሮ እስከ አርቲስቶች እና ስራ ፈጣሪዎች ድረስ ሴቶች ሊታሰብ በሚችለው በሁሉም መስክ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል። እነዚህን ስኬቶች በማጉላት የወደፊት ሴት ትውልዶች ህልማቸውን እንዲያሳኩ እና ሙሉ አቅማቸውን እንዲረዱ ማነሳሳት እንችላለን።

በተጨማሪም ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ማክበር በዓለም ዙሪያ ባሉ ሴቶች መካከል አብሮነት እንዲኖር ይረዳል። የተለያዩ አስተዳደግ እና ልምድ ያላቸው ሴቶች እርስ በርስ በመደጋገፍ ድምጻቸውን የሚያሰሙበት ቀን ነው። ሴቶች በአንድነት በመቆም በአለም አቀፍ ደረጃ ለውጥ እንዲመጣ መምከር እና የፆታ እኩልነትን የሚያበረታቱ ፖሊሲዎችን መግፋት ይችላሉ።

እርምጃን ማፋጠን፡ የ2025 የአለም አቀፍ የሴቶች ቀን መሪ ቃል

የ2025 ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን (IWD) ዘመቻ መሪ ቃል “እርምጃን ማፋጠን” የሚል ነው:: መሪ ቃሉ ወደ ሙሉ የፆታ እኩልነት ለመድረስ እድገትን ለማፋጠን የሚደረግ ጥሪ ነው።

የአለም ኢኮኖሚክ ፎረም የአለም አቀፍ የስርዓተ-ፆታ ልዩነት ሪፖርት እንደሚናገረው አሁን ባለው ፍጥነት የተሟላ ዓለም አቀፍ የሥርዓተ-ፆታ እኩልነትን ማግኘት እስከ 2158 እ.ኤ.አ  ድረስ ወይም 134 ዓመታት ይወስዳል:: ይህ ማለት ከአሁን በኋላ ለአምስት ትውልዶች የሥርዓተ-ፆታ እኩልነት ሳይከበር ይቆያል ማለት ነው። እ.ኤ.አ. በ2024 68.5% የሚሆነው የአለም አቀፍ የስርዓተ-ፆታ ልዩነት ተስተካክሏል፣ ይህም ካለፈው አመት የ0.1 በመቶ ነጥብ ብቻ መጠነኛ መሻሻል ያሳያል። ይህ አዝጋሚ እድገት የሴቶችን እድገት የሚያደናቅፉ እንቅፋቶችን ለማስወገድ አስቸኳይ እና ወሳኝ እርምጃዎችን አስፈላጊነት ያሳያል::

የሥርዓተ-ፆታ ክፍተቱ በአራት ቁልፍ ገጽታዎች ይገመገማል፡- ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ እና ዕድልየትምህርት ዕድልጤና እና ህልውና እና የፖለቲካ ተሳትፎ። እንደ የትምህርት ዕድል እና ጤና ባሉ ዘርፎች የሥርዓተ-ፆታ ክፍተት መስተካከል ቢያሳይም በፖለቲካዊ እና በኢኮኖሚ ተሳትፎ ላይ የነበሩ ከፍተኛ ልዩነቶች አሁንም ቀጥለዋል።

የኢኮኖሚ ተሳትፎ እና እድል፡- በ2024 በአለም አቀፍ የሰው ሃይል ተሳትፎ ውስጥ ያለው እኩልነት 65.7%  ደርሷል፣ ይህም በኮቪድ ወረርሽኝ ጊዜ ከነበረበት 62.3% መሻሻል ያሳየ ነው። ይሁን እንጂ ሴቶች በሁሉም ኢንዱስትሪዎች ውስጥ በአመራር ሚና ውስጥ ዝቅተኛ ውክልና ነው ያላቸው::. መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የሴቶች ውክልና ከመግቢያ ደረጃ እስከ ከፍተኛ የሥራ አስፈፃሚ ድረስ ከነበረበት አሽቆልቁሏል: ይህ በሙያ እድገት ላይ ሴቶች መሰናክሎች እንዳሉባቸው ያሳያል።

የፖለቲካ ማጎልበት፡- ይህ ልኬት ትልቁን ክፍተት ያሳያል፣ በአለም አቀፍ ደረጃ የተዘጋው የስርዓተ-ፆታ ልዩነት  22.5% ብቻ ነው። ምንም እንኳን የሴቶች የፖለቲካ ውክልና በተለያዩ ደረጃዎች ቢጨምርም፣ የከፍተኛ ደረጃ የፖለቲካ ሹመቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ የሴቶች ተሳታፊነትአይታይም።

ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራትን ለይተን ስንመለከት የ2024 የአለም አቀፍ የስርዓተ-ፆታ ልዩነት ሪፖርት እንደሚያመለክተው ክልሉ ከአጠቃላይ የስርዓተ-ፆታ ክፍተቱን 68.2% ዘግቷል። በተለይም ሴራሊዮን ከነበረችበት 32 ደረጃዎችን በማሻሻል በአለም አቀፍ 80ኛ ደረጃ ላይ ለመድረስ ከፍተኛ እድገት አሳይታለች። እነዚህ እድገቶች ቢኖሩም በኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ እና በትምህርት ተደራሽነት ላይ ከፍተኛ ልዩነቶች ቀጥለዋል፣ ይህም ስርአታዊ መሰናክሎችን ለመፍታት እና አሃጉሩ ውስጥ ያሉ ሴቶችን ሁሉን አቀፍ እድገት ለማምጣት የተፋጠነ እርምጃ እንደሚያስፈልግ ያመልክታል።

ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የፆታ እኩልነትን በማሳደግ ረገድ ጉልህ እድገት አሳይታለች። የአለም ኢኮኖሚክ ፎረም የአለም አቀፍ የስርዓተ-ፆታ ልዩነት ሪፖርት በ2024 ኢትዮጵያ የስርዓተ-ፆታ ልዩነትን ከነበረበት በ0.709 በማጥበብ ሀገሪቱን ከ146 ሀገራት 79ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧል። ይህም ካለፉት አመታት ተከታታይ መሻሻልን የሚያሳይ ሲሆን ኢትዮጵያ በ2020 በ0.71 በ82ኛ ደረጃ ላይ ነበረች። በፖለቲካዊ ውክልና ውስጥ ጉልህ ለውጦች ታይተዋል። ይሁን እንጂ የፆታ እኩልነትን ሙሉለሙሉ ከማሳካት የሚገቱ ተግዳሮቶች አሁንም ቀጥለዋል፣ በተለይም በኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ። በ2016 ከነበረበት 77.8% ተሳትፎ በ2023 ወደ 46.8% የሴት ሰራተኛ ሃይል ተሳትፎ መጠን ዝቅ ብሏል፤ ይህም የስርዓተ-ፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥ መስተካከል ያለባቸውን የስርአት ችግሮች ያሳያል።

የአለም አቀፍ የሴቶች ቀን 2025 “ድርጊት ማፋጠን” በሚል መሪ ሃሳብ ለስርዓተ-ፆታ እኩልነት የሚደረገውን ጥረት ለማፋጠን ያለውን ወሳኝ አስፈላጊነት ያጎላል። የተጠናከረ ተነሳሽነት ከሌለ ፣ አሁን ባለው ፍጥነት ብዙ ትውልዶች በስርዓተ-ፆታ ላይ የተመሰረቱ ልዩነቶች ባለባት አለም እንደሚቀጥሉ ይጠቁማል። እርምጃን ማፋጠን ጠንካራ ፖሊሲዎችን መተግበር፣ ሁሉን አቀፍ የስራ ቦታዎችን ማጎልበት እና እኩልነትን የሚያራምዱ የህብረተሰብ ደንቦችን ተፈጻሚ ማድረግን ያካትታል። እነዚህ እርምጃዎች የስርዓተ-ፆታ እኩልነት የሚረጋገጥባት ፍትሃዊ አለም በአስቸኳይ ለመገንባት ያስችለናል።

በተጨማሪም፣ የዘንድሮው 2025 የአለም አቀፍ የሴቶች ቀን  በተባበሩት መንግስታት ሴቶች ካስተዋወቀው ጭብጥ ጋር ይስማማል፡ “ለሁሉም ሴቶች እና ልጃገረዶች፡ መብት፣እኩልነት፣ ማጎልበት” ይህም ሁሉም ሴቶች እና ልጃገረዶች እኩል እድሎችን እንዲያገኙ እና በሁሉም የህይወት ዘርፎች እንዲመሩ ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን ያጎላል.

እነዚህ ሁለት ጭብጦች እርስ በርስ ይደጋገፋሉ:: የዓለም አቀፍ የሴቶች “እርምጃን ማፋጠን” የሥርዓተ-ፆታ ክፍተቱን ለመዝጋት አፋጣኝ እና ደፋር እርምጃዎችን ይጠይቃል, የተባበሩት መንግስታት “ለሁሉም ሴቶች እና ልጃገረዶች” እነዚህ ድርጊቶች ፍትሃዊ እና አካታች መሆናቸውን ያረጋግጣል, እንዲሁም ማንንም ሴት ወደ ኋላ መተው እንደሌለባት ይጠቅሳል:: ሁለቱንም አብረን ስንረዳቸው ፍጥነትን ከአካታችነት ጋር በማጣመር ለውጥን ማፋጠን ማለት በዓለም ዙሪያ ያሉ ሴቶች የሚያጋጥሟቸውን የተለያዩ ተግዳሮቶች እውቅና የመስጠት እና የመፍታት ጥረቶች የተገለሉ ማህበረሰብ አባል የሆኑ ሴቶችን ታሳቢ እና ተደራሽ ማድረግ ይጠበቅበታል ማለት ነው።

እድገትን በእውነት ለማፋጠን በሁሉም የህብረተሰብ ደረጃ የጋራ እርምጃ ያስፈልጋል። ድርጅቶች አካታች የስራ ቦታዎችን በማጎልበት በአመራር ላይ የሥርዓተ-ፆታ ክፍተቶችን በመዝጋት፣ መንግስታት የሴቶችን መብት ለመጠበቅ ጠንከር ያሉ ፖሊሲዎችን በማውጣት፣ እና ግለሰቦች አድሏዊ ጉዳዮችን በመቃወም በማህበረሰባቸው ውስጥ ፍትሃዊነት እንዲሰፍን በመሟገት ሴቶች ቀጣዩ ትውልድ መሪዎች እንዲሆኑ ማብቃት ይቻላል።

ይህ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን፣ ከውይይቶች አልፈን ወደ እውነተኛ ለውጥ የሚያመጡ ደፋር ድርጊቶችን እንድንሸጋገር ፣ የፆታ እኩልነት የሩቅ ግብ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ ላሉ ሴቶች የአሁን እውነታ እንዲሆን ማድረግ እንዳለብን ያሰምራል።

 

 

References

https://www.internationalwomensday.com/

https://www.unwomen.org/en/news-stories/announcement/2024/12/international-womens-day-2025-for-all-women-and-girls-rights-equality-empowerment

https://yourpeopleareyourpower.com/international-womens-day-2025-theme/

https://www.weforum.org/press/2024/06/parity-for-women-remains-five-generations-away-but-historical-election-year-offers-hope/

https://africa.unwomen.org/sites/default/files/2024-10/overview_-_developments_and_achievements_in_the_uptake_and_use_of_gender_data_and_statistics_-_ethiopia.pdf?

https://africa.unwomen.org/sites/default/files/2024-07/abridged_version-ethiopia_country_gender_profile.pdf