በዶ/ር አዘነ ደሴ መንግስቱ እና በዶ/ር መሀመድ በድሩ

 

የልብ ህመም ሳይኖር በተፈጥሮ ሁኔታ እርግዝና በልብ አሠራር ላይ ምን ተፅእኖ ያስከትላል?

በነፍሰጡርነት ወቅት በተፈጥሮ ሁኔታ በደም ሥር የሚዘዋወረው የደም መጠን እስከ ሃምሳ ፐርሰንት የሚጨምር ሲሆን ይህም ለውጥ በልብ አሠራር ላይ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል በመሆኑም በእርግዝና ወቅት የሚከሰተውን ከፍተኛ የልብ አሠራር ጫና ለመቋቋም ልባችን ጤነኛ መሆን ይኖርበታል ማለት ነው፡፡

 

ለመሆኑ የተፈጥሮ የልብ ህሙማን እናቶች ማርገዝ ይችላሉን?

አስፈላጊው ህክምና የተደረገላቸው የተፈጥሮ የልብ ህሙማን እናቶች ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ በሚመለከተው ባለሙያ የህክምና ክትትል እስካደረጉ ድረስ አብዛኛዎቹ ልጅ መውለድ ይችላሉ ይሁንና የሚከተሉት ችግሮች ያለባቸው የልብ ህሙማን እንዳያረግዙ ይመከራል፣

  • ከፍተኛ የሳንባ የደም ግፊት (ፐልመናሪ ሃይፐርቴንሽን)  
  • በሐኪም የተረጋገጠ የልብ ድካም ካለ (በተለይም የልብ መጭመቅ አቅም በልብ አሰራር መለኪያ ከሰላሳ ፐርሰንት በታች ከሆነ) 
  • ህክምና ያልተደረገላቸውና  በልባቸው ክፍል ከፍተኛ የቫልቭ ጥበት ያለባቸው የልብ ህሙማን ሴቶች
  • የማርፋን ሲንድረም ያለባቸውና ከግራ የታችኛው የልብ ክፍል የሚነሳውና ዋናው የደም ቧንባ የመስፋት (የመለጠጥ) ችግር ያለባቸው እናቶች፡፡

 

የልብ ህመም ጠቋሚ ምልክቶች ምንድናቸው?

አንዳንድ ጊዜ ሴቶች የልብ ህመም ያለባቸው መሆኑን ሳያውቁ ሊያረግዙ ስለሚችሉ የሚከተሉት ምልክቶች የልብ ህመምን ጠቋሚ በመሆናቸውን እንዚህን ምልክቶች ካስተዋሉ የሚመለከተውን የጤና ባለሙያ ማማከር ይኖርባቸዋል፣

  • ያልተለመደ የድካም ስሜት
  • ተከታታይነት ያለውና አክታ ያዘለ ሳል
  • የደረት ውጋት 
  • ራስን መሳት
  • ተከታታይነት ባለው ሁኔታ የልብ ምት ጎልቶ ለራስ መሰማት
  • ከፍተኛ የልብ ምት መጨመር

 

የልብ ህሙማን ሴቶች እርጉዝ ሲሆኑ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች ምንድናቸው?

በእናት ላይ፣

  • በእርግዝና ወቅት የሚጨምረውን ተፈጥሮአዊ የደም መጠንና ዝውውር ልባቸው መሸከም ስለማይችል የልብ ህመማቸው የመባባስ እና የሞት አደጋም ሊከሰት ይችላል
  • በልባቸው ውስጥ ካሉት ቫልቮች በኦፕራሲዎን የተተካ የብረት ነክ ቫልቭ ካለ ያልተስተካከለ አሰራር መኖር 
  • የደም መርጋት ችግር፡- ይህ ችግር ተፈጥሮአዊ ከሆነውና ከእርግዝና ጋር የተያያዘ በቀላሉ የደም መርጋት ሁኔታና የሰው ሰራሽ ቫልቮች ልብ ውስጥ መኖር ጋር የተያያዘ ክስተት ነው፡፡

በፅንሱ ላይ፣

  • ያልተስተካከለ የፅንስ እድገት
  • ያለ ጊዜ መወለድና ተያያዥ ችግሮች
  • እናት ከምትወስዳቸው መድሐኒቶች ጋር ተያያዥነት ያላቸው የመድኃኒት የጎንዮሽ ችግሮች
  • አልፎ አልፎ እናት የልብ ደዌ ተፈጥሮአዊ ከሆነ ችግሩ በሚወለደው ህፃን ላይም ሊከሰት ይችላል፡፡

 

የልብ ህሙማን እናቶች ልጅ መውለድ በሚፈልጉ ጊዜ ማድረግ ያለባቸው ወሳኝ ነገሮች ምንድናቸው?

  • በመጀመሪያ ካለባቸው የልብ ህመም ደረጃ አንፃር ማርገዝ እንደሚችሉና እንደማይችሉ የሚከታተላቸውን የልብ ሐኪም ማማከር
  • የልብ ኦፕራሲዮን ያደረጉና በልባቸው ውስጥ ሰው ሰራሽ የብረት ቫልቭ ያላቸው የልብ ሕሙማን እናቶች ባያረግዙ የሚመከር ሲሆን ነፍሰጡር ከሆኑ ግን በሚመለከተው ባለሙያ ልዩ ክትትል እንደሚያስፈልጋቸው መረዳት ያፈልጋል፡፡
  • ማርገዝ እንደሚችሉ ከባለሙያ ካረጋገጡ በኃላ በእርግዝና ወቅት በፅንስና በልብ ሐኪሞች አስፈላጊውን የቅርብ ክትትል ማድረግ