በዶ/ር ናታን ሙሉብርሃን (የድንገተኛ እና ፅኑ ህክምና ስፔሻሊስት ሀኪም)

    የልብ ድካም በአለማችን ቁጥር አንድ ገዳይ በሽታ ነው። በአለማችን ላይ በአመት ወደ ሰባት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በልብ ድካም ሳቢያ ህይወታቸውን የሚያጡ ሲሆን በሃገራችንም ቁጥሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ በአሳሳቢ መልኩ እየጨመረ ይገኛል።  የልብ ድካም ሲከሰት ወደ ልብ ጡንቻ የሚዘዋወረው ደም በከፊል ወይም ሙሉ ለሙሉ የሚቋረጥ ሲሆን ወደ ልብ ህዋሳት መሄድ ያለበት ኦክስጅንና ሌሎች ጠቃሚ ንጥረ ነገሮች ስለማይደርሱ የልብ የመምታት ስራ ይስተጓጉላል ማለት ነው። 

የልብ ድካም በዋነኝነት መንስኤው የልብ ደም ስር መጥበብ ሲሆን በተጨማሪም የኦክስጅን እጥረት ፣ የልብ ደም ስር መኮማተርና የልብ ቀዶ ህክምና ሌሎች የልብ ድካም መነሻ ሊሆኑ ይችላሉ። 

የልብ ደም ስር መጥበብ እንዴት ይመጣል?

 

የልብ ጡንቻዎች ደም በተገቢው መልኩ ወደ ሰውነታችን ለማድረስ ያልተቋረጠ ኦክስጅንና ሌሎች እንደ ግሉኮስ ያሉ ንጥረ ነገር ያስፈልጋቸዋል፤ ይህንንም ለማግኘት ቀጫጭን የሆኑ የልብ የደም ስሮች በልብ ጡንቻዎች መሃል ተዘርግተው ይገኛሉ። አዘውትረን ቅባትና ስብ የበዛበት ምግቦችን የምንጠቀም ከሆነ እንደ ኮሌስትሮል ያሉ መጥፎ ስቦች በልብ ደም ስር ውስጥ መከማቸት ይጀምራ ፤ በጊዜ ሂደትም (እስከ 10 አመታት) የልብ የደም ስር መጥበብን ያስከትላል። ከልክ ያለፈ ውፍርት፣ የደም ግፊት፣ ሲጋራ ማጨስ፣ የአካል እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ የስኳር በሽታ ለልብ ድካም ተጋላጭነትን ይጨምራሉ። 

 

 

የልብ ድካም ምልክቶች 

በልብ የደም ስር የተከማቸው ስብ በድንገት ተላቆ የደም ዝውውሩን ሲገታ የልብ ድካም ምልክቶች ይከሰታሉ። ምልክቶቹም ከሰው ሰው ሊለያዩ ይችላሉ፤ እንዲሁም በሴቶችና ወንዶች መከል ሊለያይ ይችላል። የልብ ድካም ያጋጠመው ሰው የሚከተሉትን ምልክቶች ያሳያል።

. የደረት ህመም፡ የህመሙ ደረጃ ከትንሽ እስከ ከባድ ሊሆን ይችላል፤ ታማሚው ደረቱ ላይ መክበድ፣ መጨምደድ፣ መግፋት ሊሰማው ይችላል፤ ህመሙ ከ3 እስከ 5 ደቂቃ የሚቆይ ወይም ሄድ መለስ የሚል ይሆናል ነገር ግን ህመሙ ከ10 ደቂቃዎች በላይ ከቆየ አስጊ ደረጃ የመድረሱ ማሳያ ነው። የልብ ድካምን ህመም ከቃር ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ህመሙ የአቀማመጥ ቦታን በመቀያየር አይጠፋም፡፡ የህመሙ ስሜት ወደ ትከሻ፣ የግራ እጅ፣ አገጭና አንገት መሰራጭት ሊኖረው ይችላል።

. ለመተንፈስ መገር፣ ትንፋሽ መቆራረጥ፣ ቶሎ ቶሎ መተንፈስ፤ በላብ መዘፈቅ፣ ማዞርና ድንግዝግዝ ማለት፤ ማቅለሽለሽና ማስመለስ፤ ድካም ድካም ማለት፤ የሰውነት መገርጣት፣ ከንፈርና ጣቶች አካባቢ መጥቆር፤ ራስን መሳት ሌሎች የልብ ድካም ምልክቶች ናቸው።

. የልብ ድካም ምልክቶች በሴቶች፣ በአዛውንቶች እና በስኳር ታማሚዎች ላይ የተለየ ምልክቶች ወይም ከነ ጭራሹም ምልክት ላያሳዩ ይችላሉ።

የልብ ድካም የመጀመሪያ እርዳታ

* የልብ ድካም ምልክቶችን ካዩ ወደ አንቡላንስ ይደውሉ፤ እርዳታን ይጠይቁ፤

* የታመመውን ሰው ስራ ላይ ከሆነ አስቁመው፣ ቁጭ ያርጉት፤

* ታማሚውን ያረጋጉት፤ ያበረታቱት (ጭንቀት በሽታውን ያባብሰዋል)

* ከዚህ በፊት የልብ ድካም ታማሚ ከነበረ፤ ለህመም ማስታገሻ መድሃኒት የሚወስድ ከነበረ (እንደ ናይትሮግላይሰሪን) በትዛዙ መሰረት ይስጡ፤

* ታማሚው መዋጥ የሚቸል ከሆነ አስፕሪን ባለ 81 ሚሊግራም 4 ፍሬ
ወይም 325 ሚሊግራም 1 ፍሬ ይስጡት፤ 

* እርዳታ እስኪመጣ ታማሚውን በደንብ ይከታተሉት፤

* ታማሚው ልቡ መምታት ካቆመ እስትንፋስ ለመስጠትና የመጀመሪያ ደረጃ ዕርዳታ ለመስጠት ይዘጋጁ። 

የልብ ድካም ህክምና

1. ወደ ህክምና ሲደርሱ የተለያዩ የደም ምርመራ፣ የኢሲጂ (ECG/EKG) እንዲሁም የልብ አልትራሳወድ (Echocardiography) እንደ አስፈላጊነቱ ይታዘዛል፤

2. የተለያዩ መድሃኒቶችን እንደ  አስፕሪን፣ ክሎፒዶግሪል፣ ሄፓሪን የመሳሰሉ የደም ማቅጠኛ መድሃኒቶች የህመሙን ስርጭት ለመግታት እንዲሁም የህመም ማስታገሻ ይታዘዛል፤

3. የህክምና ተቋሙ Cath Lab ካለውና የሰለጠነ ባለሞያ ካለው የልብ የደም ስር ህክምና ካልሆነም ደግሞ በመድሃኒትቶች (Thrombolysis) በመጠቀም የረጋውን ደም የማፍረስ ህክምና ይሰጣል።

4. የልብ ድካም ክትትል ስለሚፈልግ ለቀናት ጽኑ ህክምና ክፍል ክትትል ይደረጋል።

5. ህመሙ በቂ እረፍት እና ጭንቀትን ማስወገድ ይኖርብናል።

6. አብዛኞቹ መድሃኒቶች ለረዥም ጊዜ የሚወሰዱ ሲሆን የተወሰኑትም የማይቋረጡ እና ዕድሜ ልክ የሚወሰዱ ስለሆኑ ከሀኪም ትዕዛዝ ውጭ መድሀኒቶችን ማቋረጥ ለከፋ አደጋ ያጋልጣል።

7. ህመሙ ከታከመ በኃላ ወደ ተለመደው የዕለትተለት ተግባር የመመለስ ሂደቱን ቀስ በቀስ መሆን የሚኖርበት ሲሆን ከሀኪም ጋር ምክክርን ይጠይቃል።

 የልብ ድካም እንዴት እንከላከል?

1. የደም ግፊት በትክክል መቆጣጥር

የታዘዘመድሃኒት በትክክል መውሰድ፣ 

2. የተመጣጠነ የአመጋገብ ስርአት መከተል፤(ፍራፍሬ፣ ጥራጥሬ፣ የእጽዋት ተዋጽኦ ዘይቶችን…)

3. የኮሌስትሮል መጠን መቀነስ፤

4. ስኳር ህመም ካለ በአግባቡ ክትትል ማድረግ፣

5. አደንዛዥ ዕፅ ከመጠቀም፣ ሲጋራ ከማጨስ፣ አልኮል ከመጠቀም መቆጠብ

6. ከመጠን ያለፈ ውፍረት ማስወገድ እንዲሁም አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ያስፈልጋል