በ ዶ/ር ኤርምያስ ካቻ በWeil Cornell የሳንባና የፅኑ ሕክምና ፈሎው
የመተንፈሻ አካላትን የሚያጠቁ ቫይረሶች በዋነኛነት በሶስት መንገዶች ይተላለፋሉ። የኋለኞቹ ሁለቱ በተለምዶ አየር ወለድ ተላላፊ (airborne) ይባላሉ።
● በንክኪ የሚተላለፉ (Contact transmission)
● በጠብታ የሚተላለፉ (Droplet transmission)
● በረቂቅ ብናኝ የሚተላለፉ (Aerosol transmission)
የተለያዩ ቫይረሶች አንደ ቫይረሱ ባህርይ፣ የአካባቢ ሙቀት፣ የስዎች ተጠጋግቶ መኖርና በመሳሰሉት ሌሎች ምክንያቶች የተለያየ አይነት መተላለፊያ መንገድ ይኖራቸዋል።
ለምሳሌ አዴኖቫይረስና ኢንተሮቫይረስ የተባሉት መሸፈኛቸው ቅባት የሌላቸው ቫይረሶች ለረጅም ሰዓት አንዳንዴም ለቀናት ግዑዝ ነገሮች ላይ ተጣብቀው ይቆያሉ። በተቃራኒው መሸፈኛቸው ቅባት ያላቸው ለምሳሌ እንደ እንፍሉዬንዛ ያሉ ቫይረሶች ቶሎ የመድረቅና ወደሌላው የመተላለፍ አቅማቸው ይቀንሳል።
ብዙዎቹ ቫይረሶች ከአንድ በላይ የመተላለፊያ መንገዶች ሊኖራቸው ቢችልም በዋነኛነት በአንዱ ብቻ ይተላለፋሉ።
በንክኪ የሚተላለፉ (Contact transmission)
በንክኪ የሚተላለፉ ስንል ሁለት ነገሮችን ያካትታል። ቀጥተኛ የሆነ (direct) አና ቀጥተኛ ያልሆነ (indirect)። ቀጥተኛ የሆነ ስንል የታመመው ወይም በሽታው ያለበት ሰው ጤነኛ ሰው ሲነካና ጤነኛው ሰው ባልታጠበ እጅ አፉን፣ አይኑን፣ ወይም አፍንልጫውን ሲነካ በሽታው ይተላለፋል። ይህም ማለት በሽታው በቀጥታ ከታመመው ሰው ወዳልታመመው ሰው ይተላለፋል ማለት ነው።
ቀጥተኛ ያልሆነ (indirect) ስንል የታመመው ሰው የሚነካቸው ማንኛውም ነገሮች ለበሽታው መተላለፍ አንደመሻገሪያ ሊያገለግሉ ይችላሉ።
ለምሳሌ የታመመው ሰው የነካው የበር አጀታ አንድ ጤነኛ ሰው ቢነካ እና ከዚያ ደግሞ ባልተጠበ አጅ፣ አፍ፣ አፍንጫውን ቢነካ በሽታው ሊተላለፍበት ይችላል ።
ለምሳሌ ሬስፕራቶሪ ሲንስሺያል ቫይረስ (RSV) በዋነኝነት በመነካካት ይተላለፋል። በመነካካት የሚተላለፉ ቫይረሶች የተያዙ በሽተኞችን በሚመረምሩበት ግዜ፣ ባለሞያዎች ጊዜያዊ ጋዎን ያደርጋሉ። በሽታው ካለበት ሰው በቂ ርቀትን ከጠበቁ በዚህ መንገድ የሚተላለፉ በሽታዎችን መከላከል ይቻላል።
በጠብታ ብናኝ የሚተላለፉ (Droplet transmission)
በሽታው የያዛቸው ሰዎች ሲያወሩ፣ ሲያስነጥሱ ወይም ሲያስሉ ከትንፋሻቸው ጋር የሚወጡ በአይን የማይታዩና መጠናቸው ከአምስት ማይክሮ ሜትር ያላነሱ ጠብታዎች ድሮፕሌት ይባላሉ። እነዚህ ብዙ ጊዜ በአየር ላይ ከ17 ደቂቃ በላይ አይቆዩም። ከታመመውም ሰው ብዙ ጊዜ በአንድ ሜትር ርቀት ውስጥ ይገኛሉ። ለዛም ነው በሰዎች መሃል ያለውን ክፍተት ጠብቁ የሚባለው። እነዚህ ጠብታዎች በቅርብ ርቀት ያለ ጤነኛ ሰው አይን፣ አፍንጫ፣ ወይም አፍ ላይ አርፈው በቀጥታ በሽታውን ሊያስተላልፉ ይችላሉ። በተጨማሪም በቅርብ ርቀት የተገናኘው ሰው አካል ላይ ወይም በቅርብ ርቀት ባሉ ግዑዝ ነገሮች ላይ በማረፍም ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ በሽታውን ሊያስተላልፉ ይችላሉ።
አንደ ኢንፍሉዌንዛና አዲሱ ኮሮና ቫይረስ ያሉ ቫይረሶች በዋነኛነት በጠብታዎች ይተላለፋሉ። ለዛም ነው ተከታዮቹን ጥንቃቄዎች ሁሉ ማድረግ ያለብን።
- ጠብታዎቹ ሊደርሱባቸው የሚችሉበትን ርቀት መጠበቅ
- ርቀትን መጠበቅ ካልተቻለ ደግሞ ጭንብል ማድረግ
- በተጨማሪም ጠብታዎች ቀጥተኛ ወይም ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ አጃችን ላይ ሊያርፉ ስለሚችሉ አጃችንን ሁልጊዜ በሚገባ መታጠብ
በረቂቅ ብናኝ የሚተላለፉ (Aerosol transmission)
አንዚህ ረቂቅ ብናኞች መጠናቸው አነስተኛ ከመሆኑ የተነሳ (ከአምስት ማይክሮ ሜትር ያነሰ) በአየር ላይ በመንሳፈፍ ለረጅም ቀናት ሊቆዩ ይችላሉ። በተጨማሪም ከታመሙ ሰዎች ከአንድ ሜትር በላይ ርቀትም ይሄዳሉ። በአየር ላይ በመንሳፈፍ ለረጅም ቀናት ሊቶዩ ይችላሉ። በተጨማሪም ከታመሙ ሰዎች ወጥተው ከአንድ ሜትር በላይ ርቀትም ይሄዳሉ። ጤነኛ ሰዎች በነዚህ ረቂቅ ብናኞች የተበከለ አየር በሚተነፍሱበት ጊዜ ብናኞቹ ወደ ሳንባ በቀጥታ በመግባት በሽታውን ያስተላልፋሉ። አንዳንዴ በዋነኛነት በጠብታ የሚተላለፉ ቫይረሶች ለህክምና ተብሎ በሚደረጉ ሂደቶች ረቂቅ ብናኝ (aerosol) ሊፈጥሩ ይችላሉ።
ለምሳሌ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ጽኑ የሆነ የሳንባ ምች ያለባቸው ሰዎች የመተንፈሻ ማሽን ላይ መሆን ቢኖርባቸውና ያንን ለማከናወን በሚደረጉ የማደንዘዝና የመተንፈሻ ቱቦ የማስገባት ሂደት ላይ እነዚህ ሂደት ላይ እነዚህ ረቂቅ ብናኝ (aerosol) ሊፈጠሩ ይችላሉ። ለዛም ነው ለምሳሌ በተወሰነ የሆስፒታል ክፍል ውስጥ የሚሰሩ ባለሙያዎች ብቻ N-95 ማስክ (ጭንብል) እንዲያደርጉ የሚመከረው።
በዋነኝነት በኤሮሶል የሚተላለፍ የቫይረስምሳሌ ኩፍኝ (Measles) ነው።
ታድያ ኮሮና ቫይረስ ከዚ አንፃር አንዴት ይተላለፋል?
ከላይ አንደተጠቀሰው አዲሱ ኮሮና ቫይረስ በዋነኛነት በ ድሮፕሌት (በጠብታ ብናኝ) ይተላለፋል። በተጨማሪም ቀጥተኛና ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድም በንክኪም ይተላለፋል። ኤይሮሶል የሚያመነጩ የህክምና ፕሮሲጀሮች (ሂደቶች) ካሉ ደግሞ በረቂቅ ብናኝ ሊተላለፍ ይችላል።
የጤና ወግ፡ በመረጃ የተመሰረተ ሕክምና ብቻ ።
………………………………………………………………………………………………………………………..
ይህ የጤና ወግ ድረ ገፅ ነው።
ስለ ጤንነታችሁ ማወቅ የምትፈልጉትን መረጃ የምታገኙበት ፣ በህክምና ባለሙያዎች የሚዘጋጅ የመረጃ ምንጭ ነው።
ሁልግዜም ከሀኪማችሁ ተማከሩ፣ ተጨማሪ መረጃ ከፈለጋችሁ የኛን ድረ ገፅ ጎብኙ።
በጥናት የተደገፈ መረጃ ብቻ እናቀርባለን።
የህክምና ባለሙያዎች ለህሙማኖቻችሁ የሚሆን የሚነበብ መረጃ ከፈለጋችሁ ይህን ገፅ ጠቁሟቸው። ህሙማኖቻችሁ እንዲያውቁት የምትፈልጉትን ነገር መረጃ ጠቅሳችሁ ፃፉልን፣ ስምችሁን ጠቅሰን እናወጣለን። የህክምና ተማሪዎች እንዲጽፉ እናበረታታለን።
በተጨማሪም በጤና ወግ ፖድካስት፣ በ ዩትዩብ ፣በ ትዊተር ፣ በ ፌስቡክ ፣ በቴሌግራም የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ገፆቻችን ታገኙናላችሁ